ኢሳይያስ 10:2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም የድኾችን መብት ለሚገፍፉ፣ የተጨቈነውን ሕዝቤን ፍትሕ ለሚያዛቡ፣ መበለቶችን ለሚበዘብዙ፣ ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ለሚመዘብሩ ወዮላቸው! መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የድኾችን መብት ለሚገፉ፤ የተጨቈነውን ሕዝቤን ፍትሕ ለሚያዛቡ፤ መበለቶችን ለሚበዘብዙ፤ ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ለሚመዘብሩ ወዮላቸው! አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የድኾች መብት እንዳይከበርና የተበደሉ ፍትሕ እንዳያገኙ የምታደርጉበት ዘዴ ይኸው ነው፤ በዚሁ ዘዴ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና አሳዳጊ የሌላቸውን የሙት ልጆች ንብረት ትነጥቃላችሁ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) መበለቶች ቅሚያቸው እንዲሆኑ፥ የሙት ልጆችንም ብዝበዛቸው እንዲያደርጉ፥ የድሃውን ፍርድ ያጣምሙ ዘንድ፥ የችግረኛውንም ሕዝቤን ፍርድ ያጐድሉ ዘንድ የግፍን ትእዛዛት ለሚያዝዙ ወዮላቸው! |
ገዥዎችሽ ዐመፀኞችና የሌባ ግብረ ዐበሮች ናቸው፤ ሁሉም ጕቦን ይወድዳሉ፤ እጅ መንሻንም በብርቱ ይፈልጋሉ፤ አባት ለሌላቸው አይቆሙም፤ የመበለቶችንም አቤቱታ አይሰሙም።
እግዚአብሔር፣ ከአለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ጋራ እንዲህ ሲል ይፋረዳል፤ “የወይኔን ቦታ ያጠፋችሁ እናንተ ናችሁ፤ ከድኾች የዘረፋችሁትም በቤታችሁ ይገኛል፤
ሰነፍ ስንፍናን ይናገራል፤ አእምሮው ክፋትን ያውጠነጥናል፤ ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌለበትን አድራጎት ይፈጽማል፤ በእግዚአብሔርም ላይ የስሕተት ቃል ይናገራል፤ ለተራበ ምግብ ይከለክላል፤ ለተጠማ ውሃ አይሰጥም።
የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር የወይን ቦታው የእስራኤል ቤት ነው፤ የይሁዳ ሰዎችም የደስታው አትክልት ናቸው። ፍትሕን ፈለገ፤ ነገር ግን ደም ማፍሰስን አየ፤ ጽድቅን ፈለገ፤ ነገር ግን የጭንቅን ጩኸት ሰማ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የእስራኤል ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ ጻድቁን ስለ ጥሬ ብር፣ ድኻውንም ስለ ጥንድ ጫማ ይሸጡታልና።
የችግረኞችን ራስ፣ በምድር ትቢያ ላይ ይረግጣሉ፤ ፍትሕንም ከጭቍኖች ይነጥቃሉ፤ አባትና ልጅ ከአንዲት ሴት ጋራ ይተኛሉ፤ እንዲህም እያደረጉ ቅዱስ ስሜን ያረክሳሉ።
ይህ ቀን አንድ ሰው ከአንበሳ ሲሸሽ፣ ድብ እንደሚያጋጥመው፣ ወደ ቤቱም ገብቶ፣ እጁን በግድግዳው ላይ ሲያሳርፍ፣ እባብ እንደሚነድፈው ነው።
“ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቍኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
“እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማይ እንዳይገቡ በሩን ስለምትዘጉባቸው እናንተ ራሳችሁ አትገቡም፤ መግባት የሚፈልጉትንም አታስገቡም። [