2 ዜና መዋዕል 23 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ በረታ፥ የመቶ አለቆቹንም፥ የይሮሐምን ልጅ ዓዛርያስን፥ የይሆሐናንንም ልጅ ይስማኤልን፥ የዖቤድንም ልጅ ዓዛሪያስን፥ የዓዳያንም ልጅ መዕሤያን፥ የዝክሪንም ልጅ ኤሊሳፋጥን ወስዶ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። 2 ይሁዳንም ዞሩ፥ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሌዋውያንንና የእስራኤልን አባቶች ቤቶች አለቆች ሰብስበው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 3 ጉባኤውም ሁሉ በጌታ ቤት ውስጥ ከንጉሥ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ዮዳሄም እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ ጌታ ስለ ዳዊት ልጆች እንደ ተናገረ የንጉሡ ልጅ ይነግሣል። 4 የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሰንበት ቀን ከምትገቡት ከእናንተ ከካህናትና ከሌዋዊውያን ከሦስቱ አንዱ በመግቢያ በሮች ላይ ጠባቂዎች ሁኑ፤ 5 ከሦስቱም አንዱ በንጉሥ ቤት ሁኑ፤ እንዲሁም ከሦስቱ አንዱ በመካከለኛው በር ሁኑ፤ ሕዝቡም ሁሉ በጌታ ቤት አደባባይ ይሁኑ። 6 ወደ ጌታ ቤት ግን ከካህናትና ከአገልጋዮቹ ሌዋውያን በቀር ማንም አይግባ፤ እነርሱ ቅዱሳን ናቸውና ይግቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ ግን የጌታን ሕግ ይጠብቅ። 7 ሌዋውያንም የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው ንጉሡን በዙሪያው ይክበቡት፤ ወደ ቤቱም የሚገባ ይገደል ንጉሡም ሲገባና ሲወጣ ከእርሱ ጋር ሁኑ።” ኢዮአስ ዘውድ መጫኑ 8 ሌዋውያንና ይሁዳም ሁሉ ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ ካህኑም ዮዳሄ ሰሞነኞቹን አላሰናበተም ነበርና እያንዳንዱ በሰንበት ቀን ይገቡ የነበሩትን በሰንበትም ቀን ይወጡ የነበሩትን ሰዎች ወሰደ። 9 ካህኑም ዮዳሄ በጌታ ቤት የነበረውን የንጉሡን የዳዊትን ጋሻና ጦር አላባሽ አግሬውንም ጋሻ ለመቶ አለቆች ሰጣቸው። 10 ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ የጦር መሣሪያውን በእጁ እየያዘ በንጉሡ ዙሪያ ከቤቱ ቀኝ እስከ ቤቱ ግራ ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ እንዲቆም አደረገ። 11 የንጉሡንም ልጅ አውጥተው ዘውዱን ጫኑበት፥ ምስክሩንም ሰጡት፥ አነገሡትም፤ ዮዳሄና ልጆቹም፦ “ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ” እያሉ ቀቡት። ጎቶሊያ መገደልዋ 12 ጎቶሊያም የሚሮጡትንና ንጉሡን የሚያመሰግኑትን የሕዝቡን ድምፅ በሰማች ጊዜ ወደ ሕዝቡ ወደ ጌታ ቤት መጣች። 13 እነሆም፥ ንጉሡ በመግቢያው በዓምዱ አጠገብ ሆኖ ከንጉሡም ጋር አለቆችና መለከተኞች ቆመው አየች። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ ብሎአቸው መለከቱን ይነፉ ነበር፤ መዘምራንም በዜማ ዕቃ እያዜሙ የምስጋና መዝሙር ይዘምሩ ነበር። ጎቶሊያም ልብስዋን ቀድዳ፦ “ዓመጽ ነው፥ ዓመጽ ነው” ብላ ጮኸች። 14 ካህኑም ዮዳሄ በጭፍራው ላይ የተሾሙትን የመቶ አለቆች፦ “ከሰልፉ መካከል አውጡአት የሚከተላትም በሰይፍ ይገደል” ብሎ አዘዛቸው። ካህኑም፦ “በጌታ ቤት ውስጥ አትግደሉአት” አለ። 15 እጃቸውን በእስዋ ላይ ጭነው ያዝዋት፤ እርሷም ወደ ፈረሱ በር መግቢያ ወደ ንጉሡ ቤት ሄደች፥ በዚያም ገደሉአት። 16 ዮዳሄም በእርሱና በሕዝቡ ሁሉ በንጉሡም መካከል የጌታ ሕዝብ እንዲሆኑ ቃል ኪዳን አደረገ። 17 ሕዝቡም ሁሉ ወደ ባዓል ቤት ሄደው አፈረሱት፥ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹንም አደቀቁ፥ የባዓልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት። 18 ዮዳሄም በሙሴ ሕግ እንደተጻፈው፥ እንደ ዳዊትም ትእዛዝ፥ በደስታና በመዝሙር ለጌታ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ዳዊት በጌታ ቤት የከፈላቸውን ካህናትና ሌዋውያን በጌታ ቤት አገልግሎት ላይ ሾመ። 19 በማናቸውም ነገር ሁሉ ርኩስ የሆነ ሰው እንዳይገባ በጌታ ቤት በር በጠባቂዎችን አኖረ። 20 የመቶ አለቆችንም፥ ከበርቴዎቹንም፥ የሕዝቡንም አለቆች፥ የአገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፥ ንጉሡንም ከጌታ ቤት ወስደው በላይኛው በር በኩል ወደ ንጉሡ ቤት መጡ፥ ንጉሡንም በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አስቀመጡት። 21 የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፥ ከተማይቱም ጸጥ አለች፤ ጎቶሊያንም በሰይፍ ገደሉአት። |