Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ነገሥት 23 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ኢዮስያስ አረማዊ አምልኮን ማስወገዱ
( 2ዜ.መ. 34፥3-7 ፤ 29-33 )

1 ንጉሥ ኢዮስያስ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን የታወቁ ሽማግሌዎች ሁሉ ጠራ፤

2 እነርሱም ካህናት፥ ነቢያት፥ ሌሎችም ሰዎች ከታናሾች ጀምሮ እስከ ታላቆች ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ መጡ፤ ንጉሡም በዚያ ጠፍቶ በነበረውና በቤተ መቅደስ በተገኘው መጽሐፍ የሰፈረውን ቃል በሙሉ ለሕዝቡ አነበበ፤

3 ንጉሡ በዐምዱ አጠገብ ቆሞ በሙሉ ልቡና ሐሳቡ እግዚአብሔርን ለመከተልና ትእዛዞቹን፥ ደንቦቹንና ድንጋጌዎቹን ለመጠበቅ በእርሱ ፊት ቃል ኪዳኑን አደሰ፤ ስለዚህም በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ቃል ኪዳን አረጋገጠ፤ ሕዝቡም በቃል ኪዳኑ ተባበረ።

4 ከዚህም በኋላ ኢዮስያስ ሊቀ ካህናቱን ሒልቅያን፥ ረዳቶቹ የሆኑትን ካህናትና የቤተ መቅደሱን መግቢያ በር ዘብ የሚጠብቁ ተረኞችን ጠርቶ ለበዓልና አሼራ ተብላ ለምትጠራው ሴት አምላክ፥ እንዲሁም ለከዋክብት ማምለኪያ ያገለግሉ የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ ከቤተ መቅደስ ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው፤ ንጉሡም እነዚያን ዕቃዎች ሁሉ ከኢየሩሳሌም ውጪ ባለው በቄድሮን ሸለቆ በእሳት አቃጥሎ ዐመዱን ወደ ቤትኤል ወሰደው፤

5 በይሁዳ ከተማዎችና በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ባሉት ስፍራዎች ሁሉ በየኰረብታው ላይ በነበሩት መሠዊያዎች መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ የይሁዳ ነገሥታት ሾመዋቸው የነበሩትን ካህናት ሁሉ ከሥራ አሰናበተ፤ በዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ፥ ለፀሐይ፥ ለጨረቃ፥ ፀሐይን ለሚዞሩ ዓለማትና ለከዋክብት መሥዋዕት በማቅረብ የሚያገለግሉ ካህናትን ሁሉ ሻረ፤

6 አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ከቤተ መቅደስ ነቅሎ ከከተማይቱ በማውጣት ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ትቢያ እስኪሆንም አድቅቆ፥ በሕዝብ መቃብር ላይ በተነው።

7 ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ወንዶች በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚያገለግሉበትንና ሴቶችም አሼራ ተብላ ለምትጠራው ሴት አምላክ መጋረጃ የሚፈትሉበትን ክፍል ሁሉ ደመሰሰ።

8 በይሁዳ ከተሞችና በመላ ሀገሪቱ ከገባዕ እስከ ቤርሳቤህ የነበሩትን ካህናት ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣ፤ መሥዋዕት ያቀርቡባቸው የነበሩትን መሠዊያዎች ሁሉ ርኩስ መሆናቸውን ዐወጀ፤ እንዲሁም የከተማይቱ ገዢ ኢያሱ ወደ ከተማይቱ ሲገቡ ከዋናው ቅጽር በር በስተ ግራ በኩል ባሠራው ቅጽር በር አጠገብ የሚገኙትን መስገጃዎች አፈራረሰ።

9 እነዚያም ካህናት በቤተ መቅደስ ከማገልገል ታገዱ፤ ይሁን እንጂ ለጓደኞቻቸው ካህናት ይሰጥ የነበረውን እርሾ ያልነካው ኅብስት እንዲመገቡ ተፈቅዶላቸው ነበር።

10 ንጉሥ ኢዮስያስ በሒኖም ሸለቆ የነበረው “ቶፌት” ተብሎ የሚጠራው የአሕዛብ ማምለኪያ ቦታ የረከሰ መሆኑን አስገነዘበ፤ ከዚህም የተነሣ “ሞሌክ” ተብሎ ለሚጠራው አምላክ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብ ማንም እንዳይኖር ተከለከለ፤

11 የይሁዳ ነገሥታት ለፀሐይ አምልኮ መድበዋቸው የነበሩትን ፈረሶች ሁሉ አስወገደ፤ ለዚሁ አምልኮ የሚያገለግሉ የነበሩትን ሠረገሎች አቃጠለ፤ እነዚህ ሁሉ ቀደም ሲል ታላቁ ባለ ሥልጣን ናታን ሜሌክ በሚኖርባቸው ክፍሎች አጠገብና በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቅጽር በር አጠገብ ይገኙ ነበር፤

12 ንጉሥ አካዝ ባሠራቸው መኖሪያ ክፍሎች ጣራ ላይ በሚገኘው ቤተ መንግሥት የይሁዳ ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትን መሠዊያዎችና በቤተ መቅደሱ ሁለት አደባባዮች ንጉሥ ምናሴ አሠርቶአቸው የነበሩትን መሠዊያዎች ሁሉ ኢዮስያስ ደመሰሳቸው፤ መሠዊያዎቹንም አንኮታክቶ ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወስዶ ጣላቸው።

13 እንዲሁም ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ከርኲሰት ተራራ በስተ ደቡብ ዐስታሮት ተብላ ለምትጠራው ለሲዶና አምላክ፥ ከሞሽ ተብሎ ለሚጠራው ለሞዓብ አምላክና ሞሌክ ተብሎ ለሚጠራው ለዐሞን አምላክ ንጉሥ ሰሎሞን አሠርቶአቸው የነበሩት አጸያፊዎች ምስሎች ሁሉ የረከሱ መሆናቸውን አስገነዘበ።

14 ንጉሥ ኢዮስያስ የድንጋይ ዐምዶችን ሁሉ ሰባበረ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውንም የሴት አምላክ ምስሎች አንኮታክቶ ጣለ፤ እነርሱ ቆመውበት የነበረውንም ስፍራ የሙታን አጥንት ሞላበት።

15 እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በቤትኤል አሠርቶት የነበረውን የማምለኪያ ቦታ ኢዮስያስ አፈራርሶ ጣለ፤ መሠዊያውን ነቅሎ፥ የተሠራበትን ድንጋይ ሁሉ ሰባብሮ በማድቀቅ እንደ ትቢያ አደረገው፤ የአሼራንም ምስል በእሳት አቃጠለ፤

16 ከዚህም በኋላ ኢዮስያስ ዙሪያውን ሲመለከት፥ በኰረብቶች ላይ የተሠሩ መቃብሮችን አየ፤ በእነዚያም መቃብሮች ውስጥ የነበረውን ዐፅም ሁሉ አስወጥቶ በመሠዊያው ላይ በእሳት አቃጠለው፤ በዚህም ዓይነት መሠዊያው የረከሰ መሆኑን አስገነዘበ፤ ኢዮስያስ ይህንን ሁሉ በማድረጉ ከብዙ ጊዜ በፊት በተደረገ የአምልኮ በዓል ላይ ንጉሥ ኢዮርብዓም በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ ነቢዩ የተናገረው የትንቢት ቃል ተፈጸመ፤ ንጉሥ ኢዮስያስ ዙሪያውን ሲመለከት ይህን ትንቢት ተናግሮ የነበረው ነቢይ የተቀበረበትን መካነ መቃብር አይቶ፥

17 “ያ መቃብር የማን ነው?” ሲል ጠየቀ። የቤትኤልም ሕዝብ “ከይሁዳ መጥቶ በዚህ መሠዊያ ላይ ይህን አንተ ያደረግኸው ነገር ሁሉ እንደሚፈጸምበት ተናግሮ የነበረው የነቢዩ መቃብር ነው” ሲሉ መለሱለት።

18 ኢዮስያስም “እንዳለ ይኑር፤ ተውት፤ የእርሱ ዐፅም ከዚህ መንቀሳቀስ የለበትም!” ሲል መለሰ። ስለዚህም የእርሱም ሆነ የሰማርያው ነቢይ ዐፅሞች ከዚያ እንዲነሡ አልተደረገም።

19 ንጉሥ ኢዮስያስ በማንኛይቱም የእስራኤል ከተማ የእስራኤል ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትን የእግዚአብሔርን ቁጣ ለማነሣሣት ምክንያት የሆኑትን የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሁሉ አፈራረሰ፤ በቤትኤል ያደረገውን ሁሉ በእነዚያ መሠዊያዎች ላይ ፈጸመ፤

20 በእነዚያ መሠዊያዎች ላይ ያገለግሉ የነበሩትንም አሕዛብ ካህናትን ገደለ፤ በመሠዊያዎቹም ላይ አጥንት አቃጠለባቸው። ይህን ሁሉ ከፈጸመ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።


ኢዮስያስ የፋሲካን በዓል ማክበሩ
( 2ዜ.መ. 35፥1-19 )

21 ንጉሥ ኢዮስያስ በቃል ኪዳኑ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር የፋሲካን በዓል ያከብሩ ዘንድ ሕዝቡን አዘዘ።

22 መሳፍንት የሕዝቡ ገዢዎች ከነበሩበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን በማንኛዎቹም የእስራኤል ወይም የይሁዳ ነገሥታት አማካይነት ይህን የመሰለ የፋሲካ በዓል ተከብሮ አያውቅም።

23 ይሁን እንጂ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ተከበረ።


ኢዮስያስ ያደረገው ሌላው ለውጥ

24 ሊቀ ካህናቱ ሒልቂያ በቤተ መቅደስ ባገኘው መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈው ሕግ ሁሉ ተፈጻሚነት እንዲኖረው በማሰብ፥ ንጉሥ ኢዮስያስ ከኢየሩሳሌምና ከሌላውም የይሁዳ ከተማ ሁሉ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ሁሉ የቤተሰብ አማልክትን፥ ጣዖቶችንና ሌሎችንም አረማዊ የአምልኮ መፈጸሚያ ዕቃዎችን ሁሉ አስወገደ።

25 ለኦሪት ሕግ በመታዘዝ በፍጹም ልቡ፥ በፍጹም ነፍሱና በፍጹም ኃይሉ እግዚአብሔርን ያገለገለ እንደ ኢዮስያስ ያለ ንጉሥ ከእርሱም በፊት ሆነ ከእርሱ ወዲህ ከቶ አልነበረም።

26 ነገር ግን ይህም ሁሉ ሆኖ ንጉሥ ምናሴ ባደረገው ክፉ ነገር ምክንያት በይሁዳ ላይ የነደደው አስፈሪ የእግዚአብሔር ቁጣ እስከ አሁን ድረስ ገና አልበረደም ነበር።

27 ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “በእስራኤል ላይ ያደረግኹትን ነገር ሁሉ በይሁዳም ላይ አደርጋለሁ፤ ይኸውም የይሁዳን ሕዝብ ከፊቴ አስወግዳለሁ፤ የመረጥኳትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና ስሜ በዚያ ይጠራል ብዬ የነበረውንም ቤተ መቅደስ እተዋለሁ።”


የኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ
( 2ዜ.መ. 35፥20—36፥1 )

28 ንጉሥ ኢዮስያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤

29 በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት ነኮ የተባለው የግብጽ ንጉሥ የአሦርን ንጉሠ ነገሥት ለመርዳት ሠራዊቱን እየመራ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ተጓዘ፤ ንጉሥ ኢዮስያስም መጊዶ ላይ የግብጽን ሠራዊት ለማገድ ጦርነት ገጥሞ በዚያ ውጊያ ላይ ተገደለ፤

30 ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖችም ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥተው እዚያ በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ። የይሁዳም ሰዎችም የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአካዝን መረጡ፤ ቀብተውም አነገሡት።


የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአካዝ
( 2ዜ.መ. 36፥2-4 )

31 ኢዮአካዝ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሀያ ሦስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሦስት ወር ገዛ፤ እናቱም ሐሙጣል ተብላ የምትጠራ የልብና ከተማ ተወላጅ የሆነው የኤርምያስ ልጅ ነበረች፤

32 ኢዮአካዝም የቀድሞ አባቶቹ እንዳደረጉት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።

33 እርሱንም ኒካዑ ተብሎ የሚጠራው የግብጽ ንጉሥ ኢዮአካዝ በኢየሩሳሌም እንዳይነግሥ በሐማት ምድር በምትገኘው በሪብላ እስረኛ በማድረግ፥ ይሁዳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ኪሎ ብር፥ ሠላሳ አራት ኪሎ ወርቅ ግብር እንዲከፍል ባደረገው ጊዜ የኢዮአካዝ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ ሆነ።

34 ንጉሥ ኒካዑ የኢዮስያስ ልጅ ኤልያቄም በአባቱ በኢዮስያስ እግር ተተክቶ በይሁዳ እንዲነግሥ አደረገ፤ ስሙንም በመለወጥ ኢዮአቄም ብሎ ጠራው፤ ኢዮአሐዝም በንጉሥ ነኮ ተማርኮ ወደ ግብጽ ተወሰደ፤ በዚያም ሞተ።


የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም
( 2ዜ.መ. 36፥5-8 )

35 ኢዮአቄም ንጉሥ ነኮ የጠየቀውን ብርና ወርቅ ከፈለ፤ ይህንንም ለማድረግ እንደየችሎታው በሕዝቡ ላይ ግብር ጣለ።

36 ኢዮአቄም በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሀያ አምስት ዓመት ነበር፤ መኖርያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ዘቢዳ ተብላ የምትጠራ የሩማ ከተማ ተወላጅ የሆነው የፐዳያ ልጅ ነበረች።

37 ኢዮአቄም የቀድሞ አባቶቹ እንደ አደረጉት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos