ራእይ 11:2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም የውጭውን አደባባይ ግን ተወው አትለካው፣ ለአሕዛብ የተሰጠ ነውና። እነርሱ የተቀደሰችውን ከተማ አርባ ሁለት ወር ይረግጧታል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከመቅደሱ ውጭ ያለውን አደባባይ ግን ተወው፤ አትለካውም፥ ምክንያቱም ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና፤ እነርሱም ለአርባ ሁለት ወር ያህል የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከቤተ መቅደሱ ውጪ ያለውን ክፍት ቦታ ግን ተወው፤ እርሱ ለአሕዛብ የተሰጠ ስለ ሆነ አትለካው፤ አሕዛብ ቅድስቲቱን ከተማ ለአርባ ሁለት ወር ይረግጡአታል፤ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው፤ አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል። |
እናንተ የቅድስቲቱ ከተማ ነዋሪዎች ነን ብላችሁ ራሳችሁን የምትጠሩ፣ በእስራኤል አምላክ የምትታመኑ፣ ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው የሚለውን አድምጡ፤
ጽዮን ሆይ፤ ተነሺ፤ ተነሺ፤ ኀይልን ልበሺ፤ ቅድስቲቱ ከተማ፤ ኢየሩሳሌም ሆይ! የክብር ልብስሽን ልበሺ፤ ያልተገረዘ የረከሰም ከእንግዲህ ወደ አንቺ አይገባም።
“ይህን ከፈጸምህ በኋላ ደግሞ በቀኝ ጐንህ ተኝተህ የይሁዳን ቤት ኀጢአት ትሸከማለህ፤ ለእያንዳንዱ ዓመት አንድ አንድ ቀን በማድረግ አርባ ቀን መድቤብሃለሁ።
ስለዚህ በአራቱም ማእዘን ለካው፤ የተቀደሰውን ስፍራ ከሌላው የሚለይ በዙሪያው ግንብ ነበረ፤ የግንቡም ርዝመት ዐምስት መቶ ክንድ ሲሆን፣ ወርዱ ዐምስት መቶ ክንድ ነበር።
ከወንዙ ውሃ በላይ የነበረው በፍታ የለበሰው ሰው፣ ቀኝ እጁንና ግራ እጁን ወደ ሰማይ አንሥቶ፣ “ለዘመን፣ ለዘመናት፣ ለዘመንም እኩሌታ ይሆናል፤ የተቀደሰው ሕዝብ ኀይል መሰበር ሲያከትም፣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ይፈጸማሉ” ብሎ ለዘላለም በሚኖረው በርሱ ሲምል ሰማሁ።
“ከዚያም የሚያደቅቀውንና የሚበላውን፣ የቀረውንም ሁሉ በእግሮቹ የሚረጋግጠውን፣ የብረት ጥርሶችና የናስ ጥፍሮች የነበሩትን፣ ከሌሎቹ አራዊት የተለየና እጅግ አስፈሪ የሆነውን የአራተኛውን አውሬ እውነተኛ ትርጕም ማወቅ ፈለግሁ።
በልዑል ላይ የዐመፅ ቃል ይናገራል፤ የልዑልንም ቅዱሳን ያስጨንቃል፤ ለበዓላት የተመደበውን ጊዜና ሕግን ለመለወጥ ይሞክራል፤ ቅዱሳንም ለዘመን፣ ለዘመናት፣ ለዘመን እኩሌታም ለርሱ ዐልፈው ይሰጣሉ።
ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፤ ሌላውም ቅዱስ እንዲህ አለው፤ “ስለ ዘወትሩ መሥዋዕት፣ ለጥፋት ምክንያት ስለ ሆነው ዐመፅ፣ ከእግር በታች እንዲረገጡ ዐልፈው ስለሚሰጡት መቅደስና ሰራዊት የታየው ራእይ የሚፈጸመው መቼ ነው?”
ምድሪቱን ለመሰለል በቈያችሁበት አርባ ቀን ልክ እያንዳንዱ ዓመት እንደ አንድ ዕለት ተቈጥሮ ስለ ኀጢአታችሁ አርባ ዓመት መከራ ትቀበላላችሁ፤ ምን ያህል በእናንተ ላይ እንደ ተነሣሁም ታውቃላችሁ።’
“እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን መልሶ ሊያገኝ ይችላልን? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ጥቅም አይኖረውም።
ታዲያ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፣ የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ተራ ነገር የቈጠረ፣ የጸጋንም መንፈስ ያክፋፋ እንደ ምን ያለ የባሰ ቅጣት ይገባው ይመስላችኋል?
ከሦስቱ ቀን ተኩል በኋላ ግን፣ የሕይወት እስትንፋስ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶ ገባባቸው፤ እነርሱም ተነሥተው በእግሮቻቸው ቆሙ፤ ይመለከቷቸውም በነበሩት ላይ ታላቅ ድንጋጤ ወረደባቸው።
ማንም በዚህ የትንቢት መጽሐፍ ከተጻፈው ቃል አንዳች ቢያጐድል፣ እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ ዕድሉን ያጐድልበታል።