Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ዜና መዋዕል 10 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ሮብዓም ላይ ዐመፅ መነሣቱ

1 እስራኤልም ሁሉ ሊያነግሡት ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ።

2 የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ሸሽቶ በግብጽ ይኖር ነበርና ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮርብዓም ከግብጽ ተመለሰ።

3 ልከውም ጠሩት፤ ኢዮርብዓምና እስራኤልም ሁሉ መጥተው ሮብዓምን እንዲህ አሉት፦

4 “አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ ስለዚህ አሁን አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቅልልልን፥ እኛም እናገለግልሃለን።”

5 እርሱም፦ “ከሦስት ቀን በኋላ ወደ እኔ ተመለሱ” አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ።

6 ንጉሡም ሮብዓም፦ “ለዚህ ሕዝብ እንድመልስለት የምትመክሩኝ ነገር ምንድነው?” ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወት ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ።

7 እነርሱም እንዲህ ብለው ተናገሩት፦ “ለዚህ ሕዝብ ቸርነት ብታደርግላቸው፥ ደስም ብታሰኛቸው፥ በገርነትም ብትናገራቸው፥ ለዘለዓለም ባርያዎች ይሆኑልሃል።”

8 እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ነገር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ።

9 እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ ‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልን’ ለሚሉኝ ሕዝብ እንድመልስላቸው የምትመክሩኝ ምንድነው?”

10 ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች እንዲህ በላቸው ብለው ተናገሩት፦ “ ‘አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፥ አንተ ግን አቅልልልን’ ለሚሉህ ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ ‘ታናሽቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፤

11 አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ።’ ”

12 ንጉሡም፦ “በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ” ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓብ መጡ።

13 ንጉሡም ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው፤ ንጉሡም ሮብዓም የሽማግሌዎቹን ምክር ትቶ፦

14 “አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን እጨምርበታለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ” ብሎ እንደ ብላቴኖቹ ምክር ተናገራቸው።

15 ጌታም በሴሎናዊው በአሒያ አድርጎ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ቃል እንዲያጸና ከጌታ ዘንድ ተወስኖ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።

16 እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ እንዳልሰማቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱለት፦ “በዳዊት ዘንድ ምን ድርሻ አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም፤ እስራኤል ሆይ! ወደ እየድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ! አሁን ቤትህን ተመልከት።” እስራኤልም ሁሉ ወደ እየድንኳኖቻቸው ሄዱ።

17 በይሁዳ ከተሞች በተቀመጡት በእስራኤል ልጆች ላይ ግን ሮብዓም ነገሠባቸው።

18 ንጉሡም ሮብዓም አስገባሪውን አዶራምን ላከ፤ የእስራኤልም ልጆች በድንጋይ ወገሩት፥ ሞተም፤ ንጉሡም ሮብዓም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ወጣ ወደ ኢየሩሳሌምም ሸሸ።

19 እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከዳዊት ቤት ላይ ዓመፀ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos