ኤርምያስ 10:15 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም እነርሱ ከንቱ የፌዝ ዕቃዎች ናቸው፤ ፍርድ ሲመጣባቸው ይጠፋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እነርሱ ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው፤ በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እነዚህ አማልክት ዋጋ ቢሶችና የፌዝ ዕቃዎች ናቸው፤ እግዚአብሔር እነርሱን ለመቅጣት በሚገለጥበትም ጊዜ ይደመሰሳሉ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አገጣጥመው የሚሠሩት ሥራ ከንቱ ነው፤ በተጐበኙ ጊዜም ይጠፋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እነርሱ ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው፥ በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ። |
ከአሕዛብ ከንቱ ጣዖቶች መካከል ዝናብ ሊያዘንብ የሚችል አለን? ሰማያትስ በራሳቸው ማካፋት ይችላሉን? አይ! አይችሉም፣ እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ ይህን ሁሉ የምታደርግ አንተ ነህ፣ ስለዚህም ተስፋችን በአንተ ላይ ነው።
ሕዝቤ ግን ረስቶኛል፤ ለማይረቡ ነገሮች ዐጥኗል፣ በራሱ መንገድ፣ በቀደሞው ጐዳና ተሰናክሏል፤ በሻካራው መሄጃ፣ ባልቀናውም ጥርጊያ መንገድ ሄዷል።
እርሱ የግብጽ አማልክት ቤተ ጣዖቶች ላይ እሳት ይለኵሳል፤ ያቃጥላቸዋልም፣ አማልክታቸውንም ማርኮ ይወስዳል። እረኛ ልብሱን እንደሚጐናጸፍ የግብጽን ምድር ተጐናጽፎ ከዚያ በሰላም ይሄዳል።
“በሕዝቦች መካከል ተናገሩ፤ አስታውቁም፤ ሰንደቅ ዐላማ አንሡ፤ ዐውጁ፤ አንዳች ሳታስቀሩ፣ እንዲህ በሉ፤ ‘ባቢሎን ትያዛለች፤ ቤል ይዋረዳል፤ ሜሮዳክ በሽብር ይሞላል፤ ጣዖቶቿ ይዋረዳሉ፤ አማልክቷም ይሸበራሉ።’
ስለ ጸያፉ ተግባራቸው ዐፍረዋል እንዴ? የለም! በጭራሽ አላፈሩም፤ ዕፍረት ምን እንደ ሆነ እንኳ አያውቁም። ስለዚህ ከወደቁት ጋራ ይወድቃሉ፤ በሚቀጡ ጊዜ ይዋረዳሉ፣ ይላል እግዚአብሔር።
እንዲህ የሚለውን የሕዝቤን ጩኸት፣ ከሩቅ ምድር ስማ፤ “እግዚአብሔር በጽዮን የለምን? ንጉሧስ በዚያ አይኖርምን?” “በተቀረጹ ምስሎቻቸው፣ እንዲሁም ከንቱ በሆኑ ባዕዳን ለምን አስቈጡኝ?”
የቅጣት ቀን መጥቷል፤ የፍርድም ቀን ቀርቧል፤ እስራኤልም ይህን ይወቅ! ኀጢአታችሁ ብዙ፣ ጠላትነታችሁም ታላቅ ስለ ሆነ፣ ነቢዩ እንደ ቂል፣ መንፈሳዊውም ሰው እንደ እብድ ተቈጥሯል።
“በዚያ ቀን የጣዖታትን ስም ከምድሪቱ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህም አይታሰቡም” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “ነቢያትንና ርኩስ መንፈስን ከምድሪቱ አስወግዳለሁ።
“እናንተ ሰዎች፤ ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? እኛም እኮ እንደ እናንተው ሰዎች ነን። እናንተም ደግሞ ከነዚህ ከንቱ ነገሮች ርቃችሁ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር እንድትመለሱ ወንጌልን እንሰብክላችኋለን።
በሚቀጥለው ቀን ጧት ተነሥተው ሲመለከቱ፣ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት፣ መሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ ነበር፤ ራሱና እጆቹ ተሰባብረው በደጃፉ ላይ የወደቁ ሲሆን፣ የቀረው ሌላው አካሉ ብቻ ነበር።