ሚልክያስ 4:1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም “እነሆ፤ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞች ሁሉና ክፉ አድራጊዎች በሙሉ ገለባ ይሆናሉ፤ ያ የሚመጣው ቀንም ያቃጥላቸዋል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “ሥርም ሆነ ቅርንጫፍ አያስቀርላቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) “እነሆ፥ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞች ሁሉና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል” ይላል የሠራዊት ጌታ፤ ሥርንና ቅርንጫፍንም አያስቀርላቸውም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ ትዕቢተኞችና ክፉ አድራጊዎች እንደ ገለባ በእሳት የሚቃጠሉበት ጊዜ እየመጣ ነው፤ የሚመጣውም ከእነርሱ ሥር፥ ወይም ቅርንጫፍ ሳያስቀር ሁሉንም ያቃጥላል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እነሆ፥ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፣ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፣ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፥ ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እነሆ፥ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፥ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፥ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፥ ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። |
ተተክለው ምንም ያህል ሳይቈዩ፣ ተዘርተው ምንም ያህል ሳይሰነብቱ፣ ገና ሥር መስደድ ሳይጀምሩ አነፈሰባቸው፤ እነርሱም ደረቁ፤ ዐውሎ ነፋስም እንደ ገለባ ጠራርጎ ወሰዳቸው።
“ከምሥራቅ አንዱን ያነሣው፣ በጽድቅም ወደ አገልግሎቱ የጠራው ማን ነው? አሕዛብን አሳልፎ ሰጠው፤ ነገሥታትን በፊቱ አስገዛለት በሰይፉም እንደ ትቢያ አቦነናቸው፤ በቀስቱም በነፋስ እንደ ተበተነ ገለባ አደረጋቸው።
እነሆ፣ እነርሱ ገለባ ናቸው፤ እሳት ይበላቸዋል፤ ከነበልባሉ ወላፈን የተነሣ፣ ራሳቸውን ማዳን አይችሉም። ሰው የሚሞቀው ፍም አይኖርም፤ ተቀምጠው የሚሞቁትም እሳት የለም።
ስለዚህ የእሳት ነበልባል ገለባን እንደሚበላ፣ ድርቆሽም በእሳት ጋይቶ እንደሚጠፋ፣ የእነርሱም ሥር እንዲሁ ይበሰብሳል፤ አበባቸውም እንደ ትቢያ ይበንናል፤ የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕግ ንቀዋልና፤ የእስራኤል ቅዱስ የተናገረውንም ቃል አቃልለዋል።
እንግዲህ ርኩሰት እንደ እሳት ይቀጣጠላል፤ እሾኽንና ኵርንችትን ይበላል፤ ጥቅጥቅ ያለውን ደን ያነድዳል፤ ጢሱም ተትጐልጕሎ እንደ ዐምድ ይቆማል።
በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቍጣ ምድር ትጋያለች፤ ሕዝቡም እሳት ውስጥ እንደሚጨመር ማገዶ ይሆናል፤ ወንድሙንም ማዳን የሚችል ማንም የለም።
በእኔ ላይ ያመፁትንና የበደሉኝን ከመካከላችሁ አስወግዳለሁ፤ ከሚኖሩበት አገር አወጣቸዋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
“ ‘መንጋዬ ስለ ሆናችሁት ስለ እናንተ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በበግና በበግ መካከል፣ በአውራ በግና በአውራ ፍየል መካከል እፈርዳለሁ።
በጽዮን መለከትን ንፉ፤ በቅዱሱ ተራራዬም የማስጠንቀቂያውን ድምፅ አሰሙ። በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ፤ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና፤ እርሱም በደጅ ነው።
“ቁመቱ እንደ ዝግባ፣ ጥንካሬውም እንደ ወርካ ዛፍ የነበረ ቢሆንም፣ አሞራዊውን ከፊታቸው አጠፋሁት፣ ከላይ ፍሬውን፣ ከታችም ሥሩን አጠፋሁ።
የያዕቆብ ቤት እሳት፣ የዮሴፍም ቤት ነበልባል ይሆናል፤ የዔሳው ቤት ገለባ ይሆናል፤ ያቃጥሉታል፤ ይበሉትማል፤ ከዔሳው ቤት የሚተርፍ አይኖርም።” እግዚአብሔር ተናግሯል።
“ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፤ ቅርብ ነው ፈጥኖም ይመጣል፤ በእግዚአብሔር ቀን የሚሰማው ልቅሶ መራራ ነው፤ በዚያ ጦረኛውም ምርር ብሎ ይጮኻል፤
በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን፣ ብራቸውም ሆነ ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም።” መላዪቱ ምድር፣ በቅናቱ ትበላለች፤ በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ፣ ድንገተኛ ፍጻሜ ያመጣባቸዋልና።
እርሱ የሚመጣበትን ቀን ማን ሊቋቋመው ይችላል? በሚገለጥበትስ ጊዜ በፊቱ መቆም የሚችል ማን ነው? እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳት ወይም እንደ ልብስ ዐጣቢ ሳሙና ነውና።
ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያነጻ ሰው ይቀመጣል፤ ሌዋውያንንም አንጽቶ እንደ ወርቅና እንደ ብር ያጠራቸዋል፤ ከዚያም እግዚአብሔር ቍርባንን በጽድቅ የሚያቀርቡ ሰዎች ይኖሩታል፤
“እነሆ፤ ወሮታችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፣ በዚያ ቀን ደስ ይበላችሁ፤ ፈንድቁም፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ ያደረጉት ይህንኑ ነበርና።