1 ዜና መዋዕል 27 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የሠራዊቱ አከፋፈል 1 የእስራኤልም ልጆች የአባቶች ቤቶች አለቆች የሺህ አለቆች የመቶ አለቆችም በክፍሎች ምደባ ሁሉ ንጉሡን ያገለገሉት ሹማምንት እንደ ቁጥራቸው እነዚህ ነበሩ። እነዚህም ክፍሎች እያንዳንዳቸው ሀያ አራት ሺህ ሆነው በዓመት ውስጥ ባሉት ወራት ሁሉ በየወሩ ይገቡና ይወጡ ነበር። 2 ለመጀመሪያው ወር የዘብድኤል ልጅ ያሾብዓም በአንደኛው ክፍል ላይ ተሹሞ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 3 እርሱ ከፋሬስ ልጆች ነበረ፤ ለመጀመሪያ ወር በሠራዊቱ አለቆች ሁሉ ላይ ተሾሞ ነበር። 4 በሁለተኛውም ወር ባለው ክፍል ላይ አሆሃዊው ዱዲ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 5 ለሦስተኛው ወር ሦስተኛው የሠራዊቱ አለቃ የካህኑ የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነበረ፤ በእነርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 6 ይህ በናያስ በሠላሳው መካከል ኃያል ሆኖ ሠላሳውን ያዝ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ልጁ ዓሚዛባድ ተሹሞ ነበር። 7 ለአራተኛው ወር አራተኛው አለቃ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ ከእርሱም በኋላ ልጁ ዝባድያ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 8 ለአምስተኛው ወር አምስተኛው አለቃ ይዝራዊው ሸምሁት ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባለላት ነበሩ። 9 ለስድስተኛው ወር ስድስተኛው አለቃ የቴቁሐዊው የዒስካ ልጅ ዒራስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 10 ለሰባተኛው ወር ሰባተኛው አለቃ ከኤፍሬም ልጆች የሆነ ፍሎናዊው ሴሌስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 11 ለስምንተኛው ወር ስምንተኛው አለቃ ከዛራውያን የነበረው ኩሳታዊው ሲቦካይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 12 ለዘጠነኛው ወር የዘጠነኛው አለቃ ከብንያማውያን የነበረው ዓናቶናዊው አቢዔዘር ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 13 ለአሥረኛው ወር አሥረኛው አለቃ ከዛራውያን የነበረው ነጦፋዊው ኖኤሬ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 14 ለዐሥራ አንደኛው ወር ዐሥራ አንደኛው አለቃ ከኤፍሬም ልጆች የነበረው ጲርዓቶናዊው በናያስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። 15 ለዐሥራ ሁለተኛው ወር ዐሥራ ሁለተኛው አለቃ ከጎቶንያል ወገን የነበረው ነጦፋዊው ሔልዳይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ውስጥ ሀያ አራት ሺህ አባላት ነበሩ። የነገዶች አለቆች 16 በእስራኤልም ነገዶች ላይ እነዚህ ነበሩ በሮቤላውያን ላይ የዝክሪ ልጅ አልዓዛር አለቃ ነበረ፤ በስማዖናውያን ላይ የመዓካ ልጅ ሰፋጥያስ አለቃ ነበረ፤ 17 በሌዊ ላይ የቀሙኤል ልጅ ሐሸብያ አለቃ ነበረ፤ በአሮን ላይ ሳዶቅ አለቃ ነበረ፤ 18 በይሁዳ ላይ ከዳዊት ወንድሞች ኢሊሁ አለቃ ነበር፤ በይሳኮር ላይ የሚካኤል ልጅ ዖምሪ አለቃ ነበረ፤ 19 በዛብሎን ላይ የአብድዩ ልጅ ይሽማያ አለቃ ነበረ፤ በንፍታሌም ላይ የዓዝሪኤል ልጅ ኢያሪሙት አለቃ ነበረ፤ 20 በኤፍሬም ልጆች ላይ የዓዛዝያ ልጅ ሆሴዕ አለቃ ነበረ፤ በምናሴ ነገድ እኩሌታ ላይ የፈዳያ ልጅ ኢዩኤል አለቃ ነበረ፤ 21 በገለዓድ ባለው በምናሴ ነገድ እኩሌታ ላይ የዘካርያስ ልጅ አዶ አለቃ ነበረ፤ በብንያም ላይ የአብኔር ልጅ የዕሢኤል አለቃ ነበረ፤ 22 በዳን ላይ የይሮሐም ልጅ ዓዛርኤል አለቃ ነበረ፤ እነዚህ የእስራኤል ነገዶች አለቆች ነበሩ። 23 ጌታ ግን እስራኤልን እንደ ሰማይ ከዋክብት ለማብዛት ተናግሮ ነበርና ዳዊት ከሀያ ዓመት በታች የነበሩትን አልቈጠረም። 24 የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ መቁጠር ጀመረ፥ ነገር ግን አልፈጸመም፤ ስለዚህም በእስራኤል ላይ ቁጣ ወረደ፥ ቁጥራቸውም በንጉሡ በዳዊት መዝገብ አልተጻፈም። ሌሎች ሹማምንት 25 በንጉሡም ቤተ መዛግብት ላይ የዓዲኤል ልጅ ዓዛሞት ሹም ነበረ፤ በአገሩም በከተሞቹም በመንደሮቹም በግንቦቹም ባሉ ቤተ መዛግብት ላይ የዖዝያ ልጅ ዮናታን ሹም ነበረ፤ 26 መሬቱን በሚያበጃጁትና እርሻውን በሚያርሱት ላይ የክሉብ ልጅ ዔዝሪ ሹም ነበረ፤ 27 በወይንም ቦታዎች ላይ ራማታዊው ሰሜኢ ሹም ነበረ፤ ለወይንም ጠጅ ዕቃ ቤት በሚቀርበው በወይኑ ምርት ላይ ሸፋማዊው ዘቢድ ሹም ነበረ። 28 በቈላውም ውስጥ ባሉት በወይራውና በሾላው ዛፎች ላይ ጌድራዊው በአልሐናን ሹም ነበረ፤ በዘይቱም ቤቶች ላይ ኢዮአስ ሹም ነበረ፤ 29 በሳሮንም በሚሰማሩ ከብቶች ላይ ሳሮናዊው ሰጥራይ ሹም ነበረ፤ በሸለቆቹም ውስጥ በነበሩት ከብቶች ላይ የዓድላይ ልጅ ሻፋጥ ሹም ነበረ፤ 30 በግመሎችም ላይ እስማኤላዊው ኡቢያስ ሹም ነበረ፤ በአህዮቹም ላይ ሜሮኖታዊው ዬሕድያ ሹም ነበረ፤ በመንጎቹም ላይ አጋራዊው ያዚዝ ሹም ነበረ። 31 እነዚህ ሁሉ በንጉሡ በዳዊት ሀብት ላይ ሹሞች ነበሩ። 32 አስተዋይና ጸሐፊ የነበረው የዳዊት አጎት ዮናታን አማካሪ ነበረ፤ የሐክሞኒም ልጅ ይሒኤል የንጉሡን ልጆች ያገለግል ነበረ፤ 33 አኪጦፌልም የንጉሡ አማካሪ ነበረ፤ አርካዊውም ኩሲ የንጉሡ ወዳጅ ነበረ፤ 34 ከአኪጦፌልም ቀጥሎ የበናያስ ልጅ ዮዳሄና አብያታር ነበሩ፤ ኢዮአብም የንጉሡ ሠራዊት አለቃ ነበረ። |