መሳፍንት 18:18 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እነዚህም ሰዎች ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረፀውን ምስል፥ ኤፉዱንም፥ ተራፊሙንም፥ ቀልጦ የተሠራውን ምስልም ወሰዱ፤ ካህኑም፥ “ምን ታደርጋላችሁ?” አላቸው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እነዚህ ሰዎች ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል በሚወስዱበት ጊዜ ካህኑ፣ “ምን ማድረጋችሁ ነው?” አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እነዚህ ሰዎች ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፥ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል በሚወስዱበት ጊዜ ካህኑ፥ “ምን ማድረጋችሁ ነው?” አላቸው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እርሱም ሰዎቹ ወደ ሚካ ቤት ሄደው ምስሎቹንና ኤፉዱን በሚወስዱበት ጊዜ “ምን ማድረጋችሁ ነው?” ሲል ጠየቃቸው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እነዚህም ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስል ኤፉዱንም ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም በወሰዱ ጊዜ፥ ካህኑ፦ ምን ታደርጋላችሁ? አላቸው። |
የባቢሎን ንጉሥ ምዋርቱን ያምዋርት ዘንድ፥ በትሩን ያነሣ ዘንድ፥ ጣዖቱንም ይጠይቅ ዘንድ በሁለት መንገዶች ራስ ላይ ይቆማል።
“ለእናንተ በእጅ የተሠራ ጣዖት አታድርጉ፤ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ትሰግዱለትም ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና።
ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎች መጥተው ወደዚያ ገቡ፤ የተቀረፀውንም ምስል ኤፉዱንም፥ ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም ወሰዱ፤ ካህኑም የጦር ዕቃ ከታጠቁት ከስድስት መቶ ሰዎች ጋር በደጃፉ አጠገብ ቆሞ ነበር።
እነርሱም፥ “ዝም በል፤ እጅህንም በአፍህ ላይ ጫን፤ ከእኛም ጋር ና፥ አባትና ካህንም ሁንልን፤ ለአንድ ሰው ቤት ካህን መሆን ወይስ በእስራኤል ዘንድ ለነገድና ለወገን ካህን መሆን ማናቸው ይሻልሃል?” አሉት።