Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ዜና መዋዕል 26 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የደጁ ጠባቂዎች

1 የደጁም ጠባቂዎች ምድባቸው እንደዚህ ነበር፤ ከቆሬያውያን ከአሳፍ ልጆች የቆሬ ልጅ ሜሱላም።

2 ሜሱላም ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በኩሩ ዘካርያስ፥ ሁለተኛው ይዲኤል፥ ሦስተኛው ዮዛባት፥ አራተኛው የትኒኤል፥

3 አምስተኛው ኤላም፥ ስድስተኛው ይሆሐናን፥ ሰባተኛው ኤሊሆዔናይ ነበሩ።

4 ዖቤድ-ኤዶም ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በኩሩ ሸማያ፥ ሁለተኛው ዮዛባት፥ ሦስተኛው ኢዮአስ፥ አራተኛው ሣካር፥ አምስተኛው ናትናኤል፥

5 ስድስተኛው ዓሚኤል፥ ሰባተኛው ይሳኮር፥ ስምንተኛው ፒላቲ ነበሩ፤ እንዲህም የሆነለት እግዚአብሔር ስለ ባረከው ነበር።

6 ለልጁም ለሸማያ ደግሞ ልጆች ተወለዱለት፤ ጽኑዓንም ኃያላን ነበሩና በአባታቸው ቤት ሠለጠኑ።

7 የሸማያ ልጆች፤ ዖትኒ፥ ራፋኤል፥ ዖቤድ፥ ኤልዛባድ ነበሩ፤ ኤልዛባድም ኃያላን ወንድሞች የነበሩት እነርሱም ኤሊሁና ሰማክያ ነበሩ። እነዚህ ሁሉ የዖቤድ-ኤዶም ልጆች ነበሩ፤

8 እነርሱም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም ለማገልገል ኃያላን የነበሩ የዖቤድ-ኤዶም ልጆች ስልሳ ሁለት ነበሩ።

9 ለሜሱላም ኃያላን የነበሩ ዐሥራ ስምንት ልጆችና ወንድሞች ነበሩት።

10 ከሜራሪም ልጆች ለነበረው ለሖሳ ልጆች ነበሩት፤ አለቃውም ሽምሪ ነበረ፤ በኩር አልነበረም፥ አባቱ ግን አለቃ አደረገው፤

11 ሁለተኛውም ኬልቅያስ፥ ሦስተኛው ጥበልያ፥ አራተኛው ዘካርያስ ነበሩ፤ የሖሳ ልጆችና ወንድሞች ሁሉ ዐሥራ ሦስት ነበሩ።

12 እንደ ወንድሞቻቸው ሆነው በጌታ ቤት እንዲያገለግሉ በየአለቆቻቸው የደጁ ጠባቂዎች ሰሞነኞች እነዚህ ነበሩ።

13 በበሩም ሁሉ ለማገልገል በየአባቶቻቸው ቤቶች ታናሹና ታላቁ በተመሳሳይ መልኩ ይዕጣ ተጣጣሉ።

14 ለሰሌምያም በምሥራቅም በኩል ዕጣ ወጣለት። ለልጁም ብልህ አማካሪ ለሆነው ለዘካርያስ ዕጣ ጣሉ፤ የእርሱም ዕጣ በሰሜን በኩል ወጣ።

15 ለዖቤድ-ኤዶም ዕጣው በደቡብ በኩል ወጣ፥ ለልጆቹም የዕቃ ግምጃ ቤቱን እንዲጠብቁ ዕጣ ወጣላቸው።

16 ለሰፊንና ለሖሳ በዐቀበቱም መንገድ ባለው በሸሌኬት በር በምዕራብ በኩል ዕጣ ወጣላቸው፤ ይህም ጥበቃ ከጥበቃ ትይዩ ነበር።

17 በምሥራቅ በኩል ስድስት ሌዋውያን ነበሩ፤ በሰሜን በኩል ለየዕለቱ አራት፥ በደቡብ በኩል ለየዕለቱ አራት፥ ለዕቃ ቤቱም ሁለት ሁለት ነበሩ።

18 በምዕራብ በኩል በምሶሶው አጠገብ ባለው መንገድ አራት፥ በምሶሶም አጠገብ ሁለት ነበሩ።

19 ከቆሬና ከሜራሪ ልጆች የነበሩ የደጁ ጠባቂዎች ሰሞን ይህ ነበረ።


የቤተ መዛግብት ሹማምንት የጦር አዛዦችና ፈራጆች

20 ከሌዋውያን አኪያ በእግዚአብሔር ቤት በሚሆኑ ቤተ መዛግብትና በንዋየ ቅዱሳቱ ቤተ መዛግብት ላይ ተሾሞ ነበር።

21 የለአዳን ልጆች፤ የለአዳን ቤተሰብ የሆኑ የጌድሶናውያን ልጆች፥ ለጌድሶናዊው ከለአዳን ቤተሰብ የሆኑ የአባቶች ቤቶች አለቆች ይሒኤሊ ነበር፤

22 የይሒኤሊ ልጆች፤ በጌታ ቤት በቤተ መዛግብት ላይ ተሹመው የነበሩት ዜቶም፥ ወንድሙም ኢዮኤል ነበሩ።

23 ከእንበረማውያን፥ ከይስዓራውያን፥ ከኬብሮናውያን፥ ከዑዝኤላውያን፤

24 የሙሴ ልጅ የጌርሳም ልጅ ሱባኤል በቤተ መዛግብት ላይ ተሹሞ ነበር።

25 ወንድሞቹም፤ ለአልዓዛር ልጁ ረዓብያ፥ ልጁም የሻያ፥ ልጁም ኢዮራም፥ ልጁም ዝክሪ፥ ልጁም ሰሎሚት ነበሩ።

26 ይህ ሰሎሚትና ወንድሞቹ ንጉሡ ዳዊትና የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች የሠራዊቱም አዛዦች፥ በቀደሱት በንዋየ ቅድሳቱ ቤተ መዛግብት ሁሉ ላይ ተሾመው ነበር።

27 በጦርነትም ከተገኘው ምርኮ የጌታን ቤት ለመሥራት ስጦታ ቀድሰው ሰጡ።

28 ባለ ራእዩም ሳሙኤል፥ የቂስም ልጅ ሳኦል፥ የኔርም ልጅ አበኔር፥ የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ የቀደሱት ንዋየ ቅድሳት ሁሉ ከሰሎሚትና ከወንድሞቹ ሥልጣን በታች ነበረ።

29 ከይስዓራውያን ከናንያና ልጆቹ ሹማምትና ፈራጆች እንዲሆኑ በውጭው በሚከናወነው ሥራ በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር።

30 ከኬብሮናውያን ሐሸብያና ወንድሞቹ፥ ጽኑዓን የነበሩት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች፥ ለጌታ ሥራ ሁሉ ለንጉሡም አገልግሎት በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል ባለው በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር።

31 ከኬብሮናውያንም እንደ አባቶች ቤቶች ትውልዶች የኬብሮናውያን አለቃ ይሪያ ነበረ። ዳዊት በነገሠ በአርባኛው ዓመት ይፈልጉአቸው ነበር፤ በእነርሱም መካከል በገለዓድ ኢያዜር ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ተገኙ፤

32 ወንድሞቹም ጽኑዓን የነበሩት የአባቶች ቤቶች አለቆች ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። ንጉሡም ዳዊት ለእግዚአብሔር ጉዳይ ሁሉና ለንጉሡ ጉዳይ በሮቤላውያንና በጋዳውያን በምናሴም ነገድ እኩሌታ ላይ ሹሞች አደረጋቸው።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos