Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ተሰሎንቄ 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ስለዚህ ወደ ፊት ለመታገስ ባልተቻለን ጊዜ፥ በአቴና ብቻችንን ልንቀር በጎ ፈቃዳችን ሆነ።

2 ስለ እምነታችሁም እንዲያጸናችሁና እንዲመክራችሁ ወንድማችንን፥ የእግዚአብሔርንም አገልጋይ ከእኛ ጋርም አብሮ በክርስቶስ ወንጌል የሚሠራውን ጢሞቴዎስን ላክነው፤

3 በዚህ መከራ ማንም እንዳይናወጥ፥ ለዚህ እንደ ተሾምን ራሳችሁ ታውቃላችሁና።

4 በእውነት ከእናንተ ጋር ሳለን፥ መከራ እንደምንቀበል አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ እንዲሁም ደግሞ ሆነ፤ ይህንንም ታውቃላችሁ።

5 ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት ለመታገስ ባልተቻለኝ ጊዜ፦ “ፈታኙ ምናልባት ፈትኖአቸዋል፤ ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል፤” ብዬ በመፍራት እምነታችሁን ለማወቅ ጢሞቴዎስን ላክሁ።


የጢሞቴዎስ የምሥራች ዜና

6 አሁን ግን ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ ወደ እኛ መጥቶ ስለ እምነታችሁና ስለ ፍቅራችሁ መልካም ዜና አመጣልን፤ እኛ እናንተን ለማየት እንደምንናፍቅ እናንተም እኛን ለማየት እንደምትናፍቁና ሁልጊዜ በመልካም እንደምታስታውሱን ደግሞ ነገረን፤

7 ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! በእምነታችሁ በኩል በችግራችንና በመከራችን ሁሉ ስለ እናንተ ተጽናናን፤

8 እናንተ በጌታ ጸንታችሁ ብትቆሙ፥ አሁን በሕይወት እንኖራለንና።

9 በእናንተ የተነሣ በአምላካችን ፊት ለተደሰትነው ደስታ ሁሉ ስለ እናንተ ለእግዚአብሔር ምን ያህል ምስጋና ልናቀርብ እንችላለን?

10 ፊታችሁን ለማየትና በእምነታችሁ የጎደለውንም ለማሟላት ሌሊትና ቀን እጅግ አብዝተን እንጸልይ የለምን?

11 አምላካችንና አባታችን ራሱ ጌታችንም ኢየሱስ ወደ እናንተ መንገዳችንን ይምራ፤

12 ጌታ እንድትበዙ ያድርጋችሁ፤ እኛም ለእናንተ ፍቅርን እንዳበዛንላችሁ እንዲሁም የእርስ በርሳችሁንና ለሁሉ ሰው ያላችሁን ፍቅር ያብዛ።

13 ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ጌታችን ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ በአባታችንና በአምላካችን ፊት ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ በቅድስና ልባችሁን ያጽና።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos