2 ዜና መዋዕል 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ቤተ መቅደሱን ለመገንባት የሚደረግ ዝግጅት 1 ሰሎሞንም ለጌታ ስም ቤተ መቅደስ፥ ለመንግሥቱም ቤተ መንግሥትን ለመሥራት አሰበ። 2 ሰሎሞንም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ ከተራሮችም የሚጠርቡትን ሰማኒያ ሺህ፥ በእነርሱም ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ቈጠረ። የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ጋር የተደረገ ጥምረት 3 ሰሎሞንም እንዲህ ሲል ወደ ጢሮስ ንጉሥ ወደ ኪራም ላከ፦ “ከአባቴ ከዳዊት ጋር እንዳደረግህ፥ የሚቀመጥበትንም ቤት ለመሥራት የዝግባ እንጨት እንደ ላክኽለት፥ እንዲሁ ለእኔ አድርግ። 4 እነሆ፥ ለእስራኤል ለዘለዓለም እንደ ታዘዘው በጌታ ፊት መዓዛው ያማረውን ሽቶ ዕጣን ለማጠን፥ የተቀደሰውንም ኅብስት ለማኖር፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በጥዋትና በማታ በሰንበታቱም በመባቻዎቹም በአምላካችንም በጌታ በዓላት ለማቅረብ ለአምላኬ ለጌታ ስም ቤት ልሠራለትና ልቀድስለት አሰብሁ። 5 አምላካችንም ከአማልክት ሁሉ በላይ ታላቅ ነውና የምሠራው ቤት ታላቅ የሆነ ነው። 6 ነገር ግን ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይ እርሱን ለመያዝ አይችልምና ለእርሱ ቤት መሥራት ማን ይችላል? በፊቱ ዕጣን ከማጠን በቀር ቤት ልሠራለት የምችል እኔ ማን ነኝ? 7 አሁንም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው በእኔ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ካሉት ብልሃተኞች ጋር አብሮ የሚሆን፥ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንና ብረቱን፥ ሐምራዊውንና ቀዩን ሰማያዊውንም ግምጃ የሚሠራ፥ ቅርጽንም የሚያውቅ ብልሃተኛ ሰው ላክልኝ። 8 ደግሞም ባርያዎችህ ከሊባኖስ እንጨት መቁረጥ እንደሚያውቁ እኔ አውቃለሁና ከሊባኖስ የዝግባና የጥድ የሰንደልም እንጨት ላክልኝ፤ እነሆ፥ ባርያዎቼ ከባርያዎችህ ጋር በመሆን 9 ብዙ እንጨት ያዘጋጁልኛል፥ ስለ ሆነም የምሠራውም ቤት እጅግ ታላቅና ድንቅ ይሆናል። 10 እነሆም፥ እንጨቱን ለሚቈርጡ ለባርያዎችህ ሀያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ የተበጠረ ስንዴ፥ ሀያ ሺህም የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣለሁ።” 11 የጢሮስ ንጉሥም ኪራም ለሰሎሞን በላከው ደብዳቤ እንዲህ ብሎ መለስ ሰጠ፦ “ጌታ ሕዝቡን ወድዶአልና በእነርሱ ላይ አነገሠህ።” 12 እንዲሁም ኪራም እንዲህ አለ፦ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ፥ ለጌታም ቤተ መቅደስ ለመንግሥቱም ቤተ መንግሥት እንዲሠራ ጥበበኛና ብልሃተኛ አስተዋይም ልጅ ለንጉሡ ለዳዊት የሰጠ የእስራኤል አምላክ ጌታ ቡሩክ ይሁን። 13 “አሁንም ኪራም-አቢ የሚባል ብልሃተኛና አስተዋይ ሰው ልኬልሃለሁ። 14 እናቱ ከዳን ልጆች ናት፥ አባቱም የጢሮስ ሰው ነው፤ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንና ብረቱን፥ ድንጋይንና እንጨቱን፥ ሐምራዊውንና ሰማያዊውን ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ ለመሥራት፥ ቅርጽም ለመሥራት ንድፍም ለመንደፍ ሌላም ነገር ሁሉ ለማድረግ እውቀት አለው፥ እርሱም ከብልሃተኛዎችህ ጋር ከጌታዬም ከአባትህ ከዳዊት ብልሃተኞች ጋር አብሮ ይሁን። 15 አሁንም ጌታዬ የተናገረውን ስንዴውንና ገብሱን ዘይቱንና የወይን ጠጁን ወደ ባርያዎቹ ይላክ፤ 16 እኛም ከሊባኖስ የምትሻውን ያህል እንጨት እንቈርጣለን፥ በታንኳም አድርገን በባሕር ላይ ወደ አንተ ወደ ኢዮጴ እናመጣለን፤ አንተም ወደ ኢየሩሳሌም ታስወስደዋለህ።” 17 ሰሎሞንም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ሁሉ አባቱ ዳዊት እንደ ቈጠራቸው ቈጠረ፤ መቶ ኀምሳ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ተገኙ። 18 ከእነርሱም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ በተራሮችም ላይ የሚጠርቡትን ሰማንያ ሺህ፥ የሕዝቡንም ሥራ ለሚቆጣጠር የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎችን ሾመ። |