1 ሳሙኤል 21 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ዳዊት ወደ ኖብ ሄደ 1 ዳዊትም ካህኑ አቢሜሌክ ወዳለበት ወደ ኖብ ሄደ። አቢሜሌክም እየተንቀጠቀጠ ዳዊትን ሊገናኘው መጣና፥ “ምነው ብቻህን? ሰውስ ለምን አብሮህ የለም?” ሲል ጠየቀው። 2 ዳዊት፥ ካህኑን አቢሜሌክን እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ፥ ‘ስለ ላክሁህ ነገርና ስለ ሰጠሁህ መመሪያ ማንም ሰው ምንም ነገር አይወቅ’ ብሎ አዞኛል። ሰዎቼንም የት እንደምንገናኝ ነግሬያቸዋለሁ። 3 ታዲያ አሁን በእጅህ ምን አለ? አምስት እንጀራ ወይም የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ስጠኝ።” 4 ካህኑም፥ “ሰው ሁሉ የሚበላው እንጀራ የለኝም፤ ነገር ግን ሰዎቹ በቅርቡ ከሴት የተጠበቁ ከሆነ፥ የተቀደሰ እንጀራ በዚህ አለ” አለው። 5 ዳዊትም “እንደተለመደው ሁሉ ከወጣሁ ጊዜ ጀምሮ ሴቶች ከእኛ ተጠብቀዋል፤ በተራ ተልእኮ ውስጥ እንኳ የሰዎቹ ዕቃዎች የተቀደሱ ናቸው፤ ዛሬማ ምንኛ የበለጠ ቅዱሳን መሆን ይገባቸዋል?” ሲል መለሰ። 6 ስለዚህ ካህኑ የተቀደሰውን እንጀራ ለዳዊት ሰጠው፤ ከጌታ ፊት ተነሥቶ በትኩስ እንጀራ ከተተካው ከኅብስት በስተቀር በዚያ ሌላ እንጀራ አልነበረምና። 7 በዚያችም ዕለት ከሳኦል አገልጋዮች አንዱና የእረኞቹ አለቃ የሆነው ኤዶማዊው ዶይቅ እዚያው በጌታ ፊት እንዲቆይ ተገዶ ነበር። 8 ዳዊት አቢሜሌክን፥ “የንጉሡ ጉዳይ ስላስቸኮለኝ፥ ሰይፌንም ሆነ ሌላ የጦር መሣሪያ አላመጣሁም፤ እዚህ ካንተ ዘንድ ጦር ወይም ሰይፍ አይገኝምን?” ሲል ጠየቀው። 9 ካህኑም፥ “በኤላ ሸለቆ አንተ የገደልኸው የፍልስጥኤማዊው የጎልያድ ሰይፍ እዚህ አለ፤ ከኤፉዱ በስተ ኋላ በጨርቅ ተጠቅልሏል፥ እነሆ፥ ከፈለግህ ውሰደው፤ ከእርሱ በስተቀር ሌላ ሰይፍ እዚህ የለም” ብሎ መለሰለት። ዳዊትም “እንደ እርሱ ያለ የለምና እርሱኑ ስጠኝ” አለው። 10 በዚያች ዕለት ዳዊት ከሳኦል ሸሽቶ ወደ ጋት ንጉሥ ወደ አኪሽ ሄደ። 11 የአኪሽ አገልጋዮችም፥ “የምድሪቱ ንጉሥ ዳዊት ይህ አይደለምን? ደግሞስ ‘ሳኦል ሺህ ገደለ፤ ዳዊት ዐሥር ሺህ ገደለ’ ብለው በጭፈራቸው የዘፈኑለትስ እርሱ አይደለምን?” አሉት። 12 ዳዊት ነገሩን በልቡ አኖረ፤ የጋትን ንጉሥ አኪሽንም እጅግ ፈራው። 13 ስለዚህ በፊታቸው አእምሮውን እንደሳተ ሰው ሆነ፤ በያዙትም ጊዜ የከተማዪቱን ቅጥሮች እየቦጫጨረ፥ ለሐጩንም በጢሙ ላይ እያዝረከረከ እንደ እብድ ሆነ። 14 አኪሽም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ “ሰውየውን እስቲ ተመልከቱት፤ እብድ እኮ ነው! ታዲያ ወደ እኔ ያመጣችሁት ለምንድን ነው? 15 በፊቴ እንዲህ ይሆን ዘንድ ይህን ሰው እዚህ ያመጣችሁት እብድ አጥቼ ነውን? እንዲህ ያለውስ ሰው ወደ ቤቴ መግባት ይገባዋልን?” |