1 ተሰሎንቄ 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የጳውሎስ አገልግሎት በተሰሎንቄ 1 ወንድሞች ሆይ! እናንተን መጎብኘታችን በከንቱ አልነበረም፥ እናንተም ራሳችሁ ታውቁታላችሁ። 2 ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራንና እንግልትን ብንቀበልም እንኳ፥ በታላቅም ተቃውሞ ፊት የእግዚአብሔርን የምሥራች ቃል ለእናንተ ለመናገር በአምላካችን ድፍረትን አገኘን። 3 ምክራችን ከስሕተት ወይም ከርኩሰት ከተንኰልም የመነጨ አልነበረምና፤ 4 ነገር ግን ወንጌል በአደራ እንዲሰጠን እግዚአብሔር የታመንን እንዳደረገን፥ እንዲሁ ሰውን ደስ ለማሰኘት ሳይሆን ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ብለን እንናገራለን። 5 እንደምታውቁት፥ የቁልምጫን ቃል ለስግብግብነትም ማመካኛ የሚሆን ነገር ከቶ አልተገኘብንም፥ እግዚአብሔርም ምስክር ነው። 6 እንዲሁም ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ክብርን አልፈለግንም፥ 7 ዳሩ ግን የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን መጠን ልንጫናችሁ በቻልን ነበር፤ ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትንከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ 8 ስለዚህም እናንተን በፍቅር በመሻት የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ ለማካፈል በጎ ፈቃዳችን ነበረ፤ ምክንያቱም ለእኛ እጅግ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ስለ ነበር ነው። 9 ወንድሞች ሆይ! ድካማችንንና ጥረታችንን ታስታውሱታላችሁ፤ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እየሰበክን በአንዳችሁም ላይ እንኳ ሸክም ላለመሆን ስንል ሌሊትና ቀን እንሠራ ነበር። 10 በእናንተ በአማኞች መካከል እንዴት ባለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ነበርን እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ፤ 11 አባት ለልጁ እንደሚሆነው እኛም እንዴት ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን እናንተው ታውቁታላችሁ፥ 12 በመሆኑም ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ እንድትመላለሱ እየመከርናችሁ፥ እያጸናናችሁና እየመሰከርንላችሁ ነበር። 13 ስለዚህም የመልእክትን ቃል፥ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በአማኞች ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን። 14 እናንተ ወንድሞች ሆይ! በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከወገኖቻችሁ ተቀብላችኋልና። 15 እነዚያም ጌታን ኢየሱስንና ነቢያትን ገደሉ፤ እኛንም ደግሞ አሳደዱ፤ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፤ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፤ 16 ለአሕዛብ እንዳንናገር በመከልከል እነርሱ እንዳይድኑ ያደርጋሉ፤ በዚህም ያለማቋረጥ የኃጢአታቸውን መስፈርያ ይሞላሉ፤ ነገር ግን በመጨረሻ የእግዚአብሔር ቁጣው ይመጣባቸዋል። ጳውሎስ የተሰሎንቄን ቤተ ክርስቲያን እንደገና ለመጎብኘት የነበረው ምኞት 17 እኛ ግን ወንድሞች ሆይ! በልብ ሳይሆን በአካል ለጥቂት ጊዜ ብናጣችሁም፥ በብዙ ናፍቆት ግን ፊታችሁን ለማየት እጅግ ጓጓን፤ 18 ወደ እናንተ ልንመጣ ፈልገን ነበርና፤ በእርግጥም እኔ ጳውሎስ አንድና ሁለት ጊዜ ሞክሬ ነበር፥ ሰይጣን ግን መሰናክል ሆነብን። 19 ጌታችን ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ በፊቱ የተስፋችን ወይም የደስታችን ወይም የመመክያችን አክሊል ምንድነው? እናንተ አይደላችሁምን? 20 እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና። |