Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ዜና መዋዕል 17 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


እግዚአብሔር ከንጉሥ ዳዊት ጋር ቃል ኪዳን ማድረጉ

1 እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ ዳዊት ነቢዩን ናታንን፦ “እነሆ፥ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጫለሁ፤ የጌታም ቃል ኪዳን ታቦት በድንኳን ውስጥ ተቀምጦአል” አለው።

2 ናታንም ዳዊትን፦ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና በልብህ ያለውን ሁሉ አድርግ” አለው።

3 በዚያም ሌሊት የጌታ ቃል ወደ ናታን መጣ እንዲህም አለው፦

4 “ሂድ፥ ለባርያዬ ለዳዊት እንዲህ ብለህ ንገረው፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም።

5 እስራኤልን ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከድንኳን ወደ ድንኳን፥ ከማደሪያም ወደ ማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርሁምና።

6 ከእስራኤል ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ፦ “ቤትን ከዝግባ እንጨት ለምን አልሠራችሁልኝም?” ብዬ ሕዝቤን እንዲጠብቁ ላዘዝኳቸው ለማናቸውም ለእስራኤል ፈራጆች በውኑ ተናግሬአለሁን?’

7 አሁንም ባርያዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ እንድትሆን አንተን ከማሰማርያው፥ ከበግ እረኝነት ወሰድሁህ።

8 በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፤ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆች ስም የአንተን ስም ታላቅ አደርጋለሁ።

9 ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራን እሰጠዋለሁ፥ በዚያም እተክለዋለሁ፥ በስፍራውም ይቀመጣል፥ ከዚያም በኋላ አይናወጥም፤ ከእንግዲህም ወዲያ እንደ ቀድሞው ዘመን ዓመፀኞች አያስጨንቁትም፤

10 ይህም የሆነው በእስራኤል ላይ ፈራጆች ባሥነሣሁ ጊዜ ነበር፤ ጠላቶችህንም ሁሉ በሥርህ እንዲገዙ አደርለሁ። ጌታ ደግሞ ቤት እንደሚሠራልህ እነግርሃለሁ።

11 ወደ አባቶችህም ለመሄድ ዕድሜህ በተፈጸመ ጊዜ ከልጆችህ የሚሆነውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ።

12 እርሱ ቤት ይሠራልኛል፤ ዙፋኑንም ለዘለዓለም አጸናለሁ።

13 እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ጽኑ ፍቅሬን ከአንተ በፊት ከነበረው ላይ እንደወሰድሁ ከእርሱ ላይ ከቶውንም አልወስድም።

14 በቤቴና በመንግሥቴም ለዘለዓለም አቆመዋለሁ፥ ዙፋኑም ለዘለዓለም ይጸናል።’ ”

15 ይህንን ቃል ሁሉ ይህንንም ራእይ ሁሉ ናታን ለዳዊት ነገረው።


የነጉሥ ዳዊት ጸሎት

16 ንጉሡም ዳዊት ገባ፥ በጌታም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፦ “አቤቱ አምላክ ሆይ! እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድነው?

17 አምላክ ሆይ! ይህ በፊትህ ጥቂት የሆነ ነገር ነበረ፤ አቤቱ አምላክ ሆይ! ስለ ባርያህ ቤት ደግሞ ስለ ወደ ፊቱ ሩቅ ዘመን ተናገርህ፤ እንደ አንድ ባለ ማዕረግ ሰው ተመለከትኸኝ።

18 አንተ ባርያህን ታውቀዋለህና ለባርያህ ስለተደረገው ክብር ዳዊት ጨምሮ የሚለው ምን ነገር አለው?

19 አቤቱ፥ ስለ ባርያህ ስትል እንደ ልብህ ይህን ታላቅ ነገር ሁሉ በማስታወቅ ይህን ተአምራት ሁሉ አድርገሃል።

20 አቤቱ፥ እንደ አንተ ያለ የለም፥ በጆሮአችንም እንደ ሰማን ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም።

21 አንተ እግዚአብሔር ከግብጽ ካወጣኸው ከሕዝብህ ፊት አሕዛብን በማሳደድ በታላቅና በሚያስፈራ ነገር ስምህን እንዳስጠራህ፥ ለአንተም ሕዝብ እንዲሆን ለመቤዠት እንደ ሄድህለት እንደ አንተ ሕዝብ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ሌላ ሕዝብ አለን?

22 ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘለዓለም ሕዝብህ አደረግኸው፤ አንተም፥ አቤቱ፥ አምላክ ሆነኸዋል።

23 አሁንም፥ አቤቱ፥ ስለ ባርያህና ስለ ቤቱ የተናገርኸው ቃል ለዘለዓለም የጸና ይሁን፤ እንደ ተናገርህም አድርግ።

24 ስምህ፦ ‘የሠራዊት ጌታ እርሱ የእስራኤል አምላክ ነው፥ በእውነት የእስራኤል አምላክ ነው’ በሚለው ውስጥ ለዘለዓለም ጽኑና ታላቅ ይሆናል፤ የባርያህም የዳዊት ቤት በፊትህ ጸንቶአል።

25 አምላኬ ሆይ! ቤት እንደምትሠራለት ለባርያህ ገልጠህለታልና ስለዚህ ባርያህ ወደ አንተ ለመጸለይ በልቡ ደፈረ።

26 አሁንም፥ አቤቱ፥ አንተ አምላክ ነህ፥ ይህንም መልካም ነገር ለባርያህ ተናግረሃል።

27 ስለዚህ አሁን በፊትህ ለዘለዓለም እንዲኖር የባርያህን ቤት ለመባረክ ፈቅደሃል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ አንተ የባረከው ለዘለዓለም ይባረካል።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos