2 ቆሮንቶስ 3:14 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ነገር ግን ብሉይ ኪዳን በተነበበ ቍጥር፣ ያ መሸፈኛ እስከ ዛሬ ድረስ ስላልተወገደ ልቡናቸው እንደ ደነዘዘ ነው፤ መሸፈኛው አሁንም አልተወገደም፤ የሚወገደው በክርስቶስ ብቻ ነውና። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ብሉይ ኪዳን ሲነበብ ያ መጋረጃ ሳይወገድ እስከ ዛሬ ድረስ በመኖሩና፥ በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና፥ አሳባቸው ደነዘዘ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የእነርሱ ልቡና በእርግጥ ደንዝዞአል፤ እስከ ዛሬም ድረስ የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ሲያነብቡ ልቡናቸው በዚያው መሸፈኛ እንደ ተሸፈነ ነው። ይህም የሚሆነው ያ መሸፈኛ የሚወገደው በክርስቶስ ብቻ ስለ ሆነ ነው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ልባቸው ተሸፍኖአል፤ ያም መጋረጃ ብሉይ ኪዳን በተነበበት ዘመን ሁሉ ጸንቶ ኖሮአል፤ ክርስቶስ እስኪያሳልፈው ድረስ አልተገለጠምና። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ነገር ግን አሳባቸው ደነዘዘ። ብሉይ ኪዳን ሲነበብ ያ መጋረጃ ሳይወሰድ እስከ ዛሬ ድረስ ይኖራልና፤ በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና። |
የእስራኤል ጠባቂዎች ዕውሮች ናቸው፤ ዕውቀት የላቸውም፤ ሁሉም ድምፅ የለሽ ውሾች ናቸው፤ መጮኽ አይችሉም፤ ተጋድመው ያልማሉ፤ እንቅልፍ ይወድዳሉ።
በቅጥሩ ላይ እንደ ዕውር ተደናበርን፤ አካሄዳችንም ዐይን እንደሌላቸው በዳበሳ ሆነ፤ ጀንበር በምትጠልቅበት ጊዜ እንደሚሆነው በእኩለ ቀን ተደናበርን፤ በብርቱዎች መካከልም እንደ ሙታን ሆንን።
የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፤ ጆሯቸውን ድፈን፤ ዐይኖቻቸውንም ክደን፤ ይህ ካልሆነማ፣ በዐይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው፣ በልባቸውም አስተውለው በመመለስ ይፈወሳሉ።”
“የሰው ልጅ ሆይ፤ በዐመፀኛ ሕዝብ መካከል ተቀምጠሃል፤ የሚያዩበት ዐይን አላቸው፤ ነገር ግን አያዩም፤ የሚሰሙበትም ጆሮ አላቸው፤ ነገር ግን አይሰሙም፤ ዐመፀኛ ሕዝብ ናቸውና።
ዐይንህ ታማሚ ከሆነ ግን መላው ሰውነትህ በጨለማ የተሞላ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፣ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን?
ኢየሱስ እንደ ገና ለሰዎቹ፣ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝም የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ ከቶ በጨለማ አይመላለስም” አላቸው።
ከሚያዳምጡትም ሴቶች መካከል ልድያ የምትባል አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም እግዚአብሔርን የምታመልክና ከትያጥሮን ከተማ የመጣች የቀይ ሐር ነጋዴ ነበረች። ጌታም፣ ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል ትሰማ ዘንድ ልቧን ከፈተላት።
አንተም ዐይናቸውን ትከፍታለህ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ትመልሳቸዋለህ፤ እነርሱም የኀጢአትን ይቅርታ ይቀበላሉ፤ በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስት ያገኛሉ።’
ወንድሞች ሆይ፤ ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ፣ ይህን ምስጢር ሳታውቁ እንድትቀሩ አልፈልግም፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ እስራኤል በከፊል በድንዳኔ ውስጥ ዐልፋለች።
እርሱም በፊደል ላይ ሳይሆን በመንፈስ ላይ የተመሠረተውን የአዲሱ ኪዳን አገልጋዮች እንድንሆን ብቁዎች አደረገን፤ ምክንያቱም ፊደል ይገድላል፤ መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።
በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እግዚአብሔር የክብሩን ዕውቀት ብርሃን ይሰጠን ዘንድ፣ “በጨለማ ብርሃን ይብራ” ያለው እግዚአብሔር ብርሃኑን በልባችን አብርቷልና።