Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ዜና መዋዕል 12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ግብጽ ይሁዳን ማጥቃትዋ

1 እንዲህም ሆነ፤ የሮብዓም መንግሥት በጸናች ጊዜ፥ እርሱም በበረታ ጊዜ፥ እርሱና እስራኤል ሁሉ የጌታን ሕግ ተዉ።

2 በጌታ ላይ አልታመኑምና ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ ኢየሩሳሌምን ሊወጋት ወጣ፥

3 እርሱም ሺህ ሁለት መቶ ሰረገሎችና ስልሳ ሺህ ፈረሰኞች ይዞ ነበር። ከእርሱም ጋር ከግብጽ ለመጣው ሕዝብ ቍጥር አልነበረውም፤ እነርሱም የልብያ ሰዎች ሱካውያን፥ የኢትዮጵያ ሰዎችም ነበሩ።

4 የይሁዳም የነበሩትን የተመሸጉ ከተሞች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ።

5 ነቢዩም ሸማያ ወደ ሮብዓምና ከሺሻቅ ሸሽተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡባት ወደ ይሁዳ መሳፍንት መጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እንናተ ተዋችሁኝ፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ በሺሻቅ እጅ ተውኋችሁ።’ ”

6 የእስራኤልም መሳፍንትና ንጉሡ፦ “ጌታ ጻድቅ ነው” ብለው ራሳቸውን አዋረዱ።

7 ጌታም ራሳቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ የጌታ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሸማያ መጣ፦ “ራሳቸውን አዋርደዋል፤ አላጠፋቸውም፤ ከጥቂት ቀንም በኋላ አድናቸዋለሁ፥ ቁጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይወርድም፤

8 ነገር ግን ለእኔ መገዛትንና ለሌሎች ለምድሪቱ ነገሥታት መገዛትን እንዲያውቁ ለእርሱ ይገዙለታል።”

9 የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ የጌታንም ቤት መዛግብትና የንጉሡን ቤት መዛግብት ወሰደ፤ ሁሉንም ነገር ወሰደ፤ ደግሞም ሰሎሞን የሠራቸውን የወርቁን ጋሻዎች ወሰደ።

10 ንጉሡም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ የናስ ጋሻዎችን ሠራ፥ የንጉሡንም ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቆች እጅ አኖራቸው።

11 ንጉሡም ወደ ጌታ ቤት በገባ ቍጥር ዘበኞች መጥተው ይሸከሙአቸው ነበር፥ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸ ነበር።

12 ራሱንም ባዋረደ ጊዜ የጌታ ቁጣ ፈጽሞ እንዳያጠፋው ከእርሱ ዘንድ ተመለሰ፤ በይሁዳም ደግሞ መልካም ሁኔታ ተፈጠረ።


ንጉሥ ሮብዓም መሞቱ

13 ንጉሡም ሮብዓም በኢየሩሳሌም በረታ ንጉሥም ሆነ፤ ሮብዓምም በነገሠ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ ጌታም ስሙን እንዲያኖርባት ከእስራኤል አገር ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም ዐሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የአሞን ሴት ናዕማ ነበረች።

14 ጌታንም ለመሻት ልቡን አላዘጋጀም ነበርና ክፉ ነገር አደረገ።

15 የሮብዓምም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር በነቢዩ ሸማያና በባለ ራእዩ በአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከልም በዘመናቸው ሁሉ ጦርነት ነበረ።

16 ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አብያ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos