1 ዮሐንስ 5:11 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ምስክርነቱም ይህ ነው፤ እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት ሰጠን፤ ይህም ሕይወት ያለው በልጁ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ምስክርነቱ ይህ ነው፦ እግዚአብሔር የዘለዓለምን ሕይወት ሰጠን፥ ይህም ሕይወት ያለው በልጁ ነው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ምስክርነቱም እግዚአብሔር የዘለዓለም ሕይወት እንደ ሰጠንና ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ የሚመሰክር ነው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። |
ዐጫጁ አሁንም ቢሆን እንኳ ደመወዙን እየተቀበለ ነው፤ ለዘላለም ሕይወት ይሆን ዘንድ አዝመራውን ይሰበስባል፤ ይህም ዘሪውና ዐጫጁ በጋራ ደስ እንዲላቸው ነው።
ይህም የሆነው ኀጢአት በሞት እንደ ነገሠ ሁሉ፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ደግሞ የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ እንዲነግሥ ነው።
ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ በርሱ ለሚያምኑና የዘላለምን ሕይወት ለሚቀበሉ ወሰን የሌለው ትዕግሥቱን ከኀጢአተኞች ዋና በሆንሁት በእኔ እንደ ምሳሌ አድርጎ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ።
ፍቅር ይህ ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው ሳይሆን እርሱ እንደ ወደደንና ስለ ኀጢአታችን ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ልጁን መላኩ ነው።
እግዚአብሔር ፍቅሩን በመካከላችን የገለጠው እንዲህ ነው፤ እኛ በርሱ አማካይነት በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከ።
በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን ሁሉ በልቡ ምስክር አለው፤ ማንም እግዚአብሔርን የማያምን ሁሉ እግዚአብሔር ስለ ልጁ የሰጠውን ምስክርነት ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።
የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ፣ እውነተኛ የሆነውን እርሱን እንድናውቅ ማስተዋልን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እኛም እውነተኛ በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አለን። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።
ለድሜጥሮስ፣ ሰው ሁሉ ይመሰክርለታል፤ እውነት ራሷም ትመሰክርለታለች፤ እኛ ደግሞ እንመሰክርለታለን፤ እናንተም ምስክርነታችን እውነት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ።