ቈላስይስ 3:16 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የክርስቶስ ቃል በሙላት በእናንተ ይኑር፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ ተማማሩ፤ ተመካከሩም፤ በመዝሙርና በውዳሴ በመንፈሳዊም ዝማሬ በልባችሁ በማመስገን ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የክርስቶስ ቃል በሙላት በልባችሁ ይኑር፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በውዳሴ፥ በመንፈሳዊ ዜማም እግዚአብሔርን ከልብ እያመሰገናችሁ ዘምሩ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በጥበብ ሁሉ እንድትበለጽጉ የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ዘንድ ይጽና፤ በመንፈስም ራሳችሁን አስተምሩ፤ ገሥፁ፤ መዝሙርንና ምስጋናን፥ የቅድስና ማሕሌትንም በልባችሁ በጸጋ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ |
እነዚህም ከቤተ ዘመዶቻቸው ጋራ በመሆን ሁሉም ወደ እግዚአብሔር በሚቀርበው ዜማ የሠለጠኑና የተካኑ ነበሩ፤ ቍጥራቸውም ሁለት መቶ ሰማንያ ስምንት ነበረ።
በሌሊት የተቀደሰ በዓል ስታከብሩ እንደምትዘምሩ፣ ትዘምራላችሁ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ እስራኤል ዐለት፣ ሰዎች ዋሽንት እየነፉ በደስታ እንደሚወጡ፣ የእናንተም ልብ እንዲሁ ሐሤት ያደርጋል።
ወንድሞቼ ሆይ፤ እናንተ ራሳችሁ በበጎነት የተሞላችሁ፣ በዕውቀትም ሁሉ የተሞላችሁና አንዱ ሌላውን ለመምከር ችሎታ ያላችሁ መሆናችሁን እኔ ራሴ ርግጠኛ ሆኛለሁ።
ወንድሞች ሆይ፤ እንግዲህ ምን እንበል? በምትሰበሰቡበት ጊዜ እያንዳንዱ መዝሙር አለው፤ ትምህርት አለው፤ መግለጥ አለው፤ በልሳን መናገር አለው፤ መተርጐም አለው። ይህ ሁሉ ግን ለማነጽ ይሁን።
የክብር አባት የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ይበልጥ እንድታውቁት፣ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ ያለ ማቋረጥ እለምናለሁ።
እኛም እያንዳንዱን ሰው በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ማቅረብ እንችል ዘንድ፣ ሰውን ሁሉ በጥበብ ሁሉ እየመከርንና እያስተማርን እርሱን እንሰብካለን።
ከዚህ የተነሣ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር የፈቃዱን ዕውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ሁሉ ይሞላችሁ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለይና መለመን አላቋረጥንም፤
የጌታ ቃል ከእናንተ ወጥቶ በመቄዶንያና በአካይያ መሰማቱ ብቻ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ያላችሁ እምነት በሁሉ ቦታ ታውቋል፤ ስለዚህ እኛ በዚህ ጕዳይ ላይ ምንም መናገር አያስፈልገንም፤
በዚህ ዓለም ባለጠጎች የሆኑት እንዳይታበዩ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።
ከሰማይ የሆነችው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ሰላም ወዳድ፣ ታጋሽ፣ ዕሺ ባይ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬ የሞላባት፣ አድልዎና ግብዝነት የሌለባት ናት።
አባቶች ሆይ፤ ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ። ጐበዛዝት ሆይ፤ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ፣ የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ስለሚኖር፣ ክፉውንም ስላሸነፋችሁ፣ እጽፍላችኋለሁ።
እናንተ ግን ከርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በውስጣችሁ ይኖራልና ማንም እንዲያስተምራችሁ አያስፈልግም፤ ነገር ግን የርሱ ቅባት ስለ ሁሉም ነገር፣ እውነተኛ የሆነውን እና ሐሰት ያልሆነው እናንተን እንደሚያስተምር፣ እናንተንም እንዳስተማራችሁ በርሱ ኑሩ።
እነርሱም በዙፋኑ ፊት፣ በአራቱ ሕያዋን ፍጡራንና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ መዝሙር ዘመሩ። ከምድር ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራቱ ሺሕ ሰዎች በቀር መዝሙሩን ማንም ሊማረው አልቻለም።
የእግዚአብሔር ባሪያ የሆነውን የሙሴን መዝሙርና የበጉን መዝሙር እንዲህ እያሉ ይዘምሩ ነበር፤ “ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ ሆይ፤ ሥራህ ታላቅና አስደናቂ ነው። የሕዝቦች ንጉሥ ሆይ፤ መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው።
እኔም ልሰግድለት በእግሩ ሥር ተደፋሁ፤ እርሱ ግን፣ “ተው! ይህን አታድርግ! እኔም ከአንተና የኢየሱስን ምስክር ከያዙት ወንድሞችህ ጋራ አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና” አለኝ።
እንዲህም እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ፤ “መጽሐፉን ልትወስድ፣ ማኅተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ታርደሃል፤ በደምህም ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል።