1 ዜና መዋዕል 11 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)በእስራኤል ላይ ዳዊት መንገሡ 1 እስራኤልም ሁሉ በኬብሮን ወደ ዳዊት ተሰብስበው እንዲህ አሉት፦ “እነሆ፥ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቁራጭ ነን፤ 2 አስቀድሞ ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስራኤልን የምታወጣና የምታገባ አንተ ነበርህ፤ ጌታ አምላክህም፦ ‘ሕዝቤን እስራኤልን አንተ ትጠብቃለህ፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።” 3 የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትም በኬብሮን በጌታ ፊት ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደረገ፤ በሳሙኤልም አንደበት እንደ ተናገረው እንደ ጌታ ቃል በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን ዳዊትን ቀቡት። ኢየሩሳሌም መያዝዋ 4 ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ ኢያቡስ ወደምትባል ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፤ በአገሩም የተቀመጡ ኢያቡሳውያን በዚያ ነበሩ። 5 በኢያቡስም የተቀመጡ ዳዊትን፦ “ወደዚህ አትገባም” አሉት፤ ዳዊት ግን አምባይቱን ጽዮንን ያዘ፤ እርሷም የዳዊት ከተማ ናት። 6 ዳዊትም፦ “ኢያቡሳውያንን አስቀድሞ የሚመታ ሰው አለቃና መኮንን ይሆናል” አለ። የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ አስቀድሞ ወጣ አለቃም ሆነ። 7 ዳዊትም በአምባይቱ ውስጥ ተቀመጠ፤ ስለዚህም የዳዊት ከተማ ብለው ጠሩአት። 8 ከሚሎም ጀምሮ በዙሪያው ከተማ ሠራ፤ ኢዮአብም የቀረውን ከተማ አደሰ። 9 ዳዊትም የሠራዊት ጌታ ከእርሱ ጋር ነበረና እየበረታ ሄደ። የንጉሥ ዳዊት ኃያላን ሰዎችና ተገዢዎቻቸው 10 ለዳዊትም የነበሩት የኃያላን አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ስለ እስራኤል እንደ ተናገረው እንደ ጌታ ቃል ሊያነግሡት ከእስራኤል ሁሉ ጋር በመንግሥቱ ላይ አጸኑት። 11 የዳዊትም ኃያላን ቍጥር ይህ ነበረ፤ የሦስቱ ኃያላን አለቃ የሐክሞናዊው ልጅ ያሾብዓም ነበረ፤ እርሱ ጦሩን አንሥቶ ሦስት መቶ ሰው በአንድ ጊዜ ገደለ። 12 ከእርሱም በኋላ በሦስቱ ኃያላን መካከል የነበረ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ አልዓዛር ነበረ። 13 እርሱ ከዳዊት ጋር በፈስደሚም ነበረ፥ በዚያም ገብስ በሞላበት እርሻ ውስጥ ፍልስጥኤማውያን ለውጊያ ተሰብስበው ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ። 14 እርሱና ዳዊት በእርሻውም መካከል ጸንተው ቆሙ፤ ስፍራውንም አላስደፈሩም፥ ፍልስጥኤማውያንንም ገደሉ፤ ጌታም በታላቅ ድል አድራጊነት አዳናቸው። 15 ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው ዳዊት ወዳለበት ወደ ዓለቱ ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ፤ የፍልስጥኤማውያንም ሠራዊት በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። 16 በዚያም ጊዜ ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በቤተልሔም ነበረ። 17 ዳዊትም፦ “በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ማን ይሰጠኛል?” ብሎ ተመኘ። 18 እነዚህም ሦስቱ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት በመካከላቸው ጥሰው አለፉ፥ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ቀዱ፤ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን ሊጠጣ አልፈለገም፥ ነገር ግን ለጌታ እንደ መባ አፈሰሰው፤ 19 እርሱም እንዲህ አለ፦ “ይህን እንዳደርግ አምላኬ አይፈቅድልኝም፤ በነፍሳቸው የደፈሩትን የእነዚህን ሰዎች ደም እጠጣለሁን? ነፍሳቸውን አደጋ ላይ ጥለው አምጥተውታል።” ስለዚህም ሊጠጣው አልፈለገም። ሦስቱም ኃያላን ያደረጉት ይህ ነው። 20 የኢዮአብም ወንድም አቢሳ የሦስቱ አለቃ ነበረ፤ ጦሩንም በሦስት መቶ ላይ አንሥቶ ገደላቸው፥ በሦስቱም መካከል ስሙ የተጠራ ነበረ። 21 በሁለተኛውም ተራ በሆኑት በሦስቱ መካከል የከበረ ነበረ፥ አለቃቸውም ሆነ፤ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ ደረጃ አልደረሰም ነበር። 22 በቀብስኤልም የነበረው፥ ታላቅ ሥራ ያደረገው የጽኑዕ ሰው የዮዳሄ ልጅ በናያስ የሞዓባዊን የአሪኤልን ሁለቱን ልጆች ገደለ፤ በአመዳይም ወራት ወርዶ በጉድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ። 23 ቁመቱም አምስት ክንድ የነበረውን ረጅሙን ግብጻዊውን ሰው ገደለ፤ በግብጻዊውም እጅ የሸማኔ መጠቅለያ የመሰለ ጦር ነበረ፤ እርሱ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፥ ከግብፃዊው እጅ ጦሩን ነጠቀው፥ በገዛ ጦሩም ገደለው። 24 የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፤ ስሙም በሦስቱ ኃያላን መካከል የተጠራ ነበረ። 25 እነሆ፥ ከሠላሳው ይልቅ የከበረ ነበረ፥ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም በዘበኞቹ ላይ ሾመው። 26 ደግሞም በሠራዊቱ ዘንድ የነበሩት ኃያላን እነዚህ ናቸው፤ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ የቤተልሔሙ ሰው የዱዲ ልጅ ኤልያናን፥ 27 ሃሮራዊው ሳሞት፥ ፈሎናዊው ሴሌስ፥ 28 የቴቁሔ ሰው የዒስካ ልጅ ዒራስ፥ ዓናቶታዊው አቢዔዜር፥ 29 ኩሳታዊው ሴቤካይ፥ አሆሃዊው ዔላይ፥ 30 ነጦፋዊው ኖኤሬ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌድ፥ 31 ከብንያም ወገን ከጊብዓ የሪባይ ልጅ ኤታይ፥ ጲርዓቶናዊው በናያስ፥ 32 የገዓስ ወንዝ ሰው ኡሪ፥ ዓረባዊው አቢኤል፥ 33 ባሕሩማዊው ዓዝሞት፥ ሰዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥ 34 የጊዞናዊው የአሳን ልጆች፥ የሃራራዊው የሻጌ ልጅ ዮናታን፥ 35 የአሮዳዊው የአራር ልጅ አምናን፥ የኡር ልጅ ኤሊፋል፥ 36 ምኬራታዊው ኦፌር፥ ፍሎናዊው አኪያ፥ 37 ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፥ የኤዝባይ ልጅ ነዕራይ፥ 38 የናታንም ወንድም ኢዮኤል፥ የሃግሪ ልጅ ሚብሐር፥ 39 አሞናዊው ጼሌቅ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ ቤሮታዊው ነሃራይ፥ 40 ይትራዊው ዒራስ፥ ይትራዊው ጋሬብ፥ 41 ኬጢያዊው ኦርዮ፥ የአሕላይ ልጅ ዛባድ፥ 42 የሮቤላዊው የሺዛ ልጅ ዓዲና፥ እርሱ የሮቤላውያን አለቃ ነበረ፥ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሰዎች ነበሩ፥ 43 የማዕካ ልጅ ሐናን፥ ሚትናዊው ኢዮሣፍጥ፥ 44 አስታሮታዊው ዖዝያ፥ የአሮዔራዊው የኮታም ልጆች ሻማና ይዒኤል፥ 45 የሺምሪ ልጅ ይዲኤል፥ ወንድሙም ቲዳዊው ዮሐ፥ 46 መሐዋዊው ኤሊኤል፥ ይሪባይ፥ ዮሻውያ፥ የኤልነዓም ልጆች፥ ሞዓባዊው ይትማ፥ 47 ኤሊኤል፥ ዖቤድ፥ ምጾባዊው የዕሢኤል ነበሩ። |