Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ዜና መዋዕል 32 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የሰናክሬም ወረራ

1 ከዚህም ነገርና በታማኝነት ከተደረገው ነገር በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ወደ ይሁዳ ገባ፥ በተመሸጉትም ከተሞች ፊት ሰፈረ፥ የራሱም ሊያደርጋቸው አሰበ።

2 ሕዝቅያስም ሰናክሬም እንደመጣ፥ ኢየሩሳሌምንም ሊወጋ ፊቱን አንዳቀና ባየ ጊዜ፥

3 ከከተማይቱ በስተ ውጭ ያለውን የውኃውን ምንጭ ለመድፈን ከሹማምንቱና ከኃያላኑ ጋር ተማከረ፤ እነርሱም ረዱት።

4 እጅግም ሰዎች ተሰብስበው፦ “የአሦር ነገሥታት መጥተው ብዙ ውኃ ለምን ያገኛሉ?” ብለው ምንጩን ሁሉ፥ በምድርም መካከል ይንዶለዶል የነበረውን ዥረት ደፈኑ።

5 ንጉሥ ሕዝቅያስም ራሱን ለሥራ ጽኑ አደረገ፥ የፈረሰውንም ቅጥር ሁሉ ጠገነ፥ በላዩም ግንብ ሠራበት፥ ከእርሱም በስተ ውጭ ሌላ ቅጥር ሠራ፤ በዳዊትም ከተማ ያለችውን ሚሎን አጠነከረ፤ ብዙም የጦር መሣሪያና ጋሻ ሠራ።

6 የጦር አዛዦቹንም በሕዝቡ ላይ ሾሞ፥ ሁሉንም በከተማይቱ በር ወዳለው አደባባይ ሰበሰበ፥ እንዲህም ብሎ አበረታታቸው፦

7 “ጽኑ፥ አይዞአችሁ፤ ከእኛም ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ይበልጣልና የአሦርን ንጉሥና ከእርሱ ጋር ያለውን ጭፍራ ሁሉ አትፍሩ፥ አትደንግጡም።

8 ከእርሱ ጋር ያለው ሥጋዊው ክንድ ነው፤ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና የሚዋጋልን ጌታ አምላካችን ነው።” ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃላት ተበረታታ።

9 ከዚህም በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር በለኪሶ ሳለ ባርያዎቹን ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስና በኢየሩሳሌም ወደ ነበሩ ወደ ይሁዳ ሁሉ እንዲህ ሲል ላከ፦

10 “የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም እንዲህ ይላል፦ ‘እናንተ በማን ተማምናችሁ በኢየሩሳሌም ምሽግ ትቀመጣላችሁ?

11 “ጌታ አምላካችን ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል” እያለ በራብና በጥም እንድትሞቱ አሳልፎ ለመስጠት የሚያባብላችሁ ሕዝቅያስ አይደለምን?

12 “በአንድ መሠዊያ ፊት ስገዱ፥ በእርሱም ላይ ዕጠኑ” እያለ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አዝዞ፥ የኮረብታው መስገጃዎቹና መሠዊያዎቹን ያፈረሰ ይህ ሕዝቅያስ አይደለምን?

13 እኔና አባቶቼ በምድር አሕዛብ ሁሉ ያደረግነውን አላወቃችሁምን? የምድርስ ሁሉ አሕዛብ አማልክት አገራቸውን ከእጄ ለማዳን በውኑ ችለዋልን?

14 አባቶቼ ካጠፉአቸው ከአሕዛብ አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄ ለማዳን የቻለ ማንስ ነበር፤ እናንተንስ አምላካችሁ ከእጄ ለማዳን የሚችል ይመስላችኋልን?

15 አሁንም ሕዝቅያስ አያስታችሁ፥ እንዲህም አያባብላችሁ፥ አትመኑትም፤ ከአሕዛብና ከመንግሥታት አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄና ከአባቶቼ እጅ ለማዳን ማንም አልቻለም፤ ይልቁንስ አምላካችሁ ከእጄ ሊያድናቸሁ እንዴት ይችላል?’ ”

16 ባርያዎቹም ደግሞ አምላክ በሆነው በጌታና በባርያው በሕዝቅያስ ላይ ሌላ ብዙ ነገር ተናገሩ።

17 ደግሞም የእስራኤልን አምላክ ጌታን ለመስደብ፥ በእርሱም ላይ ለመናገር፦ “የምድር አሕዛብ አማልክት ሕዝባቸውን ከእጄ ለማዳን እንዳልቻሉ፥ እንዲሁ የሕዝቅያስ አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ሊያድን አይችልም” የሚል ደብዳቤ ጻፈ።

18 ከተማይቱንም ወርሮ ለመውሰድ፥ በቅጥርም ላይ የተቀመጡትን የኢየሩሳሌም ሕዝብ ለማስፈራራትና ለማስደንገጥ፥ በታላቅ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ይጮኹባቸው ነበር።

19 በሰውም እጅ በተሠሩ በምድር አሕዛብ አማልክት ላይ እንደሚናገሩ መጠን በኢየሩሳሌም አምላክ ላይ ተናገሩ።


ሰናክሬም መሸነፉና መሞቱ

20 ንጉሡም ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ነገር ጸለዩ፥ ወደ ሰማይም ጮኹ።

21 ጌታም ጽኑዓን ኃያላኑንና መሳፍንቱን የጦር አዛዦቹንም ከአሦር ንጉሥ ሰፈር እንዲያጠፋ መልአኩን ላከ። የአሦርም ንጉሥ አፍሮ ወደ አገሩ ተመለሰ። ወደ አምላኩም ቤት በገባ ጊዜ ከአብራኩ የወጡት ልጆቹ በዚያ በሰይፍ ገደሉት።

22 እንዲሁም ጌታ ሕዝቅያስንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ከአሦር ንጉሥ ከሰናክሬም እጅ ከጠላቶቻቸውም ሁሉ እጅ አዳናቸው፤ በዙሪያቸውም ካለው ሁሉ አሳረፋቸው።

23 ብዙዎቹም ለጌታ መባ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር፥ ለይሁዳም ንጉሥ ለሕዝቅያስ እጅ መንሻ ይሰጡ ነበር፤ እርሱም ከዚህ ነገር በኋላ በአሕዛብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አለ።


ንጉሥ ሕዝቅያስ መታመሙ

24 በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስኪሞት ድረስ ታመመ፥ ወደ ጌታም ጸለየ፤ እርሱም ተናገረው፥ ምልክትም ሰጠው።

25 ሕዝቅያስ ግን እንደ ተቀበለው ቸርነት መጠን አላደረገም፥ ልቡም ኰራ፤ ስለዚህም በእርሱና በይሁዳ በኢየሩሳሌምም ላይ ቁጣ ሆነ።

26 ሕዝቅያስም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋር ስለ ልቡ ኩራት ራሱን አዋረደ፥ የጌታም ቁጣ በሕዝቅያስ ዘመን አልመጣባቸውም።


የንጉሥ ሕዝቅያስ ሀብትና ስኬት

27 ለሕዝቅያስም እጅግ ብዙ ሀበትና ክብር ነበረው፤ ለብርና ለወርቅም፥ ለከበረው ዕንቁና ለሽቶው፥ ለጋሻውና ለከበረው ዕቃ ሁሉ ግምጃ ቤቶች ሠራ።

28 ለእህልና ለወይን ጠጅም ለዘይትም ዕቃ ቤቶች፥ ለልዩ ልዩም እንሰሳ ጋጥ፥ ለመንጎችም በረት ሠራ።

29 ጌታም እጅግ ብዙ ጥሪት ሰጥቶት ነበርና ከተሞችን ሠራ፥ ብዙም የበግና የላም መንጋ ሰበሰበ።

30 ይህም ሕዝቅያስ የላይኛውን የግዮንን ውኃ ምንጭ ደፈነ፥ በዳዊትም ከተማ በምዕራብ በኩል አቅንቶ አወረደው። የሕዝቅያስም ሥራ ሁሉ ተከናወነ።

31 ነገር ግን የባቢሎን መሳፍንት መልእክተኞች በአገሩ ላይ ስለተደረገው ተአምራት ለመጠየቅ ወደ እርሱ በተላኩ ጊዜ ጌታ እርሱን ለመፈተንና በልቡ ያለውን ሁሉ ለማወቅ ሲል ተወው።

32 የሕዝቅያስም የቀረው ነገር፥ ቸርነቱም፥ እነሆ፥ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራእይ በይሁዳና በእስራኤልም ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።

33 ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ልጆች መቃብር በላይኛው ክፍል ቀበሩት፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ሁሉ ታላቅ የቀብር ሥርዓት አደረጉለት። ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos