Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ዮሐንስ 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ልጆቼ ሆይ፥ ይህን የምጽፍላችሁ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ብዬ ነው። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

2 እርሱም የኃጢአታችን ማስተስረያ ነው፥ ለእኛ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።

3 ትእዛዛቱን ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን።

4 “አውቀዋለሁ” የሚል፥ ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ እርሱ ሐሰተኛ ነው፥ እውነትም በእርሱ ዘንድ የለም።

5 ቃሉን የሚጠብቅ ግን በእውነት የእግዚአብሔርን ፍቅር በእርሱ ፍጹም ሆኗል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን።

6 በእርሱ እኖራለሁ የሚል፥ ልክ እርሱ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል።

7 ወዳጆቼ ሆይ፥ አዲስ ትእዛዝ አልጽፍላችሁም፤ ነገር ግን ከመጀመሪያ የነበራችሁ አሮጌ ትእዛዝ ነው እንጂ፤ አሮጌውም ቃል የሰማችሁት ነው።

8 በሌላ በኩል አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም በእርሱ እና በእናንተ ዘንድ እውነት ነው፤ ጨለማው አልፏል፥ እውነተኛው ብርሃን እያበራ ነው።

9 በብርሃን አለሁ እያለ ወንድሙን ግን የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ ውስጥ ነው።

10 ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ይኖራል፥ በእርሱም ዘንድ ማሰናከያ የለም።

11 ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ ይኖራል፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ ጨለማው ዐይኖቹን ስላሳወረው ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም።

12 ልጆች ሆይ፥ ስለ ስሙ ኃጢአታችሁ ይቅር ስለ ተባለላችሁ እጽፍላችኋለሁ።

13 አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችሁታልና እጽፍላችኋለሁ። ወጣቶች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችሁታልና እጽፍላችኋለሁ።

14 ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችሁታልና ጽፌላችኋለሁ። አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችሁታልና ጽፌላችኋለሁ። ወጣቶች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በውስጣችሁ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ ጽፌላችኋለሁ።

15 ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን ነገሮች አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ የአብ ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።

16 ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፥ የሥጋ ምኞት፥ የዐይን ምኞት፥ በኑሮ ደረጃ መመካት፥ ከዓለም ነው እንጂ ከአብ አይደለም።

17 ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘለዓለም ይኖራል።

18 ልጆች ሆይ፥ ይህ የመጨረሻው ሰዓት ነው፤ የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣል ሲባል እንደ ሰማችሁት አሁን እንኳ ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች መጥተዋል፤ በዚህም ይህ የመጨረሻው ሰዓት እንደሆነ እናውቃለን።

19 ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ነገር ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ኖሮ ከእኛ ጋር በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ እንዲገለጥ ወጡ።

20 እናንተ ግን ከቅዱሱ፥ ቅባት አላችሁ፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ።

21 የምጽፍላችሁ እውነትን ስለማታውቁ አይደለም፥ ነገር ግን ስለምታውቁትና ውሸት ሁሉ ከእውነት ስላልሆነ ነው።

22 ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን ከሚክድ በቀር ሐሰተኛ ማን ነው? ይህ አብን እና ወልድን የሚክድ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።

23 ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ የለውም፤ በወልድ የሚያምን አብ አለው።

24 ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ከኖረ፥ እናንተም በወልድና በአብ ትኖራላችሁ።

25 እርሱ የሰጠን ተስፋ ይህ ነው፥ እርሱም የዘለዓለም ሕይወት ነው።

26 ስለሚያታልሉአችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ።

27 እናንተ ግን ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ስለሚኖር፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉም እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነትም እንደሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እርሱ እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።

28 ልጆች ሆይ፥ እርሱ በሚገለጥበት ጊዜ ድፍረት እንዲኖረን፥ በሚመጣበትም ጊዜ በፊቱ እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ።

29 እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ካወቃችሁ፥ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ ታውቃላችሁ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos