Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የማታትያስ ቅዱስ ጦርነት መጀመር ማታትያስና ልጆቹ

1 በእነዚያ ዘመን ከዮሃሪብ ልጆች መካከል ካህን የሆነ፥ የዮሐንስ ልጅ የሆነ፥ የስምዖን የልጅ ልጅ ማታያስ ተነሣ፤ ኢየሩሳሌምን ትቶ በመዲን ተቀመጠ።

2 አምስት ልጆችም ነበሩት፤ እነሱም ጋዲ የተባለ ዮሐንስ፤

3 ባሕሲ የተባለ ስምዖን፥

4 መቃቢስ የተባለ ይሁዳ፤

5 አዋራን የተባለ ኤልዓዛር፥ አጶሁስ የተባለ ዮናታን ናቸው።

6 በይሁዳ አገርና በኢየሩሳሌም የተደረገውን ርኩሰት አየ፤

7 እንዲህም አለ፥ “ወዮልኝ፥ እኔ የተወለድሁት የሕዝቤን መጥፋትና የቅድስቲቱን ከተማ መደምሰስ ለማየት ነውን? ከተማይቱ በጠላት እጅ ስትወድቅና ቤተ መቅደሷም ለባዕድ ሰዎች ተላልፎ ሲሰጥ ቁጭ ብሎ ልቀር ነውን?

8 ቤተ መቅደሱ ክብር እንደሌለው ሰው ሆኗል፤

9 ክብሩን የሚያንጸባርቁ ዕቃዎች ተማርከው ሄደዋል፤ ሕፃናቱ በየመንገዱ ታርደዋል፤ ወጣቶቹም በጠላት ሰይፍ ወድቀዋል።

10 (የከተማችንን) የመንግሥትነት መብቷን ያልወረሰባት ምን አገር አለ? ምርኮዎችዋን ያልወሰደ ማን አለ?

11 ጌጧ ተወስዶባታል፤ የቀድሞ ነጻነትዋ በባርነት ተቀይሯል።

12 እነሆ የተቀደሰው ቦታ፥ ተቀይሯል። ውበታችን መና ሆኗል፤ አሕዛብ አርክሰውታል።

13 ለመሆኑ የምንኖረው ለምኑ ነው?”

14 ማታትያስና ልጆቹ በኀዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ የተለተለ ልብሳቸውን የተለተለ ለብሰው ታላቅ ኀዘን አደረጉ።

15 ለማስካድ የታዘዙ የንጉሡ መልእክተኞች መሥዋዕት ፍለጋ ወደ ሞደን መጡ።

16 ብዙ እስራኤላውያን ወደ እነርሱ ሄዱ፤ ማታትያስና ልጆቹ ግን ብቻቸውን ተለይተው ቀሩ።

17 የንጉሡ መልእክተኞች ማታትያስን እንዲህ አሉት፥ “አንተ በዚች ከተማ ክቡርና ታላቅ ሹም ነህ፤ በልጆችህና በወንድሞችህ የተደገፍህ ነህ።

18 በል እንግዲህ ሕዝቦች ሁሉና በኢየሩሳሌም የቀሩ ሰዎች እንዳደረጉት አንተ በመጀመሪያ ቅደምና በንጉሡ የተወሰነውን ነገር ፈጽም፤ አንተና ልጆችህ ቁጥራችሁ ከንጉሡ ወዳጆች ጋር ይሆናል፤ ብርና ወርቅ ይሰጣችሁና ብዙ ስጦታዎችም ይደረግላችሁና ትከብራላችሁ”።

19 ማታትያስ በብርቱ ቃል እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፤ “በንጉሡ መንግሥት ውስጥ ያሉት ሕዝቦች ሁሉ ከየአባቶቻቸው አምልኮ ርቀውና ትእዛዙንም እሺ ብለው ቢቀበሉትም

20 እኔና ልጆቼ፥ ወንድሞቼም የምንከተለው የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን ነው።

21 ሕጉንና ትእዛዞቹን እንዳንተው ጸጋውን ይስጠን።

22 ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ በማለት ከአምልኮአችን ርቀን የንጉሡን ትእዛዞች አንቀበልም”።

23 ማታትያስ ንግግሩን ባቆመ ጊዜ አንድ አየሁዳዊ ሰው በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት በሞዲን መሠዊያ ላይ በሰዎች ሁሉ ፊት ለመሠዋት ወደ ፊት ሄደ።

24 ማታትያስ ይህን ባየ ጊዜ በእግዚአብሔር ፍቅር ተቃጠለ፤ ሰውነቱም በቁጣ ተንቀጠቀጠ፥ በጣም ተቆጣ፥ ሮጦም ሰውዬውን በመሠዊያው ላይ አረደው፤

25 ሰዎቹ እንዲሰዉ ያስገድድ የነበረውን የንጉሡን ባለሟል ወዲያው ገደለውና መሠዊያውንም ገልብጦ ጣለው።

26 በሳሉ ልጅ በዚምሪ ላይ ፊንሃስ እንዳደረገው ሁሉ ማታትያስ በሙሴ ሕግ ፍቅር በመቃጠል እንዲሁ አደረገ።

27 ከዚህ በኋላ ማታትያስ በከተማው መካከል ሲያልፍ ድምፁን ከፍ አድርጐ፥ “የሙሴን ሕግ የሚያፈቅሩ ሰዎች ሁሉ፥ ቃል ኪዳኑንም የሚደግፉ ሁሉ ይከተሉኝ” እያለ ጮኸ።

28 እርሱና ልጆቹ በከተማ ያላቸውን ሁሉ ትተው ወደ ተራራ ሸሹ።


የሰንበት ቀን መከራ በበረሃ

29 ፍትሕንና ትክክለኛነትን ይፈልጉ የነበሩ ብዙ ሰዎች በበረሃ ለመኖር ወደ በረሃማው አገር ወረዱ፤

30 እነርሱ፥ ልጆቻቸውና ሚስቶቻቸው መከራ ስለ በዛባቸው ሁሉም ወደ በረሃ ሄዱ።

31 በዳዊት ከተማም፥ ኢየሩሳሌም ለነበሩ ለንጉሡ ባለሥልጣኖችና ወታደሮች የንጉሡን ትእዛዝ አንቀበልም ያሉ በበረሃ ወደሚገኝ ያልታወቀ ስፍራ እንደ ሸሹ ተነገራቸው።

32 ብዙ ወታደሮች ተከታተሏቸውና ደረሱባቸው፤ የጦር ሰፈራቸውንም በእነርሱ ፊት ለፊት አደረጉ፤ በሰንበት ቀን ከእነርሱ ጋር ውጊያ ለመግጠምም ተዘጋጁ፤

33 “አሁን እንግዲህ በቃ፤ ውጡና የንጉሡን ትእዛዝ ፈጽሙ፤ ሕይወታችሁም ይድናል” አሏቸው።

34 እነርሱ ግን፥ “አንወጣም፥ ሰንበትን አፍርሰን ንጉሡ ያዘዘውን አንቀበልም” ብለው መለሱ።

35 ወታደሮቹ ወዲያውኑ ውጊያ ገጠሙዋቸው፤

36 እነዚያ ምንም አልመለሱለቸውም፤ ድንጋይም አልወረወሩባቸውም፤ መደበቂያቸውንም አልዘጉባቸውም።

37 “ሕሊናችን ንጹሕ ሆኖ እንሙት፤ ያለ አግባብ እንደምትገድሉን ሰማይና ምድር ይታዘባሉ” ይሉ ነበር።

38 እነዚህ ሰዎች በሰንበት ቀን ጦርነት ገጠሙዋቸው፤ ከነሚስቶቻቸው፥ ከነልጆቻቸው፥ ከነአባቶቻቸው አንድ ሺህ የሚያህሉቱ በዚህ ቀን አለቁ።

39 ማታትያስና ጓደኞቹም ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ።

40 እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፦ “ሁላችንም እንደ ወንድሞቻችን አይሁዶች ብንሆን ኖሮ ሕይወታችንንና ሃይማኖታችንን ለመጠበቅ ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን ስንዋጋ እንኑር ብንል፥ ከምድር ገጽ ፈጽመው ያጠፉናል።”

41 በዚያም ቀን በሰንበት ቀን አንድ ሰው ቢገድልባቸው፥ እነርሱም ራሳቸውን መከላከል እንዳለባቸውና ከዋሻቸው ውስጥ እንዳሉ ዐይኖቻቸው እያየ እንደሞቱ ወገኖቻቸው እንዳይጠፉ ወሰኑ።

42 በዚያን ጊዜ የእስራኤል ጀግኖች እና ተዋጊዎች ከሕጉ ጎን ለመቆም ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች በአሲዳውያን እየተመሩ ተቀላቀሉዋቸው።

43 ከእነዚህ ከሚደርስባቸው ክትትል ለመሸሽ የመረጡት ሁሉ ከጐናቸው በመሰለፋቸው ኃይላቸው እየተጠናከረ ሄደ።

44 ራሳቸውን በሠራዊት መልክ አደራጅተው ኃጢአተኞችንና ክፉዎቹን (ከሐዲዎቹን) በቁጣቸው መቷቸው፤ የቀሩት ወደ አረማውያን ሕዝብ ሸሽተው አመለጡ።

45 ማታትያስና ጓደኞቹ እየዞሩ የአረማውያንን መሠዊዎች አፈራረሱ።

46 በእስራኤል አገር የሚገኙትን ያልተገረዙ ልጆችንም በግድ ገረዙዋቸው፤

47 ትዕቢተኞቹንም በታተኑዋቸው፥ ሥራቸውም ተቃናላቸው።

48 ከአረማውያንና ከነገሥታት እጅ የሙሴን ሕግ ነጥቀው ወሰዱ፤ የኃጢአተኛቹንም ወኔ ሰለቡ።


የማታትያስ ምስክርነት እና ሞት

49 የማታትያስ ቀኖች ወደ ፍጻሜአቸው እየተቃረቡ ሄዱ፤ ለልጆቹ እንዲህ አላቸው፥ “እነሆ አሁን ትዕቢትና በደል ወደ ላይ ከፍ ከፍ እያሉ ነው፤ ዘመኑም የብጥብጥና ጥላቻ ዘመን ነው፤

50 ልጆቼ ሆይ የሙሴ ሕግ ፍቅር ይኑራችሁ፤ የአባቶቻችሁን ቃል ኪዳን ለመፈጸም ሕይወታችሁን አሳልፋችሁ የምትሰጡበት ወቅት አሁን ነው።

51 አባቶቻችን በጊዜአቸው የፈጸሟቸውን ሥራዎች አስታውሰ፤ ታላቅ ክብርና ዘላለማዊ ዝና ታገኛላችሁ፤

52 አብርሃም በፈተናው ጊዜ ታማኝ ሆኖ ስለ ተገኘ እንደ ጽድቅ ሆኖ አልተቆጠረለትምን?

53 ዮሴፍ በመከራው ጊዜ ሕግን ጠብቆ የግብጽ አገር ጌታ ሆነ።

54 አባታችን ፊንሃስ በተቃጠለ ፍቅሩ የዘላለማዊ ክህነት ቃል ኪዳንን ተቀበለ።

55 ኢያሱ ግዳጁን በመፈጸሙ በእስራኤል ዳኛ ሆነ።

56 ካሌብ ለእስራኤል ሕዝብ በሰጠው እውነተኛ ምስክርነቱ እርስት አገኘ።

57 ዳዊት በመንፈሳዊነቱ ለዘለዓለም ንጉሣዊ ዜማን ወረሰ።

58 ኤልያስ ስለ ሙሴ ሕግ በፍቅር በመቃጠሉ፤ ወደ ሰማይ ተወሰደ።

59 አናንያ፥ አዛርያ፥ ሚሳኤል በእግዚአብሔር ስለተማመኑ፤ ከእሳት ነበልባል አመለጡ።

60 ዳንኤል በቅንነቱ ከአንበሶች አፍ ዳነ።

61 በእርሱ በእግዚአብሔር ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ ከትውልድ እስከ ትውልድ ድክመት እንደማያገኛቸው ዕወቁ።

62 የኃጢአተኛን ሰው ዛቻ አትፍሩ፤ ምክንያቱ የእርሱ ክብር የሚሄደው ወደ መበስበስና ወደ ትል ነው።

63 ዛሬ ክብርን ያገኛል፥ ነገ ግን አይገኝም፤ ምክንያቱም ወደ መጣበት ትቢያ ይመለሳል፤ ዕቅዱም እንዳልነበር ይሆናል።

64 ልጆቼ ሆይ፥ የሙሴን ሕግ ጠንክራችሁ ያዙ፤ ምክንያቱም ትልቅ ክብር የሚያስገኝላችሁ እርሱ ነው።

65 ወንድማችሁ ስምዖን መልካም ምክር ሊለግሳችሁ እንደሚችል አውቃለሁ፤ ሁልጊዜ ስሙት፥ አባት ይሆናችኋል።

66 ገና በወጣትነቱ ጀግና የሆነው ይሁዳ መቃቢስ የጦር ሠራዊታችሁ መሪ ይሆናል፤ በአሕዛቦች ላይ በምታደርጉት ጦርነት ይመራችኋል።

67 እናንተ ግን የሙሴን ሕግ የሚጠብቁትን ሁሉ ወደ እናንተ ሰብስቧቸው፤ የሕዝባችሁን በደል ተበቀሉ።

68 አረማውያን ያደረጉባችሁን ክፉ ነገር መልሳችሁ አድርጉባቸው፤ የሙሴ ሕግ የሚያዘውን በጥብቅ ፈጽሙ”።

69 ከዚህ በኋላ ባረካቸውና ሞተ።

70 በመቶ አርባ ስድስት ዓመተ ዓለም ሞተ፤ በሞዲን በቤተሰብ መቃብ ተቀበረ፤ መላው እስራኤል በጥልቅ አዘነለት።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos