ዮሐንስ 10:28 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም፤ ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘለዓለምም አይጠፉም፤ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እኔ የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ስለዚህ ከቶ አይጠፉም፤ ከእኔ እጅ ማንም ነጥቆ አይወስዳቸውም። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እኔም የዘለዓለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘለዓለሙም አይጠፉም፤ ከእጄም የሚነጥቃቸው የለም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። |
በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል፤ የሚከስሽንም አንደበት ሁሉ ትረቺያለሽ፤ እንግዲህ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፤ ከእኔ የሚያገኙትም ጽድቃቸው ይኸው ነው፤” ይላል እግዚአብሔር።
ጆሯችሁን ከፍታችሁ ወደ እኔ ቅረቡ፤ ነፍሳችሁም እንድትኖር አድምጡኝ። ለዳዊት በገባሁት በጽኑ ፍቅሬ፣ ከእናንተም ጋራ የዘላለም ኪዳን አደርጋለሁ።
ከእንግዲህ ማንም ሰው ባልንጀራውን፣ ወይም ወንድሙን፣ ‘እግዚአብሔርን ዕወቅ’ ብሎ አያስተምርም፤ ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ፣ ሁሉም እኔን ያውቁኛልና፤” ይላል እግዚአብሔር። “በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስብም።”
መልካምን ነገር ለእነርሱ ከማድረግ እንዳልቈጠብና ከእኔም ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በውስጣቸው ላኖር ከእነርሱ ጋራ የዘላለም ቃል ኪዳን እገባለሁ።
ለሚጠፋ እንጀራ አትሥሩ፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር ምግብ ሥሩ፤ ለዚህም እግዚአብሔር አብ ማረጋገጫ ማኅተሙን በርሱ ላይ ዐትሟልና።”
በአንድ ሰው መተላለፍ ምክንያት ሞት በዚህ ሰው በኩል የነገሠ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅ ስጦታ የተቀበሉት፣ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንዴት አብልጠው በሕይወት አይነግሡ!
ይህም የሆነው ኀጢአት በሞት እንደ ነገሠ ሁሉ፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ደግሞ የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ እንዲነግሥ ነው።
እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው፤ ይኸውም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኵር እንዲሆን ነው።
በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፤ እኛ ግን ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ ልናመሰግን ይገባናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር እናንተን ከመጀመሪያ አንሥቶ በመንፈስ ተቀድሳችሁና በእውነትም አምናችሁ እንድትድኑ መርጧችኋል።
ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ በርሱ ለሚያምኑና የዘላለምን ሕይወት ለሚቀበሉ ወሰን የሌለው ትዕግሥቱን ከኀጢአተኞች ዋና በሆንሁት በእኔ እንደ ምሳሌ አድርጎ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ።
መከራን የምቀበለውም ለዚሁ ነው፤ ሆኖም ያመንሁትን እርሱን ስለማውቅ አላፍርበትም፤ የሰጠሁትንም ዐደራ እስከዚያች ቀን ድረስ መጠበቅ እንደሚችል ተረድቻለሁ።
ይህም ሕይወት ተገለጠ፤ እኛም አይተናል፤ እንመሰክራለንም። ከአብ ዘንድ የነበረውን፣ ለእኛም የተገለጠውን የዘላለም ሕይወት እንነግራችኋለን፤
ከእኛ መካከል ወጡ፤ ይሁን እንጂ ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገን ቢሆኑማ ኖሮ ከእኛ ጋራ ጸንተው በኖሩ ነበር። ነገር ግን ሁሉም ከእኛ ወገን እንዳልነበሩ ይታወቅ ዘንድ ከእኛ ተለዩ።