La Biblia Online

Anuncios

Toda la Biblia A.T. N.T.


መጽሐፈ ሲራክ 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
መጽሐፈ ሲራክ 7

ልዩ ልዩ ምክሮች

1 ክፉ ነገር አታድርግ፥ ክፉ ነገር አይደርስብህም።

2 ከበደል ራቅ፥ በደል ካንተ ይርቃል።

3 ልጄ ሆይ በግፍ ትልሞች አትዝራ፥ ሰባት ጊዜ እጥፍ ታጭዳቸዋለህና።

4 ከእግዚአብሔር ታላቅ ሥልጣንን፥ ከንጉሥ የክብር መንበርን አትጠይቅ፤

5 በእግዚአብሔር ፊት አትመጻደቅ፤ በንጉሡም ፊት ጥበበኛ ነኝ አትበል።

6 በዳኝነት ለመመረጥ አታስብ፥ የፍትሕን መዛባት ላታስወግድ ትችላለህና፤ ምክንያቱም ሹም ተፅዕኖ ሊያደርግብህ ይችላል፤ የአንተም ሐቀኛነት አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል።

7 የአገርህን ሰዎች አትበድል፤ በሕዝብህም ፊት ራስህን አታዋርድ።

8 በድጋሚ አትበድል፤ ስለ አንዱም ቢሆን ከቅጣት አታመልጥምና፤

9 “እግዚአብሔር ብዙ መሥዋዕቶቼን ይመለከትልኛል፤ ለልዑል እግዚአብሔር ሳቀርባቸው ይቀበላቸዋል” አትበል።

10 በጸሎትህ አታመንታ፤ መመጽወትንም አትዘንጋ፤

11 በመራራ ችግር ላይ በሚገኝ ሰው ከቶ አትሳቅ፤ ዝቅ ያደረገ አምላክ ከፍ ያደርጋልና።

12 በወንድምህ ላይ ውሸትን ፈጥረህ አትናገር፤ በወዳጅህም ላይ እንደዚሁ አታድርግ።

13 ምንም ጊዜ ከውሸት ተጠንቀቅ፤ ከውሸት ምንም ደግ ነገር አይገኝምና።

14 በሽማግሌዎች ስብሰባ ላይ ንግግር አታብዛ፤ በጸሎትህ ቃሎችህን አትደጋግም።

15 አድካሚ ሥራን አትጥላ፤ በልዑል እግዚአብሔር የተደነገገውን የእርሻ ሥራ አትጥላ።

16 ከኃጢአተኞች ጐራ አትደባለቅ፤ የእግዚአብሔር ቁጣ የማይዘገይ መሆኑን አስታውስ።

17 ራስህን በጣም ዝቅ አድርግ፤ ምክንያቱም የክፉ ሰው ቅጣቱ እሳትና ትል ነው።

18 ለገንዘብ ስትል ወዳጅህን፥ ለኦፊር ወርቅ ብለህ እውነተኛ ወንድምህን አትለውጥ።

19 በጥበበኛዋና በመልካም ሚስትህ ላይ ፊትህን አትመልስ፤ የእርሷ ሞገስ ከወርቅ ይበልጣልና።

20 በታማኝነት የሚሠራውን አገልጋይ፥ ወይም ልቡ ወደ ሥራ ያዘነበለውን የዕለት ሠራተኛ አትበድል።

21 አስተዋዩን አገልጋይህን ከልብህ ውደደው፤ ነጻነቱንም አትንፈገው። ልጆች

22 የከብት መንጋዎች አሏችሁን? ጠብቋቸው፤ ትርፉንም ካስገኙላችሁ በሚገባ ያዟቸው፤

23 ልጆች አሉህን? አስተምራቸው፤ ከልጅነታቸው ጀምረህ አንገታቸውን እንዲደፉ አድርግ።

24 ሴቶች ልጆች አሉህን? ሰውነታቸውን ተከባከብ፤ ይሁን እንጂ አታሞላቃቸው።

25 ልጅህን ዳራት፥ ያኔም ታላቅ ሥራ ሠራህ። የምትድራት ግን ላስተዋይ ይሁን። ወላጆች

26 በልብህ የምትወዳት ሚስት አለችህን? አታባራት፤ የማትወዳት ከሆንህ ግን አትመናት።

27 በሙሉ ልብህ አባትህን አክብር፤ የእናትህን የምጥ ስቃይ አትርሳ።

28 አንተን የወለዱህ መሆናቸውን አትርሳ፤ ላንተ ያደረጉልህን እንዴት አድርገህ ትመልስላቸዋለህ?

ካህናት

29 በሙሉ ልብህ እግዝአብሔርን ፍራ፤ የሱን ካህናትም አክብር።

30 በሙሉ ኃይልህ የፈጠረህን ውደድ፤ የሱን አገልጋዮችንም ቸል አትበል፤

31 እግዚአብሔርን ፍራ፤ ካህንን አክብር፤ እንደታዘዝኸው ድርሻውን ስጠው፤ የምትሰጠውም ከእህሉ የመጀመሪያውን ስለ ኃጢአት ካሣ የሚሠዋውን መሥዋዕት፥ ወርቹን፥ የመቀደሻውን መሥዋዕት ከተቀደሱት ነገሮች የመጀመሪያውን ነው።

የተቸገሩና የተጨነቁ ሰዎች

32 በረከትህ ፍጹም እንዲሆን ለድሆች እጅህን ዘርጋ።

33 ደግነትህ ለሕያዋን ሁሉ ይድረስ፤ ለሞቱት እንኳ ከምታደርገው አትታቀብ።

34 በሚያለቅሱ ላይ ጀርባህን አታዙር፤ የኀዘንተኞችን ኀዘን ተጋራ፤

35 በሽተኞችን ከመጠየቅ ወደ ኋላ አትበል፤ እንዲህ ያለ ሥራ በመሥራትህ ተወዳጅ ትሆናለህ።

36 በሥራህ ሁሉ መጨረሻህን አስታውስ፤ በኃጢአትም ከቶውን አትወድቅም።