Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ዜና መዋዕል 21 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ቈጠራና መቅሰፍት

1 ሰይጣንም በእስራኤል ላይ ተነሣ፥ እስራኤልንም እንዲቈጥር ዳዊትን አነሣሣው።

2 ዳዊትም ኢዮአብንና የሕዝቡን አለቆች፦ “ሂዱ፥ ከቤር-ሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ እስራኤልን ቁጠሩ፥ ድምራቸውንም እንዳውቅ ተመልሳችሁ አስታውቁኝ” አላቸው።

3 ኢዮአብም አለ፦ “ጌታ ሕዝቡን በአሁኑ ላይ መቶ እጥፍ ይጨምር፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! ሁሉ የጌታዬ ባርያዎች አይደሉምን? ይህን ነገር ጌታዬ ለምን ይሻል? በእስራኤል ላይ በደል ስለምን ያመጣል?”

4 ነገር ግን የንጉሡ ቃል በኢዮአብ ላይ አሸነፈ፤ ኢዮአብም ወጥቶ በእስራኤል ሁሉ ላይ ተዘዋወረ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ።

5 ኢዮአብም የቈጠራቸውን የሕዝቡን ድምር ለዳዊት ሰጠ፤ ከእስራኤልም ሁሉ አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ፤ ከይሁዳም አራት መቶ ሰባ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ።

6 የንጉሡ ትእዛዝ ግን በኢዮአብ ዘንድ የተጠላ ነበረና ሌዊና ብንያም ከእነርሱ ጋር አልተቈጠሩም።

7 ከዚህም ነገር የተነሣ እግዚአብሔር ተቈጣ፥ እስራኤልንም ቀሠፈ።

8 ዳዊትም እግዚአብሔርን፦ “ይህን በማድረግ እጅግ በድያለሁ፤ አሁን ግን ይህን ባለማወቅ አድርጌአለሁና የባርያህን ኃጢአት እንድታስወግድ እለምንሃለሁ” አለው።

9 ጌታም ለዳዊት ባለ ራእይ ለጋድ፦

10 “ሂድ፥ ለዳዊት፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሦስቱን ነገሮች በፊትህ አኖራለሁ፤ በአንተ ላይ እንዳደርግብህ ከእነርሱ አንዱን ምረጥ’ ብለህ ንገረው” ብሎ ተናገረው።

11 ጋድም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘የምትወድደውን ምረጥ፤

12 የሦስት ዓመት ራብ፥ ወይም ሦስት ወር የጠላቶችህ ሰይፍ እንዲያገኝህ ከጠላቶችህም ፊት እንድትሰደድ፥ ወይም ሦስት ቀን የጌታ ሰይፍ ቸነፈርም በምድር ላይ እንዲሆን፥ የጌታም መልአክ በእስራኤል ምድር ሁሉ ጥፋትን እንዲያመጣ ምረጥ፤’ ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ አሁን ወስን።”

13 ዳዊትም ጋድን፦ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ብዙ ነውና በጌታ እጅ ልውደቅ፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ” አለው።

14 ጌታም በእስራኤል ላይ ቸነፈርን ሰደደ፤ ከእስራኤልም ሰባ ሺህ ሰዎች አለቁ።

15 እግዚአብሔርም ለማጥፋት ወደ ኢየሩሳሌም መልአክን ላከ፤ ሊያጠፋትም በቀረበ ጊዜ ጌታ አይቶ ስለ ክፉው ነገር ተፀፀተ፥ የሚያጠፋውንም መልአክ፦ “በቃህ፤ አሁን እጅህን መልስ” አለው። የጌታም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር።

16 ዳዊትም ዐይኖቹን አነሣ፤ የጌታ መልአክ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ፥ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተዘርግቶ አየ። ዳዊትም ሽማግሌዎችም ማቅ ለብሰው በግምባራቸው ተደፍተው ሰገዱ።

17 ዳዊትም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፦ “ሕዝቡ እንዲቈጠር ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? የበደልሁና ክፉ የሠራሁ እኔ ነኝ፤ እነዚህ በጎች ግን ምን አድርገዋል? አቤቱ አምላኬ ሆይ! እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ይሁን፥ ነገር ግን መቅሰፍት በሕዝብህ ላይ አይሁን።”


የንጉሥ ዳዊት መሠውያና መሥዋዕት

18 የጌታም መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ላይ ለጌታ መሠዊያ እንዲሠራ ለዳዊት እንዲነግረው ጋድን አዘዘው።

19 ዳዊትም በጌታ ስም እንደ ተናገረው እንደ ጋድ ቃል ወጣ።

20 ኦርናም ዘወር ብሎ መልአኩን አየ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩ አራቱ ልጆች ተሸሸጉ፤ ኦርናም ስንዴ ያበራይ ነበር።

21 ዳዊትም ወደ ኦርና በመጣ ጊዜ ኦርና ቀና ብሎ ተመለከተ ዳዊትንም አየ፤ ከአውድማውም ወጥቶ ዳዊትን እጅ ሊነሣ በምድር ላይ ተደፍቶ ሰገደ።

22 ዳዊትም ኦርናን፦ “በላዩ ለጌታ መሠዊያ እንድሠራ ይህን የአውድማ ስፍራ ስጠኝ፤ ሙሉ ዋጋ ልክፈልና ስጠኝ፤ መቅሰፍቱም ከሕዝቡ ይከለከላል” አለው።

23 ኦርናም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ለአንተ ውሰደው፥ ጌታዬ ንጉሡም ደስ የሚያሰኘውን ያድርግ፤ እነሆ፥ ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሬዎቹን፥ ለማገዶም የአውድማውን መውቅያ፥ ለእህልም ቁርባን ስንዴውን እሰጥሃለሁ፤ ሁሉን እሰጣለሁ።”

24 ንጉሡም ዳዊት ኦርናን፦ “አይደለም፥ ነገር ግን የአንተ የሆነውን ለጌታ አምጥቼ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ በከንቱ አላቀርብምና በሙሉ ዋጋ እገዛዋለሁ” አለው።

25 ዳዊትም ስለ ስፍራው ስድስት መቶ ሰቅል ወርቅ በሚዛን ለኦርና ሰጠው።

26 ዳዊትም በዚያ ለጌታ መሠዊያ ሠራ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕት አቀረበ፥ ጌታንም ጠራ፤ ጌታም ከሰማይ የሚቃጠለው መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ በእሳት መለሰለት።

27 ጌታም መልአኩን አዘዘው፥ ሰይፉንም በአፎቱ ከተተው።


ለቤተ መቅደሱ የተመረጠ ቦታ

28 በዚያን ጊዜ ጌታ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ እንደ መለሰለት ዳዊት ባየ ጊዜ፥ በዚያ መሥዋዕት ሠዋ።

29 ሙሴም በምድረ በዳ የሠራት የጌታ ማደሪያና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ በዚያን ጊዜ በገባዖን ባለው በኮረብታው መስገጃ ነበሩ።

30 ዳዊት ግን የጌታን መልአክ ሰይፍ ስለ ፈራ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደዚያ መሄድ አልቻለም።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos