La Biblia Online

Anuncios

Toda la Biblia A.T. N.T.


1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 10 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 10

ስክንድር ባላስ የዮናታንን ድጋፍ ለማግኘት ጣረ፤ ሊቀ ካህናትም አድርጐ መረጠው

1 በመቶ ስልሳ ዓመተ ዓለም የአንጥዮኩስ ልጅ እስክንድር ኤጲፋኔስ መጥቶ ጰጠሎማይዳን ያዘ፤ ሰዎቹ ተቀበሉት፤ ከዚያም ነገሠ።

2 ይህን በሰማ ጊዜ ንጉሥ ዲመትሪዮስ እጅግ ብዙ ሠራዊት ሰብስቦ እርሱን ለመውጋት ወደ እርሱ ሄደ።

3 ከዚህም ሌላ በእርቅ የተሞላና ዮናታንንም ለከፍተኛ ማዕረግ እንደሚያበቃው የሚያረጋግጥ ቃል የያዘ ደብዳቤ ላከ፤

4 “በእኛ ላይ ከእስክንድር ጋር የሰላም ንግግር ከማድረጉ በፊት እኛ በፍጥነት ከሱ ጋር የሰላም ንግግር እናድርግ፤

5 ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በእርሱ ላይና በወንድሞቹ ላይ እንዲሁም በሕዝቡ ላይ ያደረግነውን ክፉ ነገር ሊያስብ ይችላል” በማለትም አሳሰበ።

6 እንዲያውም ሠራዊት እንዲያሰባስብ፤ የጦር መሣሪያ እንዲሠራ፥ የጦር ጓደኛው ነኝ እንዲል ሥልጣን ሰጠው፤ በኢየሩሳሌም ምሽግ ውስጥ በዋስትና የተያዙበት ሰዎች እንዲመለሱለትም አዘዘ።

7 ዮናታን ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ በሕዝቡ ሁሉና በምሽጉ ውስጥ በነበሩት ሰዎች ሁሉ ፊት መልእክቱን አነበበ።

8 ንጉሡ ለዮናታን ሠራዊት እንዲሰበሰብ ሥልጣን መስጠቱን በሰሙ ጊዜ ሰዎቹ በጣም ፈሩ።

9 የኢየሩሳሌም ምሽግ ሰዎች በዋስትና የተያዙትን ሰዎች ለዮናታን አስረከቡ፤ እሱም እነርሱን ለቤተሰቦቻቸው አስረከባቸው።

10 ዮናታን በኢየሩሳሌም የተቀመጠ፤ ከተማዋን እንደገና መገንባት ጀመረ።

11 ሥራውን ለሚሠሩት ሰዎች ግንቡን እንዲገነቡና የጽዮንን ተራራ በጥርብ ድንጋይ ዙሪያዋን እንደከቧት ትእዛዝ ሰጣቸው፤ እነርሱም እንደ ትእዛዙ አደረጉ።

12 ባቂደስ ባሠራቸው ምሽጐች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የሌላ አገር ሰዎች ሸሽተው ሄዱ።

13 እያንዳንዱ ሰው ወደየአገሩ ለመመለስ ቦታውን ተወ።

14 ሕግንና ትእዛዝን ጥሰው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች በቤተሱር ብቻ እንዲቀሩ ተውአቸው፤ ምክንያቱም እርሱ የመጠጊያ ቦታ ነበረ።

15 ዲመትሪዮስ ለዮናታን የላከለትን የተስፋ ቃል ንጉሥ እስክንድር አወቀ። እንዲሁም ዮናታንና ወንድሞቹ ያደረሱባቸወም መከራዎች ተነገረው።

16 “ከቶ እንዲህ ያለ ሰው እናገኛለን? ከዛሬ ጀምሮ እርሱን ወዳጅና የጦር ጓደኛ ማድረግ ያስፈልገናል” አለ።

17 ስለዚህ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፈለት፤

18 “ንጉሥ እስክንድር ለወንድሙ ለዮናታን ሰላምታ ያቀርባል።

19 አንተ ጀግናና የኛ ወዳጅ ለመሆን ብቁ መሆንህን ሰምተናል፤

20 ስለዚህ ከዛሬ ቀን ጀምሮ የሕዝብህ ሊቀ ካህናት እንድትሆን ሾመንሃል፤ የእኛ ወገን እንድትሆንና ከእኛ ጋር ያለህን ወዳጅነት እንድትጠብቅ ‘የንጉሥ ወዳጅ’ የሚል ስም ሰጥተንሃል።” ለዮናታን የከፋይ ልብስና የወርቅ አክሊል በመላክ አከበረው። “በዚህም መሠረት ፍላጎታችንና ወንድማዊ ግንኙነታችንን እንድታውቅና እንድታጠናክርም እንፈልጋለን”።

21 ዮናታን በሰባተኛው ወር በመቶ ስልሳ ዓመት (ጥቅምት) 15 2 ዓ.ዓ. (በዳስ) በዓል ጊዜ ቅዱሱን ልብስ ለበሰ፤ ወዲያውኑ ሠራዊቱን ለማሰባሰብና መሣሪያ ለመሥራት ተነሣ።

ለዮናታን የተላከ የንጉሥ ዲሜጥሮስ ደብዳቤ

22 ዲሜጥሮስ ይህን በሰማ ጊዜ አዘነ፤

23 “እስክንድር የአይሁዳውያኑን ወዳጅነት ቀድሞ በማግኘት አቋሙን ያጠናከረውና እቅዳችንንም ያሰናከለው ምን ብናደርገው ይሆን?

24 እኔም ብሆን እድገትና ሀብትን አስገኝላችኋለሁ በሚል የእነርሱን ድጋፍ ማግኘት አለብኝ” በማለት ተናገረ። በመቀጠልም

25 እንዲህ ሲል ጻፈላቸው፥ “ንጉሥ ዲሜጥሮስ ለአይሁድ ሕዝብ ሰላምታ ያቀርባል፤

26 በእኛ መካከል የተደረገውን ውል እናንተ ሁልጊዜ አጽንታችሁ ይዛችኋል፤ የእኛ ወዳጆች ሆናችሁ ቀርታችኋል፤ ወደ ጠላቶቻችን አልሄዳችሁም፤ ይህን ሁሉ አውቀናል፤ ስለዚህም ደስ ብሎናል።

27 ለእኛ ታማኞች መሆናችሁን ቀጥሉ፤ ስለታማኝነታችሁ መልካም ነገሮች እናደርግላችኋለን።

28 ከቀረጥ ነጽ እናውጣችኋለን፤ ልዩ መብቶችን እንሰጣችኋለን።

29 ከዛሬ ጀምሮ እንግዲህ ነጻ አውጥቻችኋለሁ፤ አይሁዳውያንን በሙሉ በቀረጥ ከጨው ግብር፥ ከዘውድ ግብር ነጻ አውጥቻለሁ።

30 በሌላ በኩል ከዛሬ ጀምሮ ከመሬት ፍሬ የሚሰጠውን ሲሶ ለሁልጊዜ ትቻለሁ፤ ከዛፎች ፍሬ የሚደርሰኝንም እኩሌታ ትቻለሁ፤ ይህን ያደረግሁት ለይሁዳ አገርና ከሰማርያና ከገሊላ ለተጨመሩለት ለሦስቱም አገሮች ነው።

31 ኢየሩሳሌም ቅድስትና ነጻ ትሆናለች፤ እንዲሁም የእርሷ ምድር ከአሥራትና ከግብር ነጻ ይሆናል።

32 የኢየሩሳሌምንም ምሽግ እለቃለሁ፤ ኢየሩሳሌምን ለሊቀ ካህናቱ ትቼለታለሁ፤ እርሱ የሚጠብቋን ሰው መርጦ እዚያ ማድረግ ይችላል።

33 በመንግሥቴ ውስጥ የትም ቦታ ይሁን ከእሁዳ አገር ተማርኮ የመጣ አይሁዳዊ ሁሉ ምንም ሳይከፍል ነፃ እንዲሆን አድርጌዋለሁ፤ ሁሉም ከግብር ነፃ ይሁኑ፤ የተያዘባቸውም እንስሳ ነፃ ይውጣ፤

34 የበዓል ቀኖች ሁሉ፤ የሰንበት ቀኖች፤ የመጀመሪያ ጨረቃ ቀኖች፤ የትእዛዝ በዓላት ቀኖች፤ እንዲሁም ከበዓል በፊት ያሉት ሦስት ቀኖችና ከበዓል በኋላ ያሉት ሦስት ቀኖች በመንግሥቴ ለሚገኙ አይሁዳውያን ሁሉ ግብር የማይከፈልባቸው ነጻ ቀኖች ይሆናሉ።

35 ማንም እነርሱን ለማስከፈል ወይም በምንም ዓይነት እነርሱን ለማስቸገር ሥልጣን አይኖረውም።

36 አይሁዳውያን በንጉሡ ሠራዊት ውስጥ እስከ ሠላሳ ሺህ ወታደሮች ተመልምለው ሊገቡ ይችላሉ፤ ለመንግሥት ሠራዊት ሁሉ የሚከፈለው ደሞዝ ይከፈላቸዋል።

37 አንዳንዶቹ በታላላቅ መንግሥት ምሽጐች ውስጥ ይሆናሉ። አይሁዳውያን በመንግሥት ታማኝነት ቦታ ላይ ይሰማሉ፤ መሪዎቻቸውና አለቆቻቸው ከነእርሱ ውስጥ ይመረጣሉ፤ ንጉሡ በይሁዳ አገር ውስጥ እንዳዘዘው በሕጋቸው መሠረት ይተዳደራሉ።

38 ከሰማርያ ተወስደው ለይሁዳ አገር የተጨመሩት ሦስቱ አገሮች ከይሁዳ አገር ጋር ይሁኑ፤ በአንድ አለቃ ሥር ብቻ ይሁኑ፤ ለሊቀ ካህናት ብቻ እንጂ ለሌላ ባሥልጣን አይታዘዙ።

39 አምልኮ የማያስፈልገውን ገንዘብ ለመሸፈን እንዲቻል ለኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ጰጦሌማይዳንና አካባቢዋን ሰጥቻለሁ።

40 እኔም ከግብር ከማገኘው ድርሻዬ በየዓመቱ ዐሥራ አምስት ሺህ ብር እሰጣለሁ።

41 መጋቢወች እንዳለፉት ዓመታት ሳይከፍሉ ያስቀሩትን ሁሉ ከዛሬ ጀምሮ ለቤተ መቅደሱ ሥራዎች እንዲውል ይሰጣሉ።

42 ከዚህም በላይ በየዓመቱ ከቤተ መቅደስ ይወሰድ የነበረው አምስት ሺህ ብር በአገልግሎት ላይ ላሉት ካህናት ይሆናል።

43 ለንጉሥ መክፈል በሚገባቸው ነገር ወይም በሌላ ጉዳይ ምክንያት በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስና በአካባቢዎቹ የሙጥኝ ያሉ ሁሉ በመንግሥቴ ውስጥ ካላቸው ንብረት ሁሉ ጋር ነጻ ይሆናሉ።

44 ለቤተ መቅደሱ ማሠሪያና ማደሻ የሚወጣው ገንዘብ ከንጉሡ ግምጃ ቤት ወጪ ይሆናል።

45 ግንቦቹን እንደገና ለማሠራትና የኢየሩሳሌምንም መካበቢያ ዳግም ለመገንባት በይሁዳ አገር ያሉትንም ግንቦች ለማሠራት የሚያስፈልገው ወጪ ከንጉሡ ሒሳብ ወጪ ያደረጋል”።

ዮናታን የንጉሥ ዲሜጥሮስን ስጦታ ሳይቀበል ቀረ፤ የንጉሥ ዲሜጥሮስ ዜና እረፍት

46 ዮናታንና ሕዝቡ እነዚህን ቃሎች በሰሙ ጊዜ አናምንም ቃሎቹንም አንቀበልም አሉ፤ ምክንያቱም ዲሜጥሮስ በእስራኤል ላይ ያደረገው ክፉ ነገር ሁሉና በነእርሱ ላይ የፈጸመው ከባድ ጭቆና ገና ከአሳባቸው አልጠፋም ነበር።

47 ከሁለቱ ምርጫዎች መካከል የተሻለ ሆኖ ያገኙትን የንጉስ እስክንድርን ቃል ለመቀበል ወሰኑ፤ ከጐኑም ተሰለፉ።

48 ንጉሥ እስክንድር ብዙ ሠራዊት ሰብስቦ በዲሜጥሮስ ላይ ለመዝመት ተነሣ።

49 ሁለቱ ነገሥታት ሲዋጉ የዲሜጥሮስ ሠራዊት ሸሸ፤ እስክንድር ተከታተለውና አሸነፈው፤

50 ጦርነቱን በወኔ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ቀጠለ፤ በዚያኑ ቀን ዲሜጥሮስ ሞተ፤

የዮናታን ገዥነትና የጦር እልቅና፤ የንጉሥ እስክንድር እና ኪሊዮጳጥራ ጋብቻ

51 እስክንድር ወደ ግብጽ ንጉሥ ጰጠሎሜዮስ እንዲህ ሲል መልእክተኛ ላከ፤

52 “እነሆ ወደ መንግሥቴ ተመልሼ በአባቶቼ ዙፋን ላይ ከተቀመጥኩ በኋላ ዲሜጥሮስን ከወታደሮች ጋር አሸፌ ዙፋኑን ይዣለሁ።

53 ከእርሱ ጋር ውጊያ አድርገን እርሱንና ሠራዊቱን በፍጹም ደምስሰናል፤ የእርሱን ንጉሣዊ ዙፋን ይዘናል።

54 አሁን እንግዲህ ወዳጆች እንሁን፤ ከዛሬ ጀምሮ ሴት ልጅህን በሚስትነት ስጠኝ፤ አማችህ እሆናለሁ፤ ለአንተም ሆነ ለእርሷ የተገባውን እጅ መንሻ አቀርባለሁ”።

55 ንጉሥ ጰጠሎሜዮስ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ወደ አባትህ አገር የገባህበትና በንጉሣዊ ዙፋን ላይ የተቀመጥህበት ቀን የተባረከ ነው፤

56 አሁንም በጽሑፉ የገለጽህልኝን አደርግልሃለሁ፤ ግን እንድነነጋገር ወደ ጰጠሎማይዳ ወጥተህ እንድንገናኝ ይሁን፤ እንዳልኸው አማችህ እሆናለሁ።”

57 ጰጠሎሜዮስ ከሴት ልጁ ከኪሊዮጳጥራ ጋር ከግብጽ ተነሥቶ በመቶ ስልሳ ሁለት ዓመተ ዓለም ወደ ጰጠሎማይዳ መጣ፤

58 ንጉሥ እስክንድርም ጰጠሎሜዮስን ለመቀበል መጣ፤ ለነገሥታት መደረግ እንደሚገባው ጰጠሎሜዮስ ልጁን ኪሊዮጳጥራን ሰጠውና በጰጠሎማይዳ ታላቅ በዓል አደረገ።

59 ንጉሥ እስክንድር ለዮናታን መጥቶ እንደገናኘው ጻፈለት።

60 ዮናታን በታላቅ ክብር ወደ ጰጠሎማይዳ ሄደ፤ ከሁለቱ ነገሥታት ጋር ተገናኘ፤ ለእነርሱና ለወዳጆቻቸውም ብርና ወርቅ፤ ብዙ እጅ መንሻም አቀረበ።

61 ሃይማኖት የሌላቸውና ሕግን የማያከብሩ የእስራኤል በሽታ የሆኑ ሰዎች በእርሱ ላይ ተነሡበትና በንጉሡ ፊት ቀርበው ከሰሱት፤ ንጉሡ ግን ክሳቸውን አልተቀበላቸውም።

62 እንዲያውም የዮናታንን ልብስ አውልቀው ከፋይ እንዲያለብሱት አዘዘ፤ እንዲሁም ተደረገ።

63 ንጉሡ በአጠገቡ አስቀመጠውና ሹማምንቱን እንዲህ አላቸው፤ “ከእርሱ ጋር አብራችሁ ወደ ከተማ መሀል ሂዱ፤ በምንም ዓይነት ምክንያት ማንም እንዳያስቸግረው አሳውጁለት”።

64 በንጉሡ አዋጅ መሠረት የተሰጠውን ክብርና የለበሰውን ከፋይ ባዩ ጊዜ ሐሜተኞቹ ሁሉ ሸሽተው ሄዱ።

65 ንጉሡ ክሱ ከመጀመሪያዎቹ ወዳጆቹ መካከል እንዲጻፍ አደረገው፤ የጦር መሪና የክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ አደረገው፤

66 ዮናታን በሰላም፤ በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

ዳግማዊ ዲሜጥሮስ፥ የቀለሶርያ ገዥ አጶሎንዮስ በዮናታን ድል መመታት

67 በመቶ ሰላሳ አምስት ዓመተ ዓለም ዲሜጥሮስ (2ኛው) የዲሜጥሮስ (1ኛው) ልጅ ከቀርጤስ ወደ አባቶቹ አገር መጣ።

68 ንጉሥ እስክንድር ይህን በሰማ ጊዜ በጣም አዝኖ ወደ አንጾኪያ ተመልሶ መጣ፤

69 አጶሎንዮስ የቀለሶርያ አስተዳዳሪ እንዲሆን ዲሜጥሮስ አጸናለት፤ አጶሎንዮስም ብዙ ሠራዊት ሰብስቦ በያምንያ አጠገብ መጣና ሠፈረ፤ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ዮናታንም እንዲህ ሲል ላከ፤

70 “በእኛ ላይ የተነሣህ በእውነት አንተ ብቻ ነህ፤ በአንተ ምክንያት እነሆ እኔ መሳቂያና ማላገጫ ሆኛለሁ፤ አንተ በተራራ ላይ ሆነህ ሥልጣንህን በእኛ ላይ ደረረግኸው ስለምንድነው?

71 በሠራዊትህ የምትተማመን ከሆንህና ከእንግዲህ አሁን ወደ ሜዳው ውረድ፤ እዚያ እኔና አንተ እንፈታተናለን፤ ምክንያቱም የከተማዎቹ ኃይል ከእኔ ጋር ነው።

72 እኔ ማን መሆኔንና የሚረዱኝም ሰዎች ማን መሆናቸውን ጠይቀህ ተረዳ፤ ከዚህ ቀደም አባቶችህ በገዛ አገራቸው ላይ ሁለት ጊዜ ተሸንፈዋልና፤ እናንተም በፊታችን መቆም እንደማትችሉ ትሰማለህ።

73 ግን ድንጋይ ወይም ዓለት እንዲሁም ማምልጫም በሌለበት ሜዳ ላይ ፈረሰኛውንና እጅግ ብዙ የሆነውን ሠራዊቴን መቋቋም አትችልም”።

74 ዮናታን የአጶሎንዮስን ቃል በሰማ ጊዜ መንፈሱ ተቆጣ፤ ተነሣሳም፤ ዐሥር ሺህ ሰዎች መረጠና ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ሄደ፤ ወንድሙ ስምንም እርሱን ለማገዝ ተከትሎት ሄደ።

75 ከኢዮጴ ወጣ ብሎ ሠረፈ፤ የአጶሎንዮስ ወታደሮች በከተማዋ ስለ ነበሩ ነዋሪዎቹ በሮቹን ዘጉባቸው፤ እነዮናታን ውጊያ ጀመሩ።

76 የከተማይቱ ነዋሪዎችም በፍርሃት ተይዘው በሮቹን ከፈቱላቸው፤ ዮናታንም ኢዮጴን ያዘ።

77 አጶሎንዮስ ይህን በሰማ ጊዜ ሦስት ሺህ ፈረሰኞችና ብዙ ሠራዊት አሰለፈና አገሩን ሰንጥቆ የሚያልፍ መስሎ ወደ አዛጦን አመራ፤ ግን ብዛት ባለው በፈረሰኛው ጦር ተማምኖ በዚያኑ ጊዜ ወደ ሜዳው ዘልቆ ሄደ።

78 ዮናታን እስከ አዛጦን ስለተከተለው ወታደሮቻቸው በዚያው ውጊያ ጀመሩ።

79 አጰሎንዮስ ከነዮናታን በስተ ኋላ አንድ ሺህ ፈረሰኞች በድብቅ ትቶ ነበር።

80 ዮናታን እንዲህ ያለ ወጥመድ በስተ ኋላው መኖሩን አወቀ፤ ፈረሰኞቹ የእርሱን ሠራዊት ከበው ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ቀስቶቻቸውን ወረወሩባቸው።

81 ዮናታን ወታደሮች እርሱ በሚያስተላልፍላቸው ትእዛዝ መሠረት ጦሩን በደንብ ተቋቋሙ፤ ፈረሰኞቹም ደከሙ።

82 በዚያን ጊዜ ስምዖን ወታደሮቹን ይዞ እግረኛውን ክፍለ ጦር ወጋ፤ ፈረሰኛው ጦር ደከመና ጠላቶች በስምዖን ተሸነፉና ሸሹ።

83 ፈረሰኛው ጦር በሜዳው ተበታተነ፤ ሸሽተው ወደ አዛጦን ደረሱና ራሳቸውን ለማዳን ወደ ጣዖታቸው ወደ ዳጐን ቤት ገቡ።

84 ዮናታን አዛጦንንና በአካባቢዋ ያሉትን ከተሞች በእሳት አጋየ፤ ዘረፋቸው የዳጐንን ቤትና በዚያ ውስጥ ተጠግተው የሚገኙትን በእሳት አቃጠለ።

85 በጠቅላላው ስምንት ሺህ ሰዎች በሰይፍ ወይም በእሳት ሞተዋል።

86 ዮናታንም ከእዚያ በመሄድ በአስቃሉን አጠገብ ሠፈረ፤ ነዋሪዎቹ በታላቅ ክብር ሊቀበሉት ወጡ፤

87 ከእዚህ በኋላ ዮናታንና የእርሱ ሰዎች ብዙ ምርኮ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

88 ንጉሥ እስክንድር ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ ለዮናታን በክብር ላይ ክብር ጨመረለት፤

89 ለንጉሥ ዘመዶች መስጠት የተለመደውን የወርቅ መቆለፊያ ላከለት፤ አቃሮንንና አካባቢዋንም ጭምር በባለቤትነት ሰጠው።