1 ነገሥት 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የሰሎሞን ቤተ መቅደሱን መሥራት መጀመር 1 የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር ከወጡ ከአራት መቶ ሰማኒያ ዓመት በኋላ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ ተብሎ በሚጠራው በሁለተኛው ወር የጌታን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ። 2 ለጌታ የሠራው ቤተ መቅደስ ርዝመቱ ኻያ ሰባት ሜትር፥ ወርዱ ዘጠኝ ሜትር፥ ቁመቱ ዐሥራ ሦስት ሜትር ተኩል ነበር። 3 በመግቢያው በር የሚገኘው በረንዳ ቁመቱ አራት ሜትር ተኩል፥ ወርዱ ልክ እንደ ቤተ መቅደሱ ዘጠኝ ሜትር ነበር። 4 ለቤተ መቅደሱም ሕንጻ ከውስጥ ሰፋ፥ ከውጪ ጠበብ ያሉ መስኮቶች ነበሩት። 5 የቤተ መቅደሱን ሕንጻ አስጠግቶ በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ ዙሪያ ደርብ ሠራ፤ በዙሪያውም ክፍሎችን አደረገ። 6 የታችኛው ፎቅ ክፍል ወርዱ ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር፥ የሁለተኛው ፎቅ ክፍል ወርዱ ሁለት ሜትር ከሰባ ሳንቲ ሜትር፥ የመጨረሻው ፎቅ ክፍል ወርዱ ሦስት ሜትር ከዐሥር ሳንቲ ሜትር ነበር፤ የእያንዳንዱም ወለል ግንብ ከታች በኩል ካለው የወለል ግንብ የሳሳ ነበር፤ ሠረገሎቹ ወደ ቤተ መቅደሱ ግድግዳ እንዳይገቡ ለማድረግ ከቤተ መቅደሱ ግድግዳ ውጪ ዐረፍቶችን አደረገ። 7 ቤተ መቅደሱ የታነጸባቸው ድንጋዮች ተጠርበው የተዘጋጁት፤ በዚያው በተፈለጡበት ቦታ ነበር፤ ስለዚህም ቤተ መቅደሱ በሚሠራበት ጊዜ የመዶሻ፥ የመጥረቢያ ወይም የሌላ ብረት ነክ መሣሪያ ድምፅ አይሰማም ነበር። 8 ተጨማሪ ሆኖ የተሠራው ሕንጻ የታችኛው ፎቅ መግቢያ በር የሚገኘው ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ በኩል ነበር፤ እርሱም ከሁለተኛውና ከሦስተኛው ፎቅ ጋር የሚያገናኙት ደረጃዎች ነበሩት። 9 በዚህ አኳኋን ሰሎሞን የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ሥራ ፈጸመ፤ ጣራውንም ከውስጥ በኩል ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ አግዳሚ ሠረገላና ጠርብ ለበደው። 10 የእያንዳንዱ ፎቅ ቁመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ሆኖ ከውጪ በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ ተጠግቶ የተሠራው ባለ ሦስት ፎቅ ተጨማሪ ሕንጻ ከዋናው ሕንጻዎች ከሊባኖስ ዛፍ በተሠሩት አግዳሚ ሠረገሎች የተያያዘ ነበር። 11 የጌታ ቃል ወደ ሰሎሞንን እንዲህ ሲል መጣ፦ 12 “ስለዚህ ስለምትሠራው ቤት ሕጎቼን፥ ትእዛዞቼንና ሥርዓቴን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባትህ ለዳዊት የሰጠሁትን የተስፋ ቃል ለአንተ አጸናለሁ። 13 በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁ፤ ሕዝቤን እስራኤልንም ከቶ አልለያቸውም።” 14 በዚህ ዓይነት ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ፈጸመ። የቤተ መቅደሱ የውስጥ አሠራር ( 2ዜ.መ. 3፥8-14 ) 15 የቤተ መቅደሱ ግንብ ከውስጥ በኩል ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርበው በተሠሩ ሳንቃዎች ተለበደ፤ የወለሉም ጣውላ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠራ ነበር። 16 ቅድስተ ቅዱሳን ተብሎ የሚጠራ አንድ ውስጣዊ ክፍል ከቤተ መቅደሱ በስተ ኋላ ገባ ብሎ ተሠራ፤ የእርሱም ርዝመት ዘጠኝ ሜትር ሲሆን ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ የተከፈለ ነበር። 17 ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት የሚገኘውም የተቀደሰ ክፍል ርዝመቱ ዐሥራ ስምንት ሜትር ነበር። 18 የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ሳንቃዎች በአበባ እንቡጦችና በፈኩ አበባዎች ቅርጽ አጊጠው ነበር፤ ውስጡም ሁሉ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ ስለ ተለበደ የግንቡ ድንጋዮች አይታዩም ነበር። 19 ከቤተ መቅደሱ ውስጥ በስተ ኋላ በኩል የጌታ የቃል ኪዳን ታቦት የሚቀመጥበት ውስጣዊ ክፍል ተሠራ። 20 ይህም ውስጣዊ ክፍል ርዝመቱ ዘጠኝ ሜትር፥ ወርዱ ዘጠኝ ሜትር፥ ቁመቱ ዘጠኝ ሜትር፥ ሲሆን በሙሉ በንጹሕ ወርቅ የተለበጠ ነበር፤ መሠዊያውም ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ የተለበደ ነበር። 21 ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱን በውስጥ በኩል በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ እርሱም በወርቅ በተለበጠው ውስጠኛ ክፍል መግቢያ በር ክፈፉንም በተሸጋገሩ የወርቅ ሰንሰለቶች አስጌጠው። 22 በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ የሚገኘውን መሠዊያ ጭምር መላውን ቤተ መቅደስ ከውስጥ በኩል በወርቅ ለበጠው። 23 የእያንዳንዳቸው ቁመት አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር የሆነ፥ ከወይራ እንጨት በሁለት ኪሩቤል አምሳል የተቀረጹ ሥዕሎች በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ሠራ። 24 የአንደኛው ኪሩብ አንዱ ክንፍ አምስት ክንድ ሲሆን፥ ሌላውም ክንፉ እንደዚሁ አምስት ክንድ ነበር፤ ይህም ከአንዱ ክንፍ ጫፍ እስከ ሌላው ክንፍ ጫፍ ዐሥር ክንድ ማለት ነው። 25 የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ እንደዚሁ ዐሥር ክንድ ሆነ፥ ሁለቱ ኪሩቤል በመጠንና በቅርጽ አንድ ዓይነት ነበሩና። 26 የየአንዳንዱ ኪሩብ ቁመት አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር ነበር። 27 ኪሩቤልንም በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ እንዲቆሙ አደረገ፤ ስለዚህም የተዘረጉ ሁለቱ ክንፎቻቸው በክፍሉ መካከለኛ ቦታ ላይ ተገናኝተው ሌሎቹ ሁለቱ ክንፎቻቸው ደግሞ በተዘረጉበት አቅጣጫ ግንቦቹን ይነኩ ነበር። 28 ሁለቱንም ኪሩቤል በወርቅ ለበጣቸው። 29 የዋናውን ክፍልና የውስጠኛውን ክፍል ግንቦች በሙሉ በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው። 30 እርሱም ከውስጥና ከውጪ በኩል ያሉትን ክፍሎች ወለል እንኳ በወርቅ ለበጣቸው። 31 ከወይራ እንጨት የተሠራ ሁለት ተከፋች በር በቅድስተ ቅዱሳኑ መግቢያ እንዲቆም አደረገ፤ በሩም አምስት ማእዘን ያለው ሆኖ አናቱ ላይ ቀጥ ብሎ የተሠራ ቅስት ነበር። 32 ሁለቱን በሮች በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው፤ እርሱም በሮቹን፥ ኪሩቤልን፥ የዘንባባ ዛፎቹን፥ ቅርጾቹንም በወርቅ ለበጣቸው። 33 እንዲሁም ወደ ዋናው ክፍል ለሚያደርሰው መግቢያ በር ከወይራ እንጨት የተሠራ ባለ አራት ማእዘን ክፈፍ አበጀለት። 34 ሁለቱንም በሮች ከዝግባ እንጨት ሠራ፤ አንዱ በር በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ፤ ሁለተኛውም በር በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ። 35 እነርሱንም ሙሉ በሙሉ በወርቅ በተለበጡ በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው። 36 በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አንድ የውስጥ አደባባይ ሠራ፤ በዚህም አደባባይ ዙሪያ በየሦስቱ ዙር የድንጋይ ረድፍ አንድ የሊባኖስ ዛፍ ሠረገላ ሳንቃ የተጋደመበት ግንብ አደረገ። 37 የጌታ ቤት መሠረት የተጣለው በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ ተብሎ በሚጠራው ወር ነበር። 38 ሰሎሞን በነገሠ በዐሥራ አንደኛ ዓመቱ፥ ቡል ተብሎ በሚጠራው በስምንተኛው ወር ላይ የቤተ መቅደሱ ሥራ ልክ በታቀደው መሠረት ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቀ፤ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የፈጀበት ጊዜ ሰባት ዓመት ነበር። |