ኢሳይያስ 7:2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ለዳዊት ቤት፣ “ሶርያና ኤፍሬም ተባብረዋል” የሚል ወሬ በደረሰ ጊዜ፣ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ የአካዝና የሕዝቡ ልብ እንዲሁ ተናወጠ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ለዳዊት ቤት፤ “ሶርያና ኤፍሬም ተባብረዋል” የሚል ወሬ በደረሰ ጊዜ፤ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ የአካዝና የሕዝቡ ልብ እንዲሁ ተናወጠ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ሶርያ ከእስራኤል መንግሥት ጋር በመተባበር የጦር ቃል ኪዳን መግባትዋን የይሁዳ ንጉሥ በሰማ ጊዜ እርሱና ሕዝቡ ደንግጠው ልባቸው በነፋስ እንደ ተመታ ዛፍ ተናወጠ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ለዳዊት ቤትም፥ “አራም ከኤፍሬም ጋር ተባብረዋል” የሚል ወሬ ተነገረ፤ የእርሱም ልብ የሕዝቡም ልብ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ ተናወጠ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ለዳዊትም ቤት፦ ሶርያ ከኤፍሬም ጋር ተባብረዋል የሚል ወሬ ተነገረ፥ የእርሱም ልብ የሕዝቡ ልብ የዱር ዛፍ በነፋስ እንድትናወጥ ተናወጠ። |
መላው እስራኤልም ንጉሡ ሊሰማቸው አለመፈለጉን በተረዱ ጊዜ፣ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ከዳዊት ምን ድርሻ አለን? ከእሴይስ ልጅ ምን ክፍል አለን? እስራኤል፣ ሆይ፤ ወደ ድንኳንህ ተመለስ፤ ዳዊት ሆይ፤ አንተም የገዛ ቤትህን ጠብቅ።” ስለዚህ እስራኤላውያን ወደ የቤታቸው ተመለሱ።
መሠዊያውንም በእግዚአብሔር ቃል በመቃወም እንዲህ አለ፤ “አንተ መሠዊያ ሆይ! እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘እነሆ፤ ኢዮስያስ የተባለ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ እርሱም አሁን እዚህ መሥዋዕት የሚያቀርቡትን የኰረብታ ማምለኪያ ካህናት በላይህ ይሠዋቸዋል፤ የሰዎችም ዐጥንት በአንተ ላይ ይነድዳል።’ ”
ስለዚህ አሜስያስ ከኤፍሬም ወደ እርሱ የመጡትን ወታደሮች ወደየመኖሪያ ስፍራቸው አሰናበታቸው። እነርሱም በይሁዳ ላይ ክፉኛ ተበሳጭተው ነበርና በታላቅ ቍጣ ወደ መኖሪያ ስፍራቸው ተመለሱ።
ከዚያም ከኤፍሬም መሪዎች ጥቂቶቹ የዮሐናን ልጅ ዓዛርያስ፣ የምሺሌሞት ልጅ በራክያ፣ የሰሎም ልጅ ይሒዝቅያ፣ የሐድላይ ልጅ ዓሜሳይ ከጦርነቱ የተመለሱትን በመቃወም፣
የሕዝቦቻቸው ኀይል ተሟጥጧል፤ ደንግጠዋል፤ ተዋርደዋልም፤ በሜዳ እንዳሉ ዕፀዋት፣ እንደ ለጋ ቡቃያ፣ በሰገነት ላይ እንደ በቀለ ሣር፣ በእንጭጩ ዋግ እንደ መታው ሆነዋል።
ከዐሥር አንድ ሰው እንኳ በምድሪቱ ቢቀር፣ እርሱም ደግሞ ይጠፋል፤ ነገር ግን የኮምበልና የወርካ ዛፍ በተቈረጠ ጊዜ ጕቶ እንደሚቀር፣ ቅዱሱም ዘር እንዲሁ በምድሪቱ ጕቶ ሆኖ ይቀራል።”
ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ዘመን በአንተ፣ በሕዝብህና በአባትህ ቤት ላይ ያመጣል፤ የሚያመጣውም የአሦርን ንጉሥ ነው።”
የዳዊት ቤት ሆይ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ካደረጋችሁት ክፋት የተነሣ፣ ቍጣዬ እንዳይቀጣጠል፣ ማንም ሊያጠፋው እስከማይችል እንዳይነድድ፣ በየማለዳው ፍትሕን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ሰው፣ ከጨቋኙ እጅ አድኑት።
ኤፍሬም የነፋስ እረኛ ነው፤ ቀኑን ሙሉ የምሥራቅን ነፋስ ይከተላል፤ ሐሰትንና ዐመፅን ያበዛል። ከአሦር ጋራ ቃል ኪዳን ያደርጋል፤ የወይራ ዘይትንም ወደ ግብጽ ይልካል።