Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ሳሙኤል 30 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ዳዊት አማሌቃውያንን አጠፋ

1 በሦስተኛው ቀን ዳዊትና ሰዎቹ ጺቅላግ ደረሱ፤ በዚህ ጊዜ አማሌቃውያን ደቡቡን አገርና ጺቅላግን ወረው ነበር፤ ጺቅላግንም ወግተው አቃጥለው ነበር።

2 ሴቶቹን፥ በዚያ የነበሩትን ወጣቶችና ሽማግሌዎቹን ሁሉ ማርከው ወሰዱ፤ የማረኩትንም ይዘው ከመሄድ በስተቀር አንዱንም አልገደሉም ነበር።

3 ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ጺቅላግ እንደ ደረሱም፥ እነሆ፤ ከተማዪቱ በእሳት ጋይታ፥ ሚስቶቻቸው፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ተማርከው አገኙ።

4 በዚህ ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ማልቀስ እስከሚያቅታቸው ድረስ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤

5 ሁለቱ የዳዊት ሚስቶች ማለትም ኢይዝራኤላዊቷ አሒኖዓምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢጌልም ተማርከው ነበር።

6 ሰዎቹ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ነፍሳቸው ተማርራ ሊወግሩት ስለ ተመካከሩ ዳዊት በጣም ተጨነቀ፤ ነገር ግን ዳዊት በአምላኩ በጌታ በረታ።

7 ከዚያም ዳዊት የአቤሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን፥ “ኤፉዱን አምጣልኝ” አለው፤ አብያታርም አመጣለት፤

8 ዳዊትም፥ “ይህን ወራሪ ሠራዊት ልከተለውን? እደርስባቸዋለሁን?” ሲል ጌታን ጠየቀ። ጌታም፥ “በእርግጥ ትደርስባቸዋለህ፤ ምርኮውንም ትመልሳለህ፤ ተከተላቸው!” ሲል መለሰለት።

9 ስለዚህ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ስድስት መቶ ሰዎች ብሦር ተብሎ ከሚጠራው ወንዝ ሲደርሱ፤ ጥቂቶቹ በብሦር ወንዝ ቆዩ።

10 ሁለት መቶዎቹ እጅግ ዝለው ስለ ነበር ወንዙን መሻገር አልቻሉም። ነገር ግን ዳዊትና አራት መቶ ሰዎች መከታተላቸውን ቀጠሉ።

11 እነርሱም በምድረ በዳ አንድ ግብፃዊ አገኙ፤ ወደ ዳዊትም አመጡት። የሚጠጣውን ውሃና የሚበላውን ምግብ ሰጡት።

12 እንደዚሁም የበለስ ጥፍጥፍ ቁራሽና ሁለት ደረቅ የወይን ዘለላዎች ሰጡት። ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ምንም እህል ስላልበላ፥ ውሃም ስላልጠጣ ይህን ከበላ በኋላ ነፍሱ ተመለሰች።

13 ዳዊትም፥ “አንተ የማን ነህ? የመጣኸውስ ከየት ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “እኔ ግብፃዊ ስሆን፥ የአንድ አማሌቃዊ አገልጋይ ነኝ፤ ከሦስት ቀን በፊት ታምሜ በነበረበት ጊዜ ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ።

14 የከሪታውያንን ደቡብ፥ የይሁዳን ግዛትና የካሌብን ደቡብ ወረርን፤ ጺቅላግንም በእሳት አጋየናት።”

15 ዳዊትም፥ “ታዲያ ወራሪው ሠራዊት ወዳለበት መርተህ ትወስደኛለህን?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፥ “እንደማትገድለኝ ወይም ለጌታዬ አሳልፈህ እንደማትሰጠኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ እንጂ እነዚህ ወራሪዎች ወዳሉበት አደርስሃለሁ” አለው።

16 ዳዊትን ወደ ታች መርቶ ባደረሰው ጊዜም፥ እነሆ ወራሪዎቹ ከፍልስጥኤማውያንና ከይሁዳ ምድር ከወሰዱት ታላቅ ምርኮ የተነሣ በየቦታው ተበታትነው ይበሉ፥ ይጠጡና ይዘፍኑ፥ ይጨፍሩም ነበር።

17 ዳዊት፥ ከዚያች እለት ምሽት ጀምሮ እስከ ማግሥቱ ምሽት ድረስ ወጋቸው፤ በግመል ተቀምጠው ከሸሹት አራት መቶ ወጣቶች በስተቀር፥ ከመካከላቸው ያመለጠ አንድም አልነበረም።

18 ዳዊት አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣለ፥ ሁለቱንም ሚስቶቹን አስመለሰ።

19 ትንሽም ሆነ ትልቅ፥ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆች፥ ምርኮም ሆነ ሌላ፥ አማሌቃውያን ከወሰዱት ነገር ምንም የጐደለ አልነበረም። ዳዊት ሁሉንም አስመለሰ።

20 እንዲሁም ዳዊት የበጉን፥ የፍየሉንና የላሙን መንጋ ሁሉ ወሰደ፤ ሰዎቹም “ይህ የዳዊት ምርኮ ነው” እያሉ መንጋውን ከሌሎች ከብቶች ፊት ለፊት ይነዱ ነበር።

21 ከዚያም ዳዊት እጅግ በመድከማቸው ምክንያት ሊከተሉት ወዳልቻሉት በብሦር ወንዝ ቀርተው ወደነበሩት ወደ ሁለቱ መቶ ሰዎች መጣ፤ እነርሱም ዳዊትንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች ለመቀበል ወጡ። ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እነርሱ እንደ ቀረቡም ዳዊት ሰላምታ ሰጣቸው።

22 ከዳዊት ተከታዮች ክፉዎቹና ምግባረ ቢሶቹ ግን፥ “አብረውን ስላልዘመቱ ካመጣነው ምርኮ አናካፍላቸውም፤ እያንዳንዱ ሚስቱንና ልጆቹን ብቻ ይዞ መሄድ ይችላል” አሉ።

23 ዳዊትም እንዲህ አለ፦ “ወንድሞቼ ሆይ፤ የጠበቀን፥ የመጣብንንም ወራሪ በእጃችን የጣለልን ጌታ ነው፤ እርሱ በሰጠን ነገር አስተውሉ፤ ይህን ማድረግ አይገባችሁም።

24 የምትሉትን ማን ይቀበላችኋል? ከጓዝ ጋር የቀረው ሰው ድርሻ ለጦርነት ከወጣው ሰው ድርሻ ጋር አይበላለጥም፤ ሁሉም እኩል ይካፈላሉ።”

25 ዳዊትም ከዚያ ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይህን ለእስራኤል እንደ ሕግና ሥርዓት አደረገው።

26 ዳዊት ወደ ጺቅላግ በመጣ ጊዜ፥ ወዳጆቹ ለሆኑት ለይሁዳ ሽማግሌዎች፥ “ከጌታ ጠላቶች የተማረከ ስጦታ እነሆ ይሄው፤” በማለት ከምርኮው ላይ ከፍሎ ላከላቸው።

27 ይህንም፥ በቤትኤል፥ በደቡብ ራሞትና በያቲር ለነበሩ ላከላቸው።

28 በአሮዔር፥ በሲፍሞት፥ በኤሽተሞዓና፥

29 በራካል ለሚገኙ፥ እንዲሁም ለይራሕመኤል ከተሞች፥ ለቄናውያን ከተሞችም፥

30 በሖርማ፥ በቦርዓሻን፥ በዐታክና፥

31 በኬብሮን ለነበሩ፥ ዳዊትና ሰዎቹም በተመላለሱበት ስፍራ ለነበሩ ሁሉ ላከላቸው።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos