ኢሳይያስ 35:8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በዚያም ንጹሕ መንገድ ይሆናል፤ እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፤ በዚያም ንጹሓን ያልሆኑ አያልፉበትም፤ ርኩስ መንገድም በዚያ አይኖርም፤ የተበተኑትም በእርሱ ይሄዳሉ፤ አይሳሳቱምም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በዚያ አውራ ጐዳና ይሆናል፤ የተቀደሰ መንገድ ተብሎ ይጠራል። የረከሱ አይሄዱበትም፤ በመንገዱ ላይ ላሉት ብቻ ይሆናል፤ ቂሎችም አይሄዱም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በዚያም አውራ ጎዳና ይኖራል፥ እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፤ ንጹሐን ያልሆኑ አያልፉበትም፥ የእርሱ የሆኑ ሕዝቦች ግን ያልፉበታል፤ ተጓዦች ሆኑ፥ ሰነፎች እንኳ አይስቱበትም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በዚያ “ቅዱስ ጐዳና” የሚባል መንገድ ይኖራል፤ እርሱም ለእግዚአብሔር ሰዎች ይሆናል፤ ንጹሕ ያልሆነ ሰው በዚያ መንገድ አይሄድም፤ ሞኞችም ሊሄዱበት አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በዚያም ጎዳናና መንገድ ይሆናል እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፥ ንጹሐንም ያልሆኑ አያልፉበትም፥ ለንጹሐን ግን ይሆናል፥ ተላላፊዎችና ሰነፎች እንኳ አይስቱበትም። |
የሕይወት መንገዶች ከክፉ ያርቃሉ፤ የጽድቅ ጎዳና የዘመን ብዛት ነው። ትምህርትን የሚቀበል በበጎ ይኖራል። ተግሣጽን የሚጠብቅም ብልሃተኛ ይሆናል። መንገዶቹን የሚጠብቅ ሰውነቱን ይጠብቃል፥ ሕይወትንም የሚወድድ አፉን ይጠብቃል።
በዚያም ወራት ከግብፅ ወደ አሦር መንገድ ይሆናል፤ አሦራዊውም ወደ ግብፅ፥ ግብፃዊውም ወደ አሦር ይገባል፤ ግብፃውያንም ለአሦራውያን ይገዛሉ።
ዕውሮችንም በማያውቋት መንገድ አመጣቸዋለሁ፤ የማያውቋትንም ጎዳና እንዲረግጡ አደርጋቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፤ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህንም አደርግላቸዋለሁ፤ አልተዋቸውምም።
እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፤ እናንተም አታውቁትም፤ በምድረ በዳም መንገድን፥ በበረሃም ወንዞችን አደርጋለሁ።
ባሕሩን ያደረቅሽ፥ ጥልቁንም ውኃ ያደረቅሽው፥ የዳኑትም ይሻገሩ ዘንድ ጥልቁን ባሕር ጥርጊያ ጎዳና ያደረግሽ አይደለሽምን?
ጽዮን ሆይ፥ ተነሺ፥ ተነሺ፤ ጽዮን ሆይ፥ ኀይልሽን ልበሺ፤ አንቺም ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ያልተገረዘና ርኩስ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አንቺ አያልፍምና ክብርሽን ልበሺ።
እናንተ የእግዚአብሔርን ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፥ እልፍ በሉ፤ እልፍ በሉ፤ ከዚያ ውጡ፤ ርኩስን ነገር አትንኩ፤ ከመካከልዋ ውጡ፤ ራሳችሁን ለዩ።
እግዚአብሔር፥ “የተቤዣቸው፥ የተቀደሰ ሕዝብ” ብለው ይጠሩአቸዋል፤ አንቺም፥ “የተተወች ያይደለች የተወደደች ቅድስት ከተማ” ትባያለሽ።
“ለራስሽ የመንገድ ምልክት አድርጊ፥ መንገድንም የሚመሩ ዐምዶችን ትከዪ፤ ልብሽንም ወደ ሄድሽበት መንገድ ወደ ጥርጊያው አቅኚ፤ አንቺ የእስራኤል ድንግል ሆይ! ተመለሺ፤ ወደ እነዚህም ወደ ከተሞችሽ እያለቀስሽ ተመለሺ።
በተራራው ራስ ላይ ያለውን ቤቱንና የቤቱን ሥርዐት ሣል፤ የዙሪያውም ዳርቻ ሁሉ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። እነሆ የቤቱ ሕግ ይህ ነው።”
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በእስራኤል ልጆች መካከል ከአሉት ሁሉ በልቡና በሥጋው ያልተገረዘ የባዕድ ልጅ እንግዳ ሁሉ ወደ መቅደሴ አይግባ።
“እኔም በተቀደሰ ተራራዬ በጽዮን የምቀመጥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ ያን ጊዜም ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ከተማ ትሆናለች፥ እንግዶችም ከእንግዲህ ወዲህ አያልፉባትም።
በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፤ ትተኛላችሁ፤ የሚያስፈራችሁም የለም፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ።
“እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤” የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፤ ትርጓሜውም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤” የሚል ነው።
ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው፥ “የእውነትና የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።
ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድድ ግን ትምህርቴ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ሆነች፥ የምናገረውም ከራሴ እንዳይደለ እርሱ ያውቃል።
ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፤ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ፥ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፤
እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።