ኢዮብ 1:1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ዑፅ ተብላ በምትጠራ አገር ኢዮብ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ከክፉ ነገር ሁሉ ርቆ እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ ምንም ነውር የሌለበት፥ ቅን ሰው ነበር። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ዖፅ በሚባል አገር የሚኖር ኢዮብ የተባለ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ዖፅ በሚባል አገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ ያም ሰው ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ነበረ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) አውስጢድ በሚባል ሀገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ ያም ሰው ቅን፥ ንጹሕና ጻድቅ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፉ ሥራም ሁሉ የራቀ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ዖፅ በሚባል አገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፥ ያም ሰው ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ነበረ። |
አብራም 99 ዓመት በሆነው ጊዜ እግዚአብሔር ተገለጠለትና “እኔ ኤልሻዳይ ሁሉን የምችል አምላክ ነኝ፤ ለእኔ በመታዘዝ ዘወትር ትክክል የሆነውን ነገር አድርግ፤
መልአኩም “ልጁን አትንካ፤ ምንም ዐይነት ጒዳት አታድርስበት፤ አንድ ልጅህን እንኳ ለእኔ ከመስጠት ስለ አልተቈጠብክ እነሆ፥ እኔን እግዚአብሔርን የምትፈራ መሆንህን ተረድቼአለሁ።”
“እግዚአብሔር ሆይ! በታማኝነትና በቅንነት እንዳገለገልኩህ፥ አንተ የምትደሰትበትንም ነገር ለማድረግ ዘወትር እጥር እንደ ነበር ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ!” እያለ በመጸለይ ምርር ብሎ አለቀሰ።
የሴም ልጆች፦ ዔላም፥ አሦር፥ አርፋክስድ፥ ሉድ፥ አራም፥ ዑፅ፥ ሑል፥ ጌቴርና ሜሼክ ሲሆኑ፥ እነርሱም በስሞቻቸው ለሚጠሩ ሕዝቦች የነገድ አባቶች ናቸው።
እግዚአብሔር ሰይጣንን “አገልጋዬን ኢዮብን ልብ ብለህ አየኸውን? እርሱን የመሰለ ታማኝና ደግ ሰው በምድር ላይ አይገኝም፤ እርሱ ከክፋት ሁሉ ርቆ እኔን የሚፈራ ቀጥተኛ ሰው ነው” አለ።
እግዚአብሔርም ሰይጣንን “አገልጋዬን ኢዮብን ልብ ብለህ አየኸውን? እርሱን የመሰለ ታማኝና ደግ ሰው በምድር ላይ አይገኝም፤ እርሱ ከክፋት ሁሉ ርቆ እኔን የሚፈራ ቀጥተኛ ሰው ነው፤ እርሱን ማጥፋት እንድትችል እፈቅድልህ ዘንድ ያነሣሣኸኝ በከንቱ ነው፤ እነሆ፥ ኢዮብ አሁንም በቅንነቱ እንደ ጸና ነው” አለው።
በተጨማሪ ግን ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መርጠህ በሕዝቡ ላይ የሺህ አለቆች፥ የመቶ አለቆች፥ የኀምሳ አለቆችና የዐሥር አለቆች አድርገህ ሹም። እነርሱ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፥ እምነት የሚጣልባቸውና በጉቦም የማይደለሉ ሰዎች መሆን አለባቸው።
እናንተ በዑፅ ምድር የምትኖሩ የኤዶም ሕዝብ ሆይ ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ! ይሁን እንጂ የእናንተም ጽዋ ተራውን ጠብቆ በመምጣት ላይ ነው፤ እናንተም ሰክራችሁ ትራቈታላችሁ።
እነዚያ ሦስት ሰዎች ማለትም ኖኅ፥ ዳንኤልና ኢዮብ በውስጥዋ ቢገኙ እንኳ በደግነታቸው ማትረፍ የሚችሉት የራሳቸውን ሕይወት ብቻ ነው፤ ይህን የተናገረ ጌታ እግዚአብሔር ነው።
ስለዚህ እኔ እግዚአብሔር ሕያው አምላክ እንደ መሆኔ ኖኅ፥ ዳንኤልና ኢዮብ እንኳ በዚያ ቢኖሩ በጽድቃቸው የራሳቸውን ሕይወት ብቻ ያድናሉ እንጂ የገዛ ልጆቻቸውን እንኳ ማዳን አይችሉም”፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ደግሞም እነዚያን በትዕግሥት የጸኑትን “የተባረኩ ናቸው” እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንዴት እንደ ታገሠ ሰምታችኋል። ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን መልካም ነገር አይታችኋል፤ በዚህም ጌታ መሐሪና ርኅሩኅ መሆኑን ተመልክታችኋል።