1 ዜና መዋዕል 15 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ታቦቱ ወደ ኢየሩሳሌም መመለሱ 1 ዳዊትም በራሱ ከተማ ላይ ለራሱ ቤቶችን ሠራ፤ ለእግዚአብሔርም ታቦት ስፍራ አዘጋጀ፥ ድንኳንም ተከለለት። 2 በዚያን ጊዜም ዳዊት እንዲህ አለ፦ “የእግዚአብሔርን ታቦት እንዲሸከሙ፥ ለዘለዓለሙም እንዲያገለግሉት ጌታ ከመረጣቸው ከሌዋውያን በቀር ማንም የጌታን ታቦት ሊሸከም አይገባውም።” 3 ዳዊትም ወዳዘጋጀለት ስፍራ የጌታን ታቦት ለማምጣት እስራኤልን ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 4 ዳዊትም የአሮንን ልጆችና ሌዋውያን ሰበሰበ። 5 ከቀዓት ልጆች፤ ከመቶ ሀያ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ኡርኤል ነበር፤ 6 ከሜራሪ ልጆች፤ ከሁለት መቶ ሀያ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ዓሣያ ነበር፤ 7 ከጌድሶን ልጆች፤ ከመቶ ሠላሳ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ኢዮኤል ነበር፤ 8 ከኤሊጻፋን ልጆች፤ ከሁለት መቶ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ሸማያ ነበር፤ 9 ከኬብሮን ልጆች፤ ከሰማንያ ወንድሞቹ ጋር አለቃው ኤሊኤል ነበር፤ 10 ከዑዝኤል ልጆች፤ ከመቶ ዐሥራ ሁለት ወንድሞቹ ጋር አለቃው አሚናዳብ ነበር። 11 ዳዊትም ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን፥ ሌዋውያንንም ኡርኤልን፥ ዓሣያን፥ ኢዮኤልን፥ ሸማያን፥ ኤሊኤልን፥ አሚናዳብንም ጠራቸው፤ 12 እነርሱንም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የሌዋውያን አባቶች ቤቶች አለቆች ናችሁ፤ ወዳዘጋጀሁለት ስፍራ የእስራኤልን አምላክ የጌታን ታቦት እንድታመጡ እናንተና ወንድሞቻችሁ ተቀደሱ። 13 ቀድሞም አልተሸከማችሁትምና፥ እንደ ሥርዓቱም አልፈለግነውምና ጌታ አምላካችን በመካከላችን ቊጣውን አወረደ።” 14 የእስራኤልንም አምላክ የጌታን ታቦት ለማምጣት ካህናቱና ሌዋውያኑ ተቀደሱ። 15 ሙሴም እንዳዘዘው እንደ ጌታ ቃል የሌዋውያን ልጆች የእግዚአብሔርን ታቦት በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎቹ ተሸከሙ። 16 ዳዊትም በዜማ ዕቃ በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም እንዲያዜሙ፥ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ እንዲያደርጉ መዘምራኑን ወንድሞቻቸውን እንዲሾሙ ለሌዋውያን አለቆች ተናገረ። 17 ሌዋውያኑም የኢዮኤልን ልጅ ኤማንን፥ ከወንድሞቹም የበራክያን ልጅ አሳፍን፥ ከወንድሞቻቸውም ከሜራሪ ልጆች የቂሳን ልጅ ኤታንን ሾሙ፤ 18 ከእነርሱም ጋር በሁለተኛው ደረጃ ያሉትን ወንድሞቻቸውን ዘካርያስን፥ ቤንን፥ ያዝኤልን፥ ሰሚራሞትን፥ ይሒኤልን፥ ዑኒን፥ ኤልያብን፥ በናያስን፥ መዕሤያን፥ መቲትያን፥ ኤሊፍሌሁን፥ ሚቅኔያን፥ ደጁንም የሚጠብቁትን ዖቤድ-ኤዶምንና ይዒኤልን ሾሙ። 19 መዘምራንም የነበሩት ኤማንና አሳፍ ኤታምንም የናሱን ጸናጽል ድምፅ ከፍ አድርገው ያሰሙ ነበር። 20 ዘካርያስ፥ ዓዝዔል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ ዑኒ፥ ኤልያብ፥ መዕሤያ፥ በናያስ በመሰንቆ ምሥጢር ነገር ያዜሙ ነበር። 21 መቲትያ፥ ኤልፍሌሁ፥ ሚቅኔያ፥ ዖቤድ-ኤዶም፥ ይዒኤል፥ ዓዛዝያ ስምንት አውታር ባለው በገና ይዘምሩ ነበር። 22 የሌዋውያኑም አለቃ ክናንያ ዜማን አዋቂ ስለ ነበር ዜማውን እንዲመራ ተሾሞ ነበር። 23 በራክያና ሕልቃናም የታቦቱን እልፍኝ ጠባቂዎች ነበሩ። 24 ካህናቱም ሰበኒያ፥ ኢዮሣፍጥ፥ ናትናኤል፥ ዓማሣይ፥ ዘካርያስ፥ በናያስ፥ አልዓዛር በእግዚአብሔር ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር። ዖቤድ-ኤዶምና ይሒያም የታቦቱን እልፍኝ ጠባቂዎች ነበሩ። 25 ዳዊትም፥ የእስራኤልም ሽማግሌዎች፥ የሻለቆችም የጌታን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከዖቤድ-ኤዶም ቤት በደስታ ለማምጣት ሄዱ። 26 የጌታንም ቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙትን ሌዋውያንን እግዚአብሔር ስለረዳቸው ሰባት በሬዎችና ሰባት አውራ በጎች ሰዉ። 27 ዳዊትም፥ ታቦቱንም የተሸከሙ ሌዋውያን ሁሉ፥ መዘምራኑም፥ የመዘምራኑም አለቃ ከናንያ የጥሩ በፍታ ቀሚስ ለብሰው ነበር፤ ዳዊትም ኤፉድ ያለበት በፍታ ለብሶ ነበር። 28 እንዲሁ እስራኤል ሁሉ ሆ እያሉ፥ ቀንደ መለከትና እምቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽልና መሰንቆም በገናም እየመቱ፥ የጌታን የቃል ኪዳን ታቦት አመጡ። 29 የጌታም ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በደረሰ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡም ዳዊት ሲያሸበሽብና ሲዘል አይታ በልብዋ ናቀችው። |