1 ዜና መዋዕል 18 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የንጉሥ ዳዊት መንግሥት መጽናቱና መስፋፋቱ 1 ከዚህም በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን መታ፥ አስገበራቸውም፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ጌትንና መንደሮችዋን ወሰደ። 2 ሞዓብን መታ፤ ሞዓባውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፥ ግብርም አመጡለት። 3 ዳዊትም በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውን ግዛት ለመያዝ በሄደ ጊዜ የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን እስከ ሐማት ድረስ መታ። 4 ዳዊትም ከእርሱ አንድ ሺህ ሰረገሎች፥ ሰባት ሺህም ፈረሰኞች፥ ሀያ ሺህም እግረኞች ወሰደ፤ ዳዊትም ለመቶ ሰረገሎች የሚሆኑትን ብቻ አስቀርቶ የሰረገሎቹን ፈረሶች ቋንጃ ቆረጠ። 5 ከደማስቆም ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ሊረዱ በመጡ ጊዜ ዳዊት ከሶርያውያን ሀያ ሁለት ሺህ ሰዎችን ገደለ። 6 ዳዊትም በደማስቆ ሶርያ የጦር ሠራዊት አሰፈረ፤ ሶርያውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፥ ግብርም አመጡለት። ጌታም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድል አድራጊ አደረገው። 7 ዳዊትም የአድርአዛር ባርያዎች ይሸከሟቸው የነበሩትን የወርቅ ጋሻዎች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ይዞአቸው መጣ። 8 ከአድርአዛርም ከተሞች ከጢብሐትና ከኩን ዳዊት እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ፤ ከዚህም ሰሎሞን የናሱን ኩሬና ዓምዶች የናሱንም ዕቃ ሠራ። 9 የሐማትም ንጉሥ ቶዑ ዳዊት የሱባን ንጉሥ የአድርአዛርን ሠራዊት ሁሉ ድል እንዳደረገ ሰማ። 10 ቶዑም ከአድርአዛር ጋር ሁልጊዜ ይዋጋ ነበርና ዳዊት አድርአዛርን ወግቶ ድል ስለ አደረገው ደኅንነቱን እንዲጠይቀውና እንዲመርቀው ልጁን አዶራምን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም የወርቅና የብር የናስም ዕቃ ይዞ መጣ። 11 ንጉሡም ዳዊት ከአሕዛብ ሁሉ ከኤዶምና ከሞዓብ ከአሞንም ልጆች ከፍልስጥኤማውያንም ከአማሌቅም ከማረከው ብርና ወርቅ ጋር እነዚህን ደግሞ ለጌታ ቀደሰ። 12 ደግሞ የጽሩያ ልጅ አቢሳ ከኤዶማውያን በጨው ሸለቆ ውስጥ ዐሥራ ስምንት ሽህ ሰዎች ገደለ። 13 በኤዶምያስም የጦር ሠራዊት አሰፈረ፥ ኤዶማውያንም ሁሉ ለዳዊት ገባሮች ሆኑ። ጌታም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድል አድራጊ አደረገው። የንጉሥ ዳዊት አስተዳደር 14 ዳዊትም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ፍርድንና ጽድቅን አደረገላቸው። 15 የጽሩያ ልጅ ኢዮአብም የሠራዊቱ አለቃ ነበረ፤ የአሒሉድም ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበረ። 16 የአኪጦብም ልጅ ሳዶቅ፥ የአቤሜሊክም ልጅ አብያታር ካህናት ነበሩ፤ ሱሳ ጸሐፊ ነበረ። 17 የዮዳሄ ልጅ በናያስ በከሊታውያንና በፈሊታውያን ላይ ነበረ፤ የዳዊትም ልጆች በንጉሡ አጠገብ አለቆች ነበሩ። |