ሕዝቅኤል 12:3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አንተም የሰው ልጅ ሆይ! የስደተኛ እክት አዘጋጅ፤ በፊታቸውም ቀን ለቀን ተማረክ፤ በፊታቸውም ከስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ተማርከህ ሂድ፤ እነርሱም ዐመፀኛ ቤት እንደ ሆኑ ምንአልባት ያስተውሉ ይሆናል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ እነርሱ እያዩህ በቀን ጓዝህን ጠቅልለህ ለመሰደድ ተዘጋጅ፤ ካለህበትም ስፍራ ተነሥተህ ወደ ሌላ ቦታ ሂድ፤ ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም ምናልባት ይህን ያስተውሉታል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የስደተኛ ጓዝ ለራስህ አዘጋጅ፥ እያዩህም በቀን ወደ ምርኮ ሂድ፥ በፊታቸውም እንደ ምርኮኛ ከስፍራህ ወደ ሌላ ስፍራ ሂድ፥ ዓመፀኛ ቤት ቢሆኑም ምናልባት ያስተውሉ ይሆናል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ! የስደት ዕቃህን ጠቅልለህ አዘጋጅ፤ እነርሱ እያዩም የስደት ጒዞህን በቀን ጀምር፤ እንደ ስደተኛ ከቦታህ ተነሥተህ ወደ ሌላ ቦታ ሂድ፤ ዐመፀኞች ቢሆኑም እንኳ ያስተውሉ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የስደተኛ እክት አዘጋጅ በፊታቸውም ቀን ለቀን ተማረክ፥ በፊታቸውም ከስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ተማርከህ ሂድ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት እንደ ሆኑ ምናልባት ያስተውሉ ይሆናል። |
ምናልባት እያንዳንዳቸው ይሰሙ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስለ ሥራቸው ክፋት ያሰብሁባቸውን ክፉ ነገር እተዋለሁ።”
ምናልባት የይሁዳ ቤት ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ዘንድ፥ እኔም በደላቸውንና ኀጢአታቸውን ይቅር እል ዘንድ፥ እኔ አደርግባቸዋለሁ ያልሁትንና ያሰብሁትን ክፉ ነገር ሁሉ ይሰሙ ይሆናል።”
እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቍጣውና መዓቱ ታላቅ ነውና ምናልባት ልመናቸው በእግዚአብሔር ፊት ትደርስ ይሆናል፤ ሁሉም ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል።”
ነገር ግን አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙኝም፤ ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ አባቶቻቸውም ከአደረጉት ይልቅ የባሰ አደረጉ።
እንዳዘዘኝም አደረግሁ፤ ቀን ለቀንም እክቴን እንደ ስደተኛ እክት አወጣሁ፤ በማታም ጊዜ ግንቡን በእጄ ነደልሁ፤ በጨለማም አወጣሁት፤ በፊታቸውም በትከሻዬ ላይ አንግቼ ተሸከምሁት።
እኔም ምላስህን ከትናጋህ ጋር አጣብቃታለሁ፤ አንተም ዲዳ ትሆናለህ፤ እነርሱም ዐመፀኛ ቤት ናቸውና የሚዘልፍ ሰው አትሆንባቸውም።
ነገር ግን በተናገርሁህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፤ እነርሱም ዐመፀኛ ቤት ናቸውና አንተ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሚሰማ ይስማ፤ እንቢ የሚልም እንቢ ይበል” ትላቸዋለህ።
እኔ ሕያው ነኝና ኀጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኀጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ! ተመለሱ፤ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው።
እነርሱም ስለ ሠሩት ሥራ ሁሉ መቅሠፍታቸውን ያገኛሉ፤ አንተም የቤቱን መልክና ምሳሌውን፥ መውጫውንም፥ መግቢያውንም፥ ሥርዐቱንም፥ ሕጉንም ሁሉ አስታውቃቸው፤ ሥርዐቱንና ሕጉን ሁሉ ይጠብቁ ዘንድ፥ ያደርጉትም ዘንድ በፊታቸው ጻፈው።
“ነቢያትን የምትገድሊያቸው፥ ወደ አንቺ የተላኩትን ሐዋርያትንም የምትደበድቢያቸው ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፍዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን ልሰበስባቸው ምን ያህል ወደድሁ? ነገር ግን እንቢ አላችሁ።
የወይኑ ባለቤትም፦ እንግዲህ ምን ላድርግ? ምናልባት እርሱን እንኳ አይተው ያፍሩ እንደ ሆነ የምወደውን ልጄን ልላክ ብሎ ላከው።
ለእነርሱ፥ ለዘለዓለምም ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ፥ እንዲፈሩኝ፥ ሁልጊዜም ትእዛዜን ሁሉ እንዲጠብቁ እንዲህ ያለ ልብ ማን በሰጣቸው፥
ደግሞም “ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሓን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው ወደ አእምሮ ይመለሳሉ፤” ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ።