Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ዜና መዋዕል 9 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 እስራኤልም ሁሉ በየትውልዳቸው ተቈጠሩ፤ እነሆም፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጻፉ። ይሁዳም ስለ ኃጢአታቸው ወደ ባቢሎን ተማረኩ።

2 በአውራጃዎቻቸውና በከተሞቻቸው መጀመሪያ የተቀመጡ እስራኤልና ካህናት ሌዋውያንም የቤተ መቅደሱም አገልጋዮች ነበሩ።


ከምርኮ በኋላ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች

3 ከይሁዳ ልጆችና ከብንያም ልጆች ከኤፍሬምና ከምናሴ ልጆች በኢየሩሳሌም ተቀመጡ።

4 ከይሁዳ ልጅ ከፋሬስ ልጆች የባኒ ልጅ የአምሪ ልጅ የዖምሪ ልጅ የዓሚሁድ ልጅ ዑታይ ደግሞ በዚያ ተቀመጠ።

5 ከሴሎናውያንም በኩሩ ዓሣያና ልጆቹ በዚያ ተቀመጡ።

6 ከዛራም ልጆች ይዑኤልና ወንድሞቻቸው፥ ስድስት መቶ ዘጠና ነበሩ።

7 ከብንያምም ልጆች የሐስኑአ ልጅ የሆዳይዋ ልጅ የሜሱላም ልጅ ሰሉ ነበር፤

8 የይሮሐም ልጅ ብኔያ፤ የሚክሪ ልጅ የኦዚ ልጅ ኤላ ነበር፤ የይብንያ ልጅ የራጉኤል ልጅ የሰፋጥያስ ልጅ ሜሱላም ነበር፤

9 በየትውልዳቸውም ወንድሞቻቸው ዘጠኝ መቶ ኀምሳ ስድስት ነበሩ፤ እነዚህ ሰዎች ሁሉ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ነበሩ።


የካህናት ወገን

10 ከካህናቱም ዮዳኤ፥ ዮአሪብ፥ ያኪን ነበሩ፤

11 የእግዚአብሔርም ቤት አለቃ የአኪጦብ ልጅ የመራዮት ልጅ የሳዶቅ ልጅ የሜሱላም ልጅ የኬልቅያስ ልጅ ዓዛርያስ ነበር፤

12 የመልክያ ልጅ የጳስኮር ልጅ የይሮሐም ልጅ ዓዳያ ነበር፤ የኢሜር ልጅ የምሺላሚት ልጅ የሜሱላም ልጅ የየሕዜራ ልጅ የዓዲኤል ልጅ መዕሣይ ነበር፤

13 የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች ወንድሞቻቸው ሺህ ሰባት መቶ ስልሳ ነበሩ፤ ለእግዚአብሔር ቤት ለሚከናወነው የአገልግሎት ሥራ እጅግ ብቃት ያላቸው ሰዎች ነበሩ።


የሌዋውያን ወገን

14 ከሌዋውያንም የሜራሪ ልጆች የአሳብያ ልጅ የዓዝሪቃም ልጅ የአሱብ ልጅ ሸማያ ነበር፤

15 በቅበቃር፥ ኤሬስ፥ ጋላል፥ የአሳፍ ልጅ የዝክሪ ልጅ የሚካ ልጅ መታንያ ነበር፤

16 የኤዶታም ልጅ የጋላል ልጅ የሰሙስ ልጅ አብድያ ነበር፤ በነጦፋውያንም መንደሮች የተቀመጠው የሕልቃና ልጅ የአሳ ልጅ በራክያ ነበር።

17 በርም ጠባቂዎች ሰሎም፥ ዓቁብ፥ ጤልሞን፥ አሒማን፥ ወንድሞቻቸውም ነበሩ፤ ሰሎምም አለቃ ነበረ።

18 እስከ ዛሬም ድረስ በንጉሥ በር በምሥራቅ በኩል ሰፍረዋል፤ ለሌዊ ልጆች ሰፈር በርም ጠባቂዎች ነበሩ።

19 የቆሬም ልጅ የአብያሳፍ ልጅ የቆሬ ልጅ ሰሎም ከአባቱም ቤት የነበሩ ወንድሞቹ ቆሬያውያን በማገልገል ሥራ ላይ ነበሩ፥ አባቶቻቸውም የጌታን ሰፈር መግቢያ ይጠብቁ እንደ ነበር እንዲሁ የድንኳኑን የመግቢያ ደጅ ይጠብቁ ነበር።።

20 አስቀድሞም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ አለቃቸው ነበረ፤ ጌታም ከእርሱ ጋር ነበረ።

21 የሜሱላም ልጅ ዘካርያስ የመገናኛው ድንኳን ደጅ ጠባቂ ነበረ።

22 የመግቢያው ደጅ ጠባቂዎች እንዲሆኑ የተመረጡ እነዚህ ሁሉ ሁለት መቶ ዐሥራ ሁለት ነበሩ። ዳዊትና ነቢዩ ሳሙኤል በሥራቸው ያቆሙአቸው እነዚህ በመንደሮቻቸው በየትውልዳቸው ተቈጠሩ።

23 እነርሱና ልጆቻቸውም በጌታ ቤት በድንኳኑ ደጆች ላይ ዘበኞች ነበሩ።

24 በአራቱ ማዕዘኖች፥ በምሥራቅ፥ በምዕራብ፥ በሰሜን፥ በደቡብ፥ ጠባቂዎች ነበሩ።

25 በመንደሮቸቻቸውም የነበሩ ወንድሞቻቸው በየሰባትም ቀን ከእነርሱ ጋር አብረው ለመሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይመጡ ነበር።

26 ከሌዋውያንም የነበሩ አራቱ የጠባቂዎች አለቆች በሥራቸው ታማኞች ነበሩ፤ በጌታም ቤት ባሉ ጓዳዎችና ቤተ መዛግብት ላይ ተሹመው ነበር።

27 የእግዚአብሔርንም ቤት የሚጠብቁ፥ ጥዋት ጥዋትም ደጆቹን የሚከፍቱ እነርሱ ነበሩና በዚያ ያድሩ ነበር።

28 ዕቃውም በቍጥር፥ ይገባና ይወጣ ነበርና ከእነዚህ እያንዳንዱ በመገልገያው ዕቃ ላይ ሹሞች ነበሩ።

29 ከእነርሱም አንዳንዶቹ በመቅደሱ ዕቃ ሁሉ በመልካሙም ዱቄት፥ በወይን ጠጁም፥ በዘይቱም፥ በዕጣኑም፥ በሽቶውም ላይ ሹሞች ነበሩ።

30 ከካህናቱም ልጆች አንዳንዶቹ የሽቶውን ቅባት ይቀምሙ ነበር።

31 የቆሬያዊውም የሰሎም በኩር ሌዋዊው ማቲትያ በምጣድ በሚጋገረው ኅብስት ላይ ሹም ነበረ።

32 ከወንድሞቻቸውም ከቀዓታውያን አንዳንዶቹን በየሰንበቱ የተቀደሰውን ኅብስት እንዲያዘጋጁ ሹሞች ነበሩ።

33 ከሌዋውያንም ወገን የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች የነበሩ መዘምራን እነዚህ ናቸው፤ ሥራቸውም ሌሊትና ቀን ነበረና ያለ ሌላ ሥራ በየእልፍኛቸው ይቀመጡ ነበር።

34 እነዚህ ከሌዋውያን የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች በየትውልዳቸውም አለቆች ነበሩ። እነዚህም በኢየሩሳሌም ይቀመጡ ነበር።


የንጉሥ ሳኦል ቤተሰብ

35 የሚስቱ ስም መዓካ የነበረው በገባዖን የተቀመጠው የገባዖን አባት ይዒኤል፥

36 የበኩር ልጁም ዓብዶን፥ ከዚያም በኋላ ዱር፥ ቂስ፥ በኣል፥ ኔር፥ ናዳብ፥

37 ጌዶር፥ አሒዮ፥ ዛኩር፥ ሚቅሎት ነበሩ።

38 ሚቅሎትም ሳምአን ወለደ፤ እነርሱ ደግሞ ከወንድሞቻቸው ጋር በኢየሩሳሌም በወንድሞቻቸው ፊት ለፊት በሚገኝ ስፍራ ይቀመጡ ነበር።

39 ኔርም ቂስን ወለደ፤ ቂስም ሳኦልን ወለደ፤ ሳኦልም ዮናታንን፥ ሜልኪሳን፥ አሚናዳብን፥ አስባኣልን ወለደ።

40 የዮናታንም ልጅ መሪበ-ኣል ነበረ፤ መሪበ-ኣልም ሚካን ወለደ።

41 የሚካም ልጆች ፒቶን፥ ሜሌክ፥ ታሪዓ፥ አካዝ ነበሩ።

42 አካዝም የዕራን ወለደ፤ የዕራም ዓሌሜትን፥ ዕዝሞትን፥ ዘምሪን ወለደ፤ ዘምሪም ሞጻን ወለደ።

43 ሞጻም ቢንዓን ወለደ፥ ልጁም ረፋያ፥ ልጁ ኤልዓሣ፥ ልጁ ኤሴል ነበሩ፤

44 ለኤሴልም ስድስት ልጆች ነበሩት፤ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ዓዝሪቃም፥ ቦክሩ፥ እስማኤል፥ ሸዓርያ፥ አብድዩ፥ ሐናን፤ እነዚህ የኤሴል ልጆች ነበሩ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos