Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ዜና መዋዕል 11 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ይሁዳና ብንያም መመሸጋቸው

1 ሮብዓምም ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ እስራኤልን ወግተው መንግሥቱን ወደ ሮብዓም ለመመለስ ከይሁዳና ከብንያም ቤት የተመረጡትን አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ወታደሮች ሰበሰበ።

2 የጌታም ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሸማያ እንዲህ ሲል መጣ፦

3 “ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም፥ በይሁዳና በብንያምም ላሉት ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ ብለህ ተናገር፦

4 ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ ይህ ነገር ከእኔ ዘንድ ነውና አትውጡ፥ ወንድሞቻችሁንም አትውጉ፤ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ይመለስ።’ ” የጌታንም ቃላት ሰሙ፥ ኢዮርብዓምንም ሄደው ከመውጋት ተመለሱ።

5 ሮብዓምም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፥ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሠራ።

6 እርሱም ቤተ ልሔምን፥ ኤጣምን፥ ቴቁሔን ቆረቆረ፤

7 እንዲሁም ቤት-ጹርን፥ ሦኮን፥ ዓዶላምን፥

8 ጌትን፥ መሪሳን፥ ዚፍን፥

9 አዶራይምን፥ ለኪሶን፥ ዓዜቃን፥

10 ጾርዓን፥ ኤሎንን፥ ኬብሮንን ሠራ፤ እነዚህም የተመሸጉ ከተሞች በይሁዳና በብንያም የሚገኙ ነበሩ።

11 ምሽጎቹንም አጠነከረ፥ አዛዦችንም አኖረባቸው፥ ምግቡንም ዘይቱንም የወይን ጠጁንም አከማቸባቸው።

12 በከተሞቹ ሁሉ ጋሻና ጦርን አኖረ። ከተሞቹንም እጅግ አጠነከራቸው፤ ይሁዳና ብንያምም የእርሱ ወገን ነበሩ።


ካህናትና ሌዋውያን ሮብዓምን መደገፋቸው

13 በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ የነበሩ ካህናትና ሌዋውያን ከየአገራቸው ሁሉ ወደ እርሱ መጡ።

14 የጌታም ካህናት እንዳይሆኑ ኢዮርብዓምና ልጆቹ አስለቅቀዋቸው ነበርና ሌዋውያን መሰማሪያቸውንና ቦታቸውን ትተው ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።

15 እርሱ ግን ለኮረብታው መስገጃዎች ለአጋንንቱም ለሠራቸውም እምቦሶች ካህናትን ሾመ።

16 ደግሞም ለአባቶቻቸው አምላክ ለጌታ ለመሠዋት ከእስራኤል ነገድ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ ጌታን ለመፈለግ ልባቸውን የሰጡ ሁሉ እነርሱን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።

17 ሦስት ዓመት በዳዊትና በሰሎሞን መንገድ ይሄዱ ነበርና ሦስት ዓመት የይሁዳን መንግሥት አበረቱ፥ የሰሎሞንንም ልጅ ሮብዓምን አጸኑ።


የንጉሥ ሮብዓም ጋብቻ

18 ሮብዓምም መሐላትን አገባ፤ አባትዋ የዳዊት ልጅ ኢያሪሙት ነበረ፤ እናትዋም የእሴይ ልጅ የኤልያብ ልጅ አቢካኢል ነበረች።

19 እርሷም የዑስ፥ ሰማራያ፥ ዘሃም የሚባሉትን ወንዶች ልጆች ወለደችለት።

20 ከእርሷም በኋላ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን አገባ፤ እርሷም አብያን፥ ዓታይን፥ ዚዛን፥ ሰሎሚትን ወለደችለት።

21 ሮብዓምም ከሚስቶቹና ከቁባቶቹ ሁሉ ይልቅ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን ወደደ፤ ዐሥራ ስምንትም ሚስቶችና ስልሳ ቁባቶች ነበሩት፥ ሀያ ስምንት ወንዶችና ስልሳ ሴቶች ልጆች ወለደ።

22 ሮብዓምም ንጉሥ ሊያደርገው አስቦአልና የመዓካን ልጅ አብያን በወንድሞቹ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው።

23 ተጠበበም፥ ልጆቹንም ሁሉ በይሁዳና በብንያም አገር ሁሉ በተመሸጉትም ከተሞች ሁሉ ከፋፈላቸው፤ ብዙም ስንቅ ሰጣቸው፤ ብዙም ሚስቶች ፈለገላቸው።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos