1 ዜና መዋዕል 20 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ረባት መከበቧና መያዝዋ 1 እንዲህም ሆነ፤ በዓመት መለወጫ ነገሥታት ወደ ጦርነት በሚወጡበት ጊዜ ኢዮአብ ሠራዊቱን አወጣ፥ የአሞንንም ልጆች አገር አጠፋ፤ መጥቶም ረባትን ከበበ። ዳዊትም በኢየሩሳሌም ቈይቶ ነበር። ኢዮአብም ረባትን መትቶ አፈረሳት። 2 ዳዊትም የንጉሣቸውን ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፥ ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ነበረ፥ ክቡርም ዕንቁ ነበረበት፥ በዳዊትም ራስ ላይ አስቀመጡት፤ ከከተማይቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ። 3 በውስጥዋም የነበረውን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቈፈሪያ በመጥረቢያም እንዲሠሩ አደረጋቸው። እንዲሁም ዳዊት በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲሁ አደረገ። ዳዊትም ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ፍልስጥኤማውያን መበዝበዛቸው 4 ከዚህም በኋላ በጌዝር ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጦርነት ተደረገ፤ ኩሳታዊውም ሴቦካይ ከራፋይም ወገን የነበረውን ሲፋይን ገደለ። ፍልስጥኤማውያንም ተሸነፉ። 5 ዳግመኛም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጦርነት ተደርጎ ነበር፤ የያዒርም ልጅ ኤልያናን የጦሩ እጀታ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን የጌት ሰው የጎልያድን ወንድም ለሕሚን ገደለ። 6 ደግሞ በጌት ላይ ጦርነት ተደርጎ ነበረ፤ ከዚያም በእጁና በእግሩ ስድስት ስድስት ባጠቃላይ ሀያ አራት ጣቶች ያሉት አንድ ረጅም ሰው ነበረ፤ እርሱም ደግሞ ከራፋይም የተወለደ ነበረ። 7 እስራኤልንም በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ዮናታን ገደለው። 8 እነዚያም በጌት ውስጥ ከራፋይም የተወለዱ ነበሩ፤ በዳዊትም እጅ በባርያዎቹም እጅ ወደቁ። |