ብዙ ወራትም ካለፈ በኋላ ሚስቱ እንዲህ አለችው፥ “እስከ መቼ ትታገሣለህ? 9 ‘ሀ’ ዳግመኛም እግዚአብሔርን ጥቂት ወራት ደጅ እጠናዋለሁ፤ ዳግመኛም መከራውን እታገሠዋለሁ፤ የቀድሞው ኑሬዬንም ተስፋ አደርገዋለሁ ትላለህን? 9 ‘ለ’ እንደዚህስ እንዳትል ከዚህ ዓለም እነሆ ስም አጠራርህ ጠፋ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቼም ሞቱ፥ ማኅፀኔም በምጥ ተጨነቀ፥ በከንቱም ደከምሁ። 9 ‘ሐ’ አንተም በመግልና በትል ትኖራለህ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ትዛብራለህ። 9 ‘መ’ እኔ ግን እየዞርሁ እቀላውጣለሁ። ከአንዱ መንደር ወደ አንዱ መንደር፥ ከአንዱ ቤትም ወደ አንዱ ቤት እሄዳለሁ፤ ከድካሜና በእኔ ላይ ካለ ችግሬም ዐርፍ ዘንድ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ እጠብቃለሁ፤ ነገር ግን አሁን እግዚአብሔርን ስደብና ሙት።”
