Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ነገሥት 11 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የይሁዳ ንግሥት ዐታልያ (ጎቶሊያ)
( 2ዜ.መ. 22፥10—23፥15 )

1 የንጉሥ አካዝያስ እናት ዐታልያ የልጇን መገደል እንደ ሰማች ወዲያውኑ የይሁዳ ንጉሣውያን ቤተሰብ አባላት በሙሉ እንዲገደሉ ትእዛዝ ሰጠች።

2 ከእርሷም እጅ ማምለጥ የቻለ የአካዝያስ ልጅ ኢዮአስ ብቻ ነበር፤ እርሱም እንኳ ከሌሎቹ ጋር እንዲገደል ተመክሮበት ነበር፤ ነገር ግን አክስቱ የነበረችው በአባትዋ በኩል የንጉሥ አካዝያስ እኅት የሆነችው፥ የንጉሥ ኢዮራም ልጅ ይሆሼባዕ በመደበቅ ከሞት አዳነችው፤ እርሷም እርሱንና ሞግዚቱን ወስዳ በቤተ መቅደሱ ግቢ በሚገኘው ማረፊያ ክፍል ውስጥ ስለ ደበቀችው በዐታልያ እጅ ሳይገደል ቀረ።

3 ዐታልያ በነገሠችበትም ስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ፥ ይሆሼባዕ ሕፃኑን ኢዮአስን በቤተ መቅደስ በመንከባከብ አሳደገችው።

4 ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ካህኑ ዮዳሄ ለንጉሡ ክብር ዘቦችና ለቤተ መንግሥቱ ጠባቂዎች ሁሉ ኃላፊዎች ወደ ሆኑት የጦር መኰንኖች ሁሉ ልኮ ወደ ቤተ መቅደስ እንዲመጡ አስጠራቸው፤ በዚያም ሊያደርገው ያቀደውን ይስማሙበት ዘንድ በመሐላ እንዲያረጋግጡለት አደረገ፤ ከዚያም በኋላ የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን አሳያቸውና፥

5 የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “በሰንበት ቀን ለዘብ ጥበቃ በምትሰማሩበት ጊዜ ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቅ፤

6 ሌላው አንድ ሦስተኛ እጅ የሱርን የቅጽር በር ይጠብቅ፤ የቀረው ሦስተኛ እጅ ደግሞ ከሌሎቹ ዘቦች በስተ ኋላ ያለውን ቅጽር በር ይጠብቅ።

7 በሰንበት ቀን ከዘብ ጥበቃ ነጻ የሆኑት ሁለቱ ቡድኖች ግን በንጉሡ ላይ አደጋ እንዳይደርስበት ለመከላከል ቤተ መቅደሱን ይጠብቁ፤

8 ንጉሥ ኢዮአስን በዙሪያው በምትጠብቁበትም ጊዜ ሰይፋችሁን መዛችሁ ወደሚሄድበት ስፍራ ሁሉ አብራችሁ ሂዱ፤ ወደ እናንተ ለመቅረብ የሚደፍር ማንም ቢኖር ይገደል።”

9 የጦር መኰንኖቹም ዮዳሄ የሰጠውን መመሪያ በመቀበል በሰንበት ቀን ለዘብ ጥበቃ የሚሰማሩትንና ከዘብ ጥበቃም የሚወጡትን ጭፍሮቻቸውን ጭምር አሰልፈው ወደ እርሱ አመጡ።

10 ዮዳሄም በቤተ መቅደስ ተቀምጠው ይጠበቁ የነበሩትን የንጉሥ ዳዊትን ጦሮችና ጋሻዎች አውጥቶ ለጦር አለቆቹ ሰጣቸው፤

11 ጭፍሮቹም ሰይፋቸውን እንደ መዘዙ ንጉሡን ከአደጋ ለመከላከል በመሠዊያው በኩል በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ዙሪያውን እንዲሰለፉ አደረጋቸው።

12 ከዚያም በኋላ ዮዳሄ ኢዮአስን አውጥቶ በራሱ ላይ ዘውድ ጫነበት፤ ለመንግሥቱ መመሪያ የሆነውንም ሕግ አንድ ቅጂ አስረከበው፤ በዚህ ዓይነት ኢዮአስ ተቀብቶ ነገሠ፤ ሕዝቡም እያጨበጨበ ድምፁን ከፍ አድርጎ “ረጅም ዕድሜ ለንጉሡ!” አለ።

13 ንግሥት ዐታልያም የክብር ዘቦቹንና የሕዝቡን ጩኸት ድምፅ በሰማች ጊዜ ሕዝቡ ወደተሰበሰበበት ቤተ መቅደስ ፈጥና ሄደች።

14 እዚያም እንደ ደረሰች አዲሱ ንጉሥ በተለመደው ባህል መሠረት በቤተ መቅደሱ መግቢያ በሚገኘው ዐምድ አጠገብ ቆሞ አየችው፤ እርሱም በጦር አዛዦችና በእምቢልታ ነፊዎች ታጅቦ ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ በደስታ ተሞልተው እልል እያሉ እምቢልታ ይነፉ ነበር፤ ዐታልያም በድንጋጤ ልብስዋን ቀዳ “ይህ በክሕደት የተፈጸመ ሤራ ነው! ሤራ ነው!” ስትል ጮኸች።

15 ዮዳሄ በበኩሉ ዐታልያ በቤተ መቅደሱ ክልል ውስጥ እንድትገደል አልፈለገም፤ ስለዚህም የጦር አለቆቹን “ግራና ቀኝ በተሰለፉት ዘቦች መካከል አውጥታችሁ ውሰዱአት፤ እርሷን ለመከተል የሚሞክር ቢኖር ይገደል” ሲል አዘዛቸው።

16 እነርሱም እርሷን አፈፍ አድርገው በመያዝ ወደ ቤተ መንግሥት ወሰዱአት፤ እዚያም የፈረስ መግቢያ ቅጽር በር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ገደሉአት።


ዮዳሄ ያደረገው ተሐድሶ
( 2ዜ.መ. 23፥16-21 )

17 ዮዳሄ፥ ንጉሡና ሕዝቡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡ አደረገ፤ እንዲሁም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን እንዲኖር አደረገ።

18 ከዚህም በኋላ ሕዝቡ ወደ በዓል ቤተ መቅደስ ሄዶ አፈራረሰው፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሁሉ ሰባበረ፤ ማታን ተብሎ የሚጠራውንም የበዓል ካህን በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደለው። ዮዳሄ ቤተ መቅደሱን በየተራ የሚጠብቁ ዘበኞችን መደበ፤

19 ከዚህም በኋላ እርሱ፥ የጦር አለቆች፥ የንጉሡ ክብር ዘብና የቤተ መንግሥቱ ዘብ ጠባቂዎች ንጉሡን ከቤተ መቅደስ እስከ ቤተ መንግሥት አጅበው እንዲሄዱና ሕዝቡም ሁሉ ከኋላ እንዲከተል አደረገ፤ ኢዮአስም በዘብ ጠባቂዎች ቅጽር በር በኩል ገብቶ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ።

20 ዐታልያ ስለ ተገደለች ሰው ሁሉ ተደሰተ፤ ከተማይቱም ጸጥ አለች።

21 ኢዮአስም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos