አሞጽ 2:10 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም የአሞራውያንን ምድር ልሰጣችሁ፣ ከግብጽ አወጣኋችሁ፤ አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መራኋችሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እኔም ከግብጽም ምድር አወጣኋችሁ፥ የአሞራዊውንም ምድር እንድትወርሱ በምድረ በዳም አርባ ዓመት መራኋችሁ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከግብጽ ምድር አውጥቼ አርባ ዓመት ሙሉ በበረሓ መራኋችሁ፤ የአሞራውያንንም ምድር ርስት አድርጌ ሰጠኋችሁ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የአሞራዊውንም ምድር ትወርሱ ዘንድ ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፤ በምድረ በዳም አርባ ዓመት መራኋችሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የአሞራዊውንም ምድር ትወርሱ ዘንድ ከግብጽ ምድር አወጣኋችሁ፥ በምድረ በዳም አርባ ዓመት መራኋችሁ። |
ስለዚህም ከግብጻውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ሰፊና ለም ወደሆነችው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ።
እነርሱም፣ ‘ከግብጽ ምድር ያወጣን፣ በወና ምድረ በዳ፣ በጐድጓዳና በበረሓ መሬት፣ በደረቅና በጨለማ ቦታ፣ ሰው በማያልፍበትና በማይኖርበት ስፍራ የመራን እግዚአብሔር ወዴት ነው?’ ብለው አልጠየቁም።
“እናንተ እስራኤላውያን፣ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁምን?” ይላል እግዚአብሔር “እስራኤልን ከግብጽ፣ ፍልስጥኤማውያንን ከቀፍቶር፣ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን?
እነዚህም ስለ ሰለሏት ምድር በእስራኤላውያን መካከል እንዲህ የሚል መጥፎ ወሬ አሠራጩ፤ “ያየናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ናት፤ እዚያ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ግዙፎች ናቸው፤
የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ስለ ነደደ፣ በፊቱ ክፉ ነገር ያደረገው ያ ትውልድ በሙሉ እስኪያልቅ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ እንዲንከራተቱ አደረጋቸው።
እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ ዘወር አለ፤ ያመልኳቸውም ዘንድ ለሰማይ ከዋክብት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም በነቢያት መጽሐፍ እንዲህ ተብሎ በተጻፈው መሠረት ተፈጸመ፤ “ ‘እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አርባ ዓመት በምድረ በዳ፣ መሥዋዕትንና ቍርባንን አቅርባችሁልኝ ነበርን?
ይማረካሉ ያላችኋቸው ታናናሾች፣ ክፉና በጎውን ለይተው የማያውቁት ልጆቻችሁ ምድሪቱን ይገቡባታል፤ ለእነርሱም እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ይወርሷታል።
አምላካችሁ እግዚአብሔር በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ባርኳችኋል፤ በዚህ ጭልጥ ባለው ምድረ በዳ ባደረጋችሁት ጕዞ ጠብቋችኋል። በእነዚህ አርባ ዓመታት አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ነበርና አንዳችም ነገር አላጣችሁም።
“ ‘በምሥራቅ ዮርዳኖስ ወደሚኖሩት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ እነርሱ ወጓችሁ፤ እኔ ግን አሳልፌ በእጃችሁ ሰጠኋቸው፤ ከፊታችሁ አጠፋኋቸው፤ እናንተም ምድራቸውን ወረሳችሁ።