Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa 1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)አንደኛ መቃብያን መግቢያ ታላቁ እስክንድር እና ተከታዮቹ 1 የመቄዶንያዊው የፊሊጶስ ልጅ እስክንድር ኪትማውያን አገር (መቄዶንያ) ወጥቶ የፋርስና የሜዶን ንጉሥ የሆነው ዳርዮስን አሸንፎ በቦታው ለመጀመሪያ ጊዜ የግሪካውያን ንጉሥ ከሆነ በኋላ፤ 2 ብዙ ጦርነቶችን አደረገ፤ ብዙ ምሽጐችን ያዘ፤ የሀገሪቱን ነገሥታት ገደለ። 3 እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ሄደ፤ የብዙ ሕዝቦችን ምርኮ ወሰደ። ምድር በፊቱ ዝም አለች፤ ልቡ ከፍ ከፍ አለና በትዕቢት ተነፋ። 4 እጅግ ብርቱ ጦር ሠራዊት አዘጋጀ፤ ለእርሱ ግብር መክፈል የሚገባቸውን አገሮች ገባሮቹ እንዲሆኑ አደረገ። 5 ከዚህ በኋላ ታመመ፤ ሊሞት መሆኑንም ተገነዘበ። 6 ታላላቅ የጦር መኰንኖችንና ከልጅነት ጀምሮ ከእርሱ ጋር ጦርነት ያደረጉትን ሰዎች ከመሞቱ በፊት መንግሥቱን አከፋፈላቸው። 7 እስክንድር የሞተው ዐሥራ ሁለት ዓመት ከነገሠ በኋላ ነው። 8 ታላላቅ የጦር መኰንኖቹ በየግዛታቸው ሥልጣን ያዙ፤ 9 እርሱ ከሞተ በኋላ ሁሉም ዘውድ ደፉ፤ ልጆቻቸውም ከእነርሱ በኋላ ለብዙ ዓመታት እንዲሁ አደረጉ፤ በምድር ላይ ብዙ ክፋትን ሠሩ። አንጥዮኩስ ኤጲፋንዮስ፥ እስራኤል በግሪካዊ ሥርዓት ተፅዕኖ ሥር 10 ከእነርሱም አንድ ክፉ ዘር ወጣ፤ አንጥዮኩስ አጲፋንዮስ ይባላል፤ የንጉሥ አንጥዮኩስ ልጅ ነው። እርሱ በሮም አስረኛ ሆኖ ከተቀመጠ በኋላ በግሪካውያን መንግሥት ጊዜ በአንድ መቶ ሰባ ሰባተኛ ዓመት ላይ ንጉሥ ሆነ። 11 በዚያን ጊዜ ከእስራኤል ውስጥ ሕግ አፈራሾች ወጡና ብዙ ሰዎችን አሳሳቱ፥ “ኑ እንሂድና በዙሪያችን ካሉት አሕዛብ ጋር እንስማማ፤ ምክንያቱም ብዙ ክፉ ነገሮች የመጣብን ከእነርሱ በመለየታችን ነው” አሉ። 12 ይህ ሐሳብ ደስ ብሎአቸው 13 ከሕዝቡ መካከል ብዙዎች በፍጥነት ወደ ንጉሡ ሄዱ፤ እርሱም የአረማውያን ሕዝቦች የሚያደርጉትን እንዲያደርጉ ሥልጣን ሰጣቸው። 14 ስለዚህ እንደ አረማውያን ሕዝቦች ልማድ በኢየሩሳሌም አንድ የእስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ሠሩ። 15 ግዛታቸውን ደበቁ፤ ከአረማውያን ጋር ለመስማማት ቅዱሱን ቃል ኪዳን ካዱ፤ ክፉ ነገርን ለማድረግ ራሳቸውን አሳልፈው ሸጡ። የመጀመሪያው የግብጻውያን ዘመቻና የቤተ መቅደሱ መዘረፍ 16 አንጥዮኩስ የመንግሥቱን ሥልጣን በሚገባ ካጠናከረና ካደራጀ በኋላ በራሱ ግዛት ላይና በምሥር (በግብጽ) ላይ ለመንገሥ ተነሣሣ። 17 ሠረገላዎች፥ ዝሆኖችና ብዙ የጦር ሠራዊት ይዞ ወደ ግብጽ አገር ገባ፤ 18 ከግብጽ ንጉሥ ከጰጠሎሜዎስ ጋር ጦርነት ገጠመ፤ ጰጠሎሜዎስ ተሸነፈና ብዙ ቁስለኞችን ትቶ ሸሸ። 19 የግብጻውያን ምሽጐች ተያዙ፤ አንጥዮኩስ የግብጽን ምርካኞች ወሰደ። 20 ግብጽን አሸንፎ በመቶ አርባ ሦስት ዓመተ ዓለም ተመለሰና ከባድ የጦር ሠራዊት ይዞ በእስራኤልና በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፥ 21 በትዕቢት ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ገብቶ የወርቅ መሠዊያውንና የመብራት መቅረዙን፥ ሌሎቹንም ዕቃዎች ሁሉ፥ 22 የሕብስት ማቅረቢያ ጠረጴዛውን የመጠጥ ማቅረቢያ ዕቃዎችን፥ ጽዋዎችን፥ የዕጣን ማጨሻ የወርቅ ዕቃዎችን፥ መጋረጃዎችና ዘውዶችን ወሰደ፤ በቤተ መቅደሱ መግቢያ ላይ የነበረውን የወርቅ ጌጥ በሙሉ አንሥቶ ወሰደው። 23 እንዲሁም ብሩንና ወርቁን፥ ክቡር ዕቃዎችን ወሰደ፤ ያገኛቸውን የቤተ መቅደሱን የሀብት ሥውር መዝገቦችንም ዘረፈ። 24 ሁሉንም ይዞ ወደ ሀገሩ ሄደ። ብዙ የሰው ደም አፈሰሰ፤ በትዕቢት የተሞሉ የስድብ ቃሎች ተናገረ። 25 በመላው የእስራኤል ሀገር ታላቅ ኀዘን ተደረገ። 26 ሹማምንትና ሽማግሌዎች በኀዘን አለቀሱ፤ ወጣቶችና ልጃገረዶች ተጐሳቆሉ፤ የሴት ቁንጅና ደበዘዘ። 27 ሙሽራው ዋይ ዋይ አለ፤ ሙሽሪትም በቤት ውስጥ በኀዘን ተኮራመተች። 28 ምድር በነዋሪዎችዋ ምክንያት ተንቀጠቀጠች፤ የያዕቆብ (የእስራኤል ቤት) በሙሉ ኀፍረትን ተከናነበ። የአክራን ግንባታና የሚሳርክ ጣልቃ ገብነት 29 ከሁለት ዓመት በኋላ ንጉሡ ወደ ይሁዳ ከተሞች አንድ የግብር ሹም ላከ እርሱም ከባድ ጦር ሠራዊት ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 30 ለሰዎቹ በውሸት የሰላም ቃል ተናገራቸውና አመኑት፤ ከዚያ በኋላ በድንገት ወደ ከተማዋ ገባ፤ ትልቅ አደጋ ጣለባት፤ በእስራኤል ውስጥ ብዙ ሰዎች ገደለ። 31 ከተማዋን ዘረፈ፤ አቃጠለ፤ ቤቶችንና ቅጥሩን አፈራረሰ። 32 ሴቶችንና ሕፃናትን ማርከው ወሰዱ፤ ከብቶችንም ወሰዱ። 33 ከእዚህ በኋላ የዳዊትን ከተማ ደግሞ ገነቡ፤ በዙሪያዋም ረጅም መካበቢያና ጠንካራ ምሽጐች አደረጉ። ምሽጋቸውም እዚያው ሆነ። 34 ሃይማኖትና ሕግ የሌላቸውን ክፉ ሰዎች ጠባቂዎች አደረጉባትና አጠናከሩዋት። 35 የጦር መሣሪያና ስንቅ አከማቹባት፤ የሰበሰቧቸውን የኢየሩሳሌምን ምርኮዎች አስቀመጡባት፤ ትልቅ ማጥመጃም ሆነላቸው። 36 ይህ ነገር ለቤተ መቅደሱ ወጥመድ ሆነ፤ ለእስራኤልም ሁልጊዜ መጥፎ ተቃራኒ ሆነበት። 37 በመቅደሱ ዙሪያ የንጹሐን ደም አፈሰሱ፤ ቅዱሱን ቦታ አረከሱ። 38 በእነርሱ ምክንያት የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሸሽተው ሄዱ፤ ከተማዋ የጸጉረ ልውጦች መኖሪያ ሆነች፤ ለትውልዷ እንግዳ ሆነች፤ የገዛ ልጆችዋ ጥለዋት ሄዱ። 39 የተበዘበዘው ቤተ መቅደስዋ ባዶውን ቀረ፤ በዓሎችዋ በኀዘን ተለወጡ፤ ሰንበቶችዋ ማላገጫ ሆኑ፤ ክብርዋም ተናቀ። 40 የከበረችውን ያህል ተዋረደች፤ ታላቅነትዋም ለኀዘን ቦታውን ለቀቀ። የአሕዛብ አምልኮ መደራጀት 41 ንጉሡ በመላው መንግሥቱ የእርሱ የሆኑ ሕዝቦች ሁሉ አንድ እንዲሆነና ሁሉም የራሱን የተለየ ባህል እንዲተው አወጀ። 42 አሕዛቦች ሁሉ የንጉሡን ትእዛዝ እሺ ብለው ተቀበሉ። 43 ብዙ እስራኤላውያን ለጣዖቶች መሥዋዕት በማቅረብና ሰንበትን በማርከስ አምልኮውን ተቀበሉ። 44 እንዲሁም ንጉሡ በሀገራቸው እንግዳ የሆኑትን ልምዶች እንዲከተሉ በማዘዝ ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ ከተሞች በመልእክተኞች አድርጐ ደብዳቤዎችን ላከ፤ 45 ከቤተ መቅደሱ የሚቃጠሉ መባዎችን፥ መሠዋዕቶችንና መጠጦችን እንዲያስወግዱ፥ ሰንበትንና በዓላትን እንዲያረክሱ አዘዘ፥ 46 ቤተ መቅደሱንና የተቀደሱ ነገሮችን እንዲያረክሱ፤ 47 ለጣዖቶች የተቀደሱ ቦታዎችን መሠዊያዎችን፥ ቤተ መቅደሶችንም እንደሠሩና አሳማዎችንና ያልተፈቀዱ እንስሶችን እንዲሠዉ፤ 48 ልጆቻቸውን እንዳያስገርዙ፤ ሁሉን ዓይነት ርክሰት በመሥራት ነፍሳቸውን እንደያሳድፉ አዘዘ፤ 49 ይህን ሁሉ የሚያደርጉትም ሁሉ የሙሴን ሕግ በመርሳትና ትእዛዘቹንም በማፍረስ ነው። 50 የንጉሡን ትእዛዝ አልፈምም ያለ ሁሉ ይገደላል። 51 በዚህ ዓይነት ነው ንጉሡ በእርሱ ሥር ለሚገኙ ዜጎች ሁሉ በጽሑፍ ትእዛዙን ያስተላለፈው፤ በሕዝቡ ሁሉ ላይ ተቆጣጣሪ አደረገበት፤ በየከተማው መሥዋዕቶች እንዲያቀርቡ ወደ ይሁዳ ከተሞች ትእዛዝ አስተላለፈ። 52 ከሕዝቡ ብዙ ሰዎች የሙሴን ሕግ በመተው ከአረማውያን ጋር ተስማሙ፤ በሀገሪቱ ላይ ክፉ ሥራ ሠሩ፤ 53 እስራኤላውያን በየመደበቂያ ቦታቸው እንዲሸሸጉ አስገደዱአቸው። 54 ቄስለው ወር (ከኀዳር 15 እስከ ታኀሣሥ 15) በዓሥራ አምስተኛው ቀን ንጉሡ በሚቀጥለው መሥዋዕት መሠዊያ ላይ የጥፋት ርኩሰት ሠራ፤ በይሁዳ ከተሞች ዙሪያም መሠዊያዎች ተቋቋሙ። 55 በቤቶች መዝጊያዎች አጠገብና በአደባባዮች ዕጣን ያጨሱ ነበር። 56 የሙሴን ሕግ መጻሕፍት ሲያገኙዋቸውም ቀዳደው በእሳት ውስጥ ይጨምሩዋቸው ነበር። 57 የብሉይ ኪዳን መጽሐፈ ይዞ የተገኘና የሙሴን ሕግ የሚያከብር ሰው በንጉሡ ውሳኔ መሠረት ይገደል ነበር። 58 ውሳኔውን ሲያፈርሱ የሚያዙ እስራኤላውያን በየወሩ በጭካኔ ይቀጡ ነበር። 59 በየወሩ በ 25ኛው ቀን በቤተ መቅደሱ መሠዊያ ላይ በተሠራው መሠዊያቸው ላይ ይሠዉ ነበር። 60 ልጆቻቸውን ያስረገዙ ሴቶች በንጉሡ ውሳኔ መሠረት ይገደሉ ነበር። የተረገዙት ሕፃናትም በእናቶቻቸው አንገት ላይ እንዲሰቀሉ ይደረጉ ነበር። 61 ቤተሰቦቻቸውና የግርዘት ሥርዓቱን የፈጸሙ ሁሉ ከሞት አያመልጡም ነበር። 62 ይሁን እንጂ በእስራኤል ብዙዎች በእምነታቸው ጠንካሮች ሆነው ተገኝተዋል፤ እርኩስ ነገር ላለመብላትመ ኃይል አግኝተዋል። 63 እርኩስ ምግብ ከመብላትና ቅዱሱን ቃል ኪዳን ከማርከስ ይልቅ ሞትን መርጠው ሞተዋል። 64 በእስራኤል ላይ የወደቀው ቅጣት አስፈሪ ጥፋት ነበር። |