2 ዜና መዋዕል 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የንጉሥ ሰሎሞነን የተለያዩ ተግባራት 1 እንዲህም ሆነ፤ ሰሎሞን የጌታን ቤትና የራሱን ቤት የሠራበት ሀያ ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ 2 ኪራም ለሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ሰሎሞን ዳግመኛ ሠራቸው፥ የእስራኤልንም ልጆች አሰፈረባቸው። 3 ሰሎሞንም ወደ ሐማት-ሱባ ሄደ አሸነፋትም። 4 በምድረ በዳም ያለውን ተድሞርን፥ በሐማትም የሠራቸውን ለግምጃ ቤት የሚያገለግሉትን ከተሞች ሁሉ ሠራ። 5 ደግሞም ቅጥርና መዝጊያ መቀርቀሪያም የነበራቸውን የተመሸጉትን ከተሞች ላይኛውን ቤት-ሖሮን ታችኛውንም ቤት-ሖሮን ሠራ። 6 ባዓላትንም፥ ለሰሎሞንም የነበሩትን ለግምጃ ቤት የሚያገለግሉ ከተሞች ሁሉ፥ የሠረገላውንም ከተሞች ሁሉ፥ የፈረሰኞችንም ከተሞች፥ በኢየሩሳሌምም በሊባኖስም በመንግሥቱም ምድር ሁሉ ሰሎሞን ለመሥራት የፈለገውን ሁሉ ሠራ። 7 ከኬጢያውያንም ከአሞራውያንም ከፌርዜያውያንም ከኤዊያውያንም ከኢያቡሳውያንም የቀሩትን ከእስራኤል ወገን ያልሆኑትን ሕዝብ ሁሉ፥ 8 የእስራኤልም ልጆች ያላጠፉአቸውን፥ በኋላቸው በምድሪቱ ላይ የቀሩትን ልጆቻቸውን ሰሎሞን እስከ ዛሬ ድረስ ገባሮች አድርጎ መለመላቸው። 9 ሰሎሞንም ለሥራው ከእስራኤል ልጆች ማንንም ባርያ አላደረገም፤ እነርሱ ግን ወታደሮች፥ የሹማምቶችም አለቆች፥ የሰረገሎችና የፈረሰኞች ባልደራሶች ነበሩ። 10 እነዚህም በሕዝቡ ላይ ሥልጣን የነበራቸው የንጉሥ ሰሎሞን ከፍተኛ ሹማምት ሁለት መቶ ኀምሳ ነበሩ። 11 ሰሎሞንም፦ “የጌታ ታቦት የገባበት ስፍራ ቅዱስ ነውና ሚስቴ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤት አትቀመጥም” ሲል የፈርዖንን ልጅ ከዳዊት ከተማ አውጥቶ ወደ ሠራላት ቤት አመጣት። 12 በዚያን ጊዜም ሰሎሞን በወለሉ ፊት በሠራው በጌታ መሠዊያ ላይ ለጌታ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ። 13 ሙሴም እንዳዘዘ እንደ ሥርዓታቸው ዘወትር በየቀኑ፥ በየሰንበታቱም፥ በየመባቻዎቹም፥ በየተወሰኑትም በዓላት፥ በየዓመቱ ሦስት ጊዜ በየቂጣው በዓልና በየሰባቱ ሱባዔ በዓል በየዳሱም በዓል ቁርባን ያቀርቡ ነበር። 14 የጌታም ሰው ዳዊት እንዲህ አዝዞ ነበርና ካህናቱን እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሥርዓት በየአገልግሎታቸው ሰሞን ከፈላቸው፤ ሌዋውያንም እንደ ሥርዓታቸው እንዲያመሰግኑ፥ በካህናቱም ፊት እንዲያገለግሉ በየሰሞናቸው ከፈላቸው፤ ጠባቂዎችንም ደግሞ በየበሩ ሁሉ በየሰሞናቸው ከፈላቸው። 15 እነርሱም ንጉሡ ስለ ነገሩ ሁሉና ስለ መዝገቡ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ያዘዘውን ነገር ሁሉ አልተላለፉም። 16 የጌታም ቤት መሠረት ከተጣለ ጀምሮ እስከ ተጨረሰበት ጊዜ ድረስ የሰሎሞን ሥራ ሁሉ የተሳካ ነበረ። የጌታም ቤት ተፈጸመ። 17 ሰሎሞንም የዚያን ጊዜ በኤዶምያስ ምድር በባሕር ዳር ወዳሉ ወደ ዔጽዮን-ጋብርና ወደ ኤሎት ሄደ። 18 ኪራምም መርከቦችንና የባሕርን ነገር የሚያውቁትን መርከበኞች በባርያዎቹ እጅ ላከለት፤ እነርሱም ከሰሎሞን ባርያዎች ጋር ወደ ኦፊር መጡ፥ ከዚያም አራት መቶ ኀምሳ መክሊት ወርቅ ወስደው ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን አመጡ። |