2 ዜና መዋዕል 19 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 የይሁዳም ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ቤቱ ወደ ኢየሩሳሌም በደኅና ተመለሰ። 2 ባለ ራእዩ የአናኒ ልጅ ኢዩ ሊገናኘው ወጣ፥ ንጉሡንም ኢዮሣፍጥን እንዲህ አለው፦ “ከሐዲውን ታግዛለህን? ወይስ ጌታን የሚጠሉትን ትወድዳለህን? ስለዚህም ነገር ከጌታ ዘንድ ቁጣ ሆኖብሃል። 3 ነገር ግን የማምለኪያ ዐፀዶቹን ከምድሪቱ አስወግደሃልና፥ ጌታን ለመፈለግ ልብህን አዘጋጅተሃልና መልካም ነገር ተገኝቶብሃል።” ኢዮሣፍጥ ማሻሻያ ማድረጉ 4 ኢዮሣፍጥም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ ዳግመኛም ከቤር-ሳቤህ ጀምሮ እስከ ተራራማው እስከ ኤፍሬም አገር ድረስ ወደ ሕዝቡ ወጥቶ ወደ አባቶቻቸው አምላክ ወደ ጌታ መለሳቸው። 5 በምድሪቱም ላይ በተመሸጉት በይሁዳ ከተሞች ሁሉ በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ፈራጆች አኖረ። 6 ፈራጆቹንም እንዲህ አላቸው፦ “ለጌታ እንጂ ለሰው አትፈርዱምና፥ እርሱም በፍርድ ነገር ከእናንተ ጋር ነውና የምታደርጉትን ልብ ብላችሁ ተገንዘቡ። 7 እንግዲህ አሁን ጌታን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን፤ በአምላካችንም በጌታ ዘንድ በደልና ለሰው ፊት ማድላት መማለጃም መውሰድ የለምና ሁሉንም ነገር ተጠንቅቃችሁ አድርጉ።” 8 ኢዮሣፍጥም ከሌዋውያንና ከካህናት ከእስራኤልም የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ በጌታ ስም ፍርድን እንዲፈርዱ በሙግትም ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ በኢየሩሳሌም ሾመ። እነርሱም በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። 9 እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፦ “እንዲህ ስታደርጉ ጌታን በመፍራት በቅንነትም በፍጹምም ልብ አድርጉ። 10 በከተሞቻቸውም ከተቀመጡት ከወንድሞቻቸሁ ዘንድ ስለ ደም መፋሰስ ስለ ሕግና ስለ ትእዛዝ ስለ ሥርዓትና ስለ ፍርድም ማናቸውም ጉዳይ ወደ እናንተ ቢመጣ ጌታን እንዳይበድሉ፥ ቁጣም በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ እንዳይመጣ አስጠንቅቁአቸው፤ እንዲህም ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም። 11 እነሆም፥ ለጌታ በሚሆነው ነገር ሁሉ የካህናቱ አለቃ አማርያ፥ በንጉሡም ነገር ሁሉ የይሁዳ ቤት አለቃ የይስማኤል ልጅ ዝባድያ በላያችሁ ተሹመዋል፤ ሌዋውያኑም ደግሞ በፊታችሁ አለቆች ይሆናሉ፤ በርትታችሁም አድርጉ፥ ጌታም መልካም ከሚያደርግ ጋር ይሁን።” |