አብድዩ 1:10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “የወንድምህን የያዕቆብን ዘሮች በግፍ ስለ ገደልክ፥ ትዋረዳለህ፤ ለዘለዓለምም ትጠፋለህ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፣ በዕፍረት ትሸፈናለህ፤ ለዘላለምም ትጠፋለህ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለተደረገው ግፍ እፍረትን ትከናነባለህ፤ ለዘለዓለምም ትጠፋለህ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለ ተደረገ ኀጢአትና ግድያ ኀፍረት ይከድንሃል፤ ለዘለዓለምም ትጠፋለህ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለ ተደረገ ግፍ እፍረት ይከድንሃል፥ ለዘላለምም ትጠፋለህ። |
አባቱ ስለ መረቀው ዔሳው ያዕቆብን አጥብቆ ጠላው፤ በልቡም “አባቴ በቅርብ ቀን ይሞታል፤ ከዚያ በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ” ብሎ አሰበ።
እግዚአብሔር ሆይ! ኢየሩሳሌም በተያዘችበት ቀን ኤዶማውያን ያደረጉትን አስብ፤ “እስከ መሠረትዋ አፈራርሳችሁ ጣሉአት!” እያሉ መጮኻቸውንም አስታውስ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ለሕዝቤ ለእስራኤል የሰጠኋቸውን ምድር ስላጠፉት ስለ እስራኤል ጐረቤቶችም የምናገረው ነገር አለኝ፤ እነዚያን ክፉ ሕዝቦች ከየአገራቸው ነቃቅዬ እወስዳቸዋለሁ፤ የይሁዳንም ሕዝብ ከመካከላቸው መንጥቄ አወጣቸዋለሁ።
እኛና የቀድሞ አባቶቻችን በመደጋገም ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔር አምላካችንን አሳዝነናል፤ ትእዛዞቹንም አልፈጸምንም፤ ስለዚህ በዕፍረት ልንወድቅና ውርደትም እንደ ልብስ ሊሸፍነን ይገባል።”
የቦጽራ ከተማ አስፈሪ ምድረ በዳ ሆና እንደምትቀር እኔ በራሴ ምዬአለሁ፤ ሕዝብ ሁሉ መቀለጃ ያደርጋታል፤ ስሟንም እንደ ርግማን ይቈጥሩታል። በአቅራቢያዋ ያሉ መንደሮች ሁሉ ለዘለዓለም ፍርስራሾች ሆነው ይቀራሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
‘ስለ ተሰደብን አፈርን፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ወደ ተቀደሱ ስፍራዎች ባዕዳን ሰዎች ስለ ገቡ ተዋርደን አንገታችንን ደፋን።’ በሉ።
እናንተ በዑፅ ምድር የምትኖሩ የኤዶም ሕዝብ ሆይ ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ! ይሁን እንጂ የእናንተም ጽዋ ተራውን ጠብቆ በመምጣት ላይ ነው፤ እናንተም ሰክራችሁ ትራቈታላችሁ።
የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! የበደላችሁ ቅጣት አብቅቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ በስደት እንድትኖሩ አያደርጋችሁም፤ ነገር ግን የኤዶም ሕዝብ ሆይ! የእናንተን በደል ይቀጣል፤ ኃጢአታችሁንም ያጋልጣል።
እኔ ለዘለዓለሙ ምድራችሁን ባድማ አደርጋለሁ፤ ዳግመኛም በከተሞቻችሁ የሚኖር አይገኝም፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ታውቃላችሁ።
“የግብጽና የኤዶም ሰዎች በይሁዳ ሕዝብ ላይ ግፍ ስለ ፈጸሙና ንጹሑንም ሕዝብ ስለ ገደሉ፥ ‘ግብጽ ወደ በረሓነት ትለወጣለች፤ ኤዶምም ሰው የማይኖርባት ምድረ በዳ ትሆናለች።’
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የኤዶም ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ወንድሞቻቸውን እስራኤላውያንን በሰይፍ አሳደዋቸዋል፤ ከያዙአቸውም በኋላ ርኅራኄ አላደረጉላቸውም፤ በእነርሱ ላይ ያላቸው ቊጣ ሊበርድም አልቻለም፤
ጠላቴም ይህን ሁሉ ያያል፤ “አምላክህ እግዚአብሔር የት አለ?” ይለኝ የነበረው ጠላቴ ኀፍረትን ይከናነባል፤ እኔ የጠላቴን ውድቀት አያለሁ፤ በመንገድ ዳር እንዳለ ጭቃ ሲረገጥም እመለከታለሁ።