መሳፍንት 20:26 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ ወጥተው ወደ ቤቴል መጡ፤ አለቀሱም፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፤ በዚያም ቀን እስከ ማታ ድረስ ጾሙ፤ በእግዚአብሔርም ፊት የሚቃጠል መሥዋዕትንና የደኅንነት መሥዋዕትን አቀረቡ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም የእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ ወደ ቤቴል ወጡ፤ እዚያም እያለቀሱ በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፤ በዚያ ቀን እስኪመሽ ድረስ ጾሙ፤ በእግዚአብሔር ፊት የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ ወደ ቤቴል ወጡ፤ እዚያም እያለቀሱ በጌታ ፊት ተቀመጡ፤ በዚያን ቀን እስኪመሽ ድረስ ጾሙ፤ በጌታ ፊት የሚቃጠል መሥዋትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚህም በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ወደ ቤትኤል ሄደው አለቀሱ፤ በዚያም ምንም ሳይበሉ እስከ ምሽት በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጠው ቈዩ፤ የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት አቀረቡ፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ ወጥተው ወደ ቤቴል መጡ፥ አለቀሱም፥ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፥ በዚያም ቀን እስከ ማታ ድረስ ጾሙ፥ በእግዚአብሔር ፊት የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት አቀረቡ። |
ሕዝቡም ሁሉ ገና ሳይመሽ ዳዊትን እንጀራ ይበላ ዘንድ ሊጋብዙት መጡ፤ ዳዊት ግን፥ “ፀሐይ ሳትጠልቅ እንጀራ ወይም ሌላ ነገር ብቀምስ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፥ ይህንም ይጨምርብኝ” ብሎ ማለ።
በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ ዘንድ፥ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን፥ ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾምን አወጅሁ።
እንዲህም ሆነ፤ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር በኢየሩሳሌም የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ፥ ከይሁዳም ከተሞች ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ለመጾም ዐዋጅ ነገሩ።
ጾምን ቀድሱ፤ ምህላንም ዐውጁ፤ ሽማግሌዎቹንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔርም በአንድነት ጩኹ።
ኢያሱም የእስራኤልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴሎ ሰበሰበ፤ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች፥ አለቆቻቸውንም፥ ጸሓፊዎቻቸውንም፥ ፈራጆቻቸውንም ጠራቸው። በእግዚአብሔርም ፊት አቆማቸው።
ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፤ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግንባራቸው ተደፉ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ።
የእስራኤልም ልጆች ተነሥተው ወደ ቤቴል ወጡ፤ እግዚአብሔርንም፥ “የብንያምን ልጆች ለመውጋት መሪ ሆኖ ማን ይውጣልን?” ብለው ጠየቁት፤ እግዚአብሔርም፥ “ይሁዳ መሪ ይሁን” አለ፤
የእስራኤልም ልጆች ወጥተው በእግዚአብሔር ፊት እስከ ማታ ድረስ አለቀሱ፤ እግዚአብሔርንም፥ “ከወንድሞቻችን ከብንያም ልጆች ጋር ለመዋጋት ዳግመኛ እንቀርባለን?” ብለው ጠየቁ። እግዚአብሔርም “በእነርሱ ላይ ውጡ” አለ።
በሁለተኛውም ቀን የብንያም ልጆች ሊገጥሙአቸው ከገባዖን ወጡ፤ ከእስራኤልም ልጆች ደግሞ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎችን በምድር ላይ ገደሉ፤ እነዚህም ሁሉ ሰይፍ የሚመዝዙ ነበሩ።
ሕዝቡም ወደ ቤቴል መጥተው በዚያ በእግዚአብሔር ፊት እስከ ማታ ድረስ ተቀመጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጽኑዕ ልቅሶ አለቀሱ።
መልእክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ገባዖን መጥተው ይህን ነገር በሕዝቡ ጆሮ ተናገሩ፤ ሕዝቡም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ።
እነርሱም ወደ መሴፋ ተሰበሰቡ፤ ውኃም ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት በምድር ላይ አፈሰሱ፤ በዚያም ቀን ጾሙ፤ በዚያም፥ “በእግዚአብሔር ፊት በድለናል” አሉ። ሳሙኤልም በእስራኤል ልጆች ላይ በመሴፋ ፈረደ።