2 ዜና መዋዕል 24 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ኢዮአስ ቤተ መቅደሱን ማደሱ 1 ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አርባ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች። 2 በካህኑም በዮዳሄ ዘመን ሁሉ ኢዮአስ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ። 3 ዮዳሄም ሁለት ሚስቶች አጋባው፤ ወንዶችና ሴቶችም ልጆች ወለደ። 4 ከዚህም በኋላ ኢዮአስ የጌታን ቤት ለማደስ አሰበ። 5 ካህናትንና ሌዋውያንንም ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ውጡ፥ የአምላካችሁንም ቤት በየዓመቱ ለማደስ ከእስራኤል ሁሉ ገንዘብን ሰብስቡ፤ ነገሩንም ፈጥናችሁ አድርጉ።” ሌዋውያን ግን ቸል አሉ። 6 ንጉሡም አለቃውን ዮዳሄን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “የጌታ ባርያ ሙሴ ስለ ምስክሩ ድንኳን የእስራኤል ጉባኤ እንዲያወጣ ያዘዘውን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ላይ ሌዋውያን እንዲሰበስቡ ለምን አላተጋሃቸውም?” 7 ጎቶሊያ ከሐዲት ነበረችና ልጆችዋም የጌታን ቤት አፍርሰዋልና፤ በጌታም ቤት ተቀድሶ የነበረውን ሁሉ ለባዓል ተጠቅመውበታልና። 8 ንጉሡም አዘዘ፥ ሣጥንም ሠርተው በጌታ ቤት በር አጠገብ በስተ ውጭ አኖሩት። 9 የጌታም ባርያ ሙሴ በምድረ በዳ በእስራኤል ላይ ያዘዘውን ግብር ለጌታ እንዲያመጡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም አዋጅ ነገሩ። 10 አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ደስ ብሎአቸው ግብሩን አመጡ፥ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ ጣሉት። 11 ሣጥኑም በሌዋውያን እጅ ወደ ንጉሡ ሹማምንት በመጣ ጊዜ፥ ብዙ ገንዘብም እንዳለበት ባየ ጊዜ፥ የንጉሡ ጸሐፊና የታላቁ ካህን ሹም እየመጡ ብሩን ከሣጥኑ ውስጥ ያወጡ ነበር፥ ሣጥኑንም ደግሞ ወደ ስፍራው ይመልሱት ነበር። እንዲህም በየቀኑ ያደርጉ ነበር፥ ብዙም ገንዘብ አከማቹ። 12 ንጉሡና ዮዳሄም በጌታ ቤት ሥራ ላይ ለተሾሙት ሰጡአቸው፤ እነርሱም የጌታን ቤት የሚጠግኑትን ጠራቢዎችንና አናጢዎችን፥ የጌታንም ቤት የሚያድሱትን የብረትና የናስ ሠራተኞችን ይቀጥሩበት ነበር። 13 ሠራተኞችም ሠሩ፥ የፈረሰውም በእጃቸው ተጠገነ፤ የጌታንም ቤት ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ መለሱት፥ አጽንተውም አቆሙት። 14 በጨረሱም ጊዜ የተረፈውን ገንዘብ በንጉሡና በዮዳሄ ፊት አመጡ፤ በእርሱም ለጌታ የቤት ዕቃ፥ የአገልግሎትና የቁርባን ዕቃ፥ ሙዳዮቹም፥ የወርቅና የብርም ዕቃ ተሠራበት። በዮዳሄም ዘመን ሁሉ በጌታ ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት ሁልጊዜ ያቀርቡ ነበር። ኢዮአስ መክዳቱ 15 ዮዳሄም ሸመገለ፥ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ፤ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሠላሣ ዓመት ነበረ። 16 በእስራኤልም፥ ለጌታና ለቤቱም ቸርነትን ሠርቶአልና በዳዊት ከተማ ከነገሥታቱ ጋር ቀበሩት። 17 ዮዳሄም ከሞተ በኋላ የይሁዳ አለቆች ገብተው ለንጉሡ እጅ ነሡ፤ በዚያን ጊዜ ንጉሡ ሰማቸው። 18 የአባቶቻቸውንም አምላክ ጌታን ትተው የማምለኪያ ዐፀዶችንና ጣዖታትን አመለኩ፤ በዚህ በደላቸውም ምክንያት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ቁጣ ወረደ። 19 ወደ ጌታም እንዲመልሱአቸው ነቢያትን ይልክላቸው ነበር፤ መሰከሩባቸውም፥ እነርሱ ግን አላደመጡም። 20 የጌታም መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆሞ እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘የጌታን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? ለእናተም አሳካላችሁም፤ ጌታን ስለ ተዋችሁ እርሱ ትቶአችኋል።’ ” 21 ተማማሉበትም በንጉሡም ትእዛዝ በጌታ ቤት አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ወገሩት። 22 እንዲሁም ንጉሡ ኢዮአስ ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፥ ልጁንም ዘካርያስን አስገደለው፤ እርሱም ሲሞት፦ “ጌታ ይየው፥ ይበቀለውም” አለ። ኢዮአስ መሞቱ 23 በዓመቱ መጨረሻ በኢዮአስ ላይ የሶርያውያን ሠራዊት መጡበት፤ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌምም መጥተው ከሕዝቡ መካከል የሕዝቡን አለቆች ሁሉ አጠፉ፥ ምርኮአቸውንም ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ደማስቆ ላኩ። 24 የሶርያውያንም ሠራዊት ቍጥር ጥቂት ሆኖ ሳለ ጌታ ታላቅን ሠራዊት አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው፤ ይህም የሆነው የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን ትተው ስለ ነበረ ነው። እነርሱም በኢዮአስ ላይ ፍርድ ፈረዱበት። 25 እርሱንም ትተውት በሄዱ ጊዜ በጽኑ አቊስለውት ነበር፤ የገዛ ባርያዎቹም የካህኑ የዮዳሄን ልጅ ደም ለመበቀል ሲሉ አሴሩበት፥ በአልጋውም ላይ ገደሉት፥ ሞተም፤ በዳዊት ከተማ እንጂ በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም። 26 ያሴሩበትም የአሞናዊቱ የሰምዓት ልጅ ዛባድ፥ የሞዓባዊቱም የሰማሪት ልጅ ዮዛባት ነበሩ። 27 የልጆቹና በእርሱ ላይ የተደረገው ነገር የጌታንም ቤት ማደሱ፥ እነሆ፥ በነገሥታቱ መጽሐፍ ተጽፎአል። ልጁም አሜስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |