Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ዜና መዋዕል 19 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


አሞናውያንና ሶርያውያን መሸነፋቸው

1 ከዚህም በኋላ የአሞናውያን ንጉሥ ናዖስ ሞተ፥ ልጁም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

2 ዳዊትም፦ “አባቱ ስላደረገልኝ ወረታ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነት አደርጋለሁ” አለ። ዳዊትም አባቱ ስለ ሞተ ሊያጽናናው መልእክተኞችን ላከ፤ የዳዊትም ባርያዎች ሊያጽናኑት ወደ ሐኖን ወደ አሞን ልጆች ምድር መጡ።

3 የአሞን ልጆች ሹማምንት ግን ሐኖንን እንዲህ አሉት፦ “ዳዊት አባትህን አክብሮ የሚያጽናኑህን ወደ አንተ የላከ ይመስልሃልን? ባርያዎቹስ አገሪቱን ለመመርመር፥ ለማጥፋት፥ ለመሰለልም ወደ አንተ የመጡ አይደሉምን?”

4 ሐኖንም የዳዊትን ባርያዎች ወስዶ አስላጫቸው፥ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ከሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው፤

5 እነርሱም ወደመጡበት ተመለሱ። ዳዊትም በሰዎቹ ላይ የተደረገውን በነገረሩት ጊዜ ሰዎቹ እጅግ ስላፈሩ እንዲቀበሏቸው መልእክተኞችን ላከ፤ ንጉሡም፦ “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፥ ከዚያም በኋላ ተመለሱ” አለ።

6 የአሞንም ልጆች በዳዊት ዘንድ እንደ ተጠሉ ባዩ ጊዜ ሐኖንና የአሞን ልጆች ከመስጴጦምያ፥ ከአራም-መዓካ፥ ከሱባ ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ለመቅጠር አንድ ሺህ መክሊት ብር ላኩ።

7 ሠላሳ ሁለትም ሺህ ሰረገሎች የመዓካንም ንጉሥ ሠራዊት ቀጠሩ፤ መጥተውም በሜድባ ፊት ለፊት ሰፈሩ። የአሞንም ልጆች ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ወደ ውግያ መጡ።

8 ዳዊትም ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኃያላኑን ሠራዊት ሁሉ ላከ።

9 የአሞንም ልጆች ወጥተው በከተማይቱ በር አጠገብ ለውግያ ተሰለፉ፤ የመጡትም ነገሥታት ለብቻቸው በሜዳው ላይ ነበሩ።

10 ኢዮአብም ውግያው በፊትና በኋላ እንደሚደረግ ባየ ጊዜ ከእስራኤል ምርጥ ምርጦችን ሁሉ ለይቶ በሶርያውያን ላይ አሰለፋቸው።

11 የቀረውንም ሕዝብ ለወንድሙ ለአቢሳ ሰጠው፤ እነርሱም በአሞንም ልጆች ላይ ተሰለፉ።

12 እርሱም እንዲህ አለ፦ “ሶርያውያን ቢበረቱብኝ እርዳኝ፤ የአሞንም ልጆች ቢበረቱብህ እረዳሃለሁ።

13 አይዞህ፥ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ ጌታም ደስ ያሰኘውን ያድርግ።”

14 ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ለውግያ ወደ ሶርያውያን ፊት ቀረቡ፥ እነርሱም ከፊቱ ሸሹ።

15 የአሞንም ልጆች ሶርያውያን እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ገቡ። ኢዮአብም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።

16 ሶርያውያንም በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ መልእክተኞች ልከው በወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን አስመጡ፤ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሾፋክ በፊታቸው ነበረ።

17 ዳዊትም በሰማ ጊዜ እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ መጣባቸው፥ ከእነርሱም ጋር ተዋጋ፤ ዳዊትም በሶርያውያን ላይ ለውግያ በተሰለፈ ጊዜ እነርሱ ከእርሱ ጋር ተዋጉ።

18 ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት ሺህ ሰረገለኞች፥ አርባ ሺህም እግረኞች ገደለ፥ የሠራዊቱንም አለቃ ሾፋክን ገደለ።

19 የአድርአዛርም ባርያዎች በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ታረቁ፥ ገበሩለትም፤ ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ለመርዳት እንቢ አሉ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos