ኢሳይያስ 62:4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከእንግዲህ ወዲህ “የተተወች” ተብለሽ አትጠሪም፤ ምድርሽም “ባድማ” ተብላ አትጠራም። የምትጠሪበትም አዲስ ስም፥ “እግዚአብሔር በእርስዋ ደስ ይለዋል!” የሚል ይሆናል፤ ምድርሽም “ባለ ባል” ተብላ ትጠራለች፤ እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤ ምድርሽም ባል እንዳላት ሴት ትሆናለች። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከእንግዲህ፣ “የተተወች” ብለው አይጠሩሽም፤ ምድርሽም፣ “የተፈታች” አትባልም፤ ነገር ግን፣ “ደስታዬ በርሷ” ትባያለሽ፤ ምድርሽም፣ “ባለባል” ትባላለች፤ እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤ ምድርሽም ባለባል ትሆናለች። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከእንግዲህ ወዲህ፦ የተተወች አትባዪም፤ ምድርሽም ከእንግዲህ ወዲህ፦ ውድማ አትባልም፤ ነገር ግን ጌታ ደስታዬ ባንቺ ነው ብሏታልና፥ ምድርሽም ባል ታገባለችና አንቺ፦ ደስታዬ የሚኖርባት ትባያለሽ ምድርሽም፦ ባል ያገባች ትባላለች። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ከእንግዲህ ወዲህ፥ “የተተወች” አትባዪም፤ ምድርሽም ከእንግዲህ ወዲህ፥ “ውድማ” አትባልም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ብሎታልና፥ ምድርሽም ባል ታገባለችና አንቺ፥ “ደስታዬ የሚኖርባት” ትባያለሽ፤ ምድርሽም፥ “ባል ያገባች” ትባላለች። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ከእንግዲህ ወዲህ፦ የተተወች አትባዪም፥ ምድርሽም ከእንግዲህ ወዲህ፦ ውድማ አትባልም፥ ነገር ግን እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ብሎታልና፥ ምድርሽም ባል ታገባለችና አንቺ፦ ደስታዬ የሚኖርባት ትባያለሽ ምድርሽም፦ ባል ያገባች ትባላለች። |
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ባል ካላት ሴት ይልቅ ፈት የሆነችው ልጆች ብዛት ያላቸው ስለ ሆነ፥ ልጅ እንዳልወለደችና አምጣ እንደማታውቀው ሴት የሆንሽው ኢየሩሳሌም ሆይ! እልል እያልሽ ዘምሪ!
“ከዚህ በፊት የተተውሽና የተጠላሽ ሆነሽ ማንም በአንቺ በኩል የማያልፍ የነበረ ቢሆንም እንኳ፥ የዘለዓለም መመኪያና በየትውልዱ ሁሉ መደሰቻ እንድትሆኚ አደርግሻለሁ።
ከእንግዲህ ወዲህ በምድርሽ የዐመፅ ድምፅ በድንበሮችሽም ጥፋት ወይም ውድመት አይሰማም፤ ነገር ግን ቅጥሮችሽን መዳን የቅጥር በሮችሽን ምስጋና ብለሽ ትጠሪአቸዋለሽ።
እኔ በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ ሁለንተናዬም በአምላኬ ሐሴትን ያደርጋል፤ የአበባ አክሊል በራሱ ላይ እንደሚያደርግ ሙሽራ፥ በጌጣጌጥም እንዳሸበረቀች ሙሽሪት አድርጎ፥ የመዳንን ልብስ አልብሶኛል፤ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛል።
ሕዝቡ “የተቀደሱና እግዚአብሔር የታደጋቸው ወገኖች” ተብለው ይጠራሉ፤ አንቺም ኢየሩሳሌም “የተፈለገችና ያልተተወች ከተማ” ተብለሽ ትጠሪአለሽ።
ጐልማሳ ድንግሊቱን ሙሽራ አድርጎ እንደሚወስድ፥ የፈጠረሽ እግዚአብሔርም ለአንቺ እንደ ባል ይሆንልሻል፤ ወንዱም ሙሽራ በሴትዋ ሙሽራ ደስ እንደሚሰኝ፥ እግዚአብሔርም በአንቺ ደስ ይለዋል።
“እናንተ እምነት የማይጣልባችሁ ሕዝብ ሆይ! የእኔ ስለ ሆናችሁ ተመለሱ፤ ከእናንተ መካከል ከየአንዳንዱ ከተማ አንዳንድ፥ ከእያንዳንዱም ቤተሰብ ሁለት ሁለት መርጬ ወደ ጽዮን ተራራ አመጣችኋለሁ።
ለኢየሩሳሌም የማደርጋቸውን መልካም ነገሮች ሁሉ በሚሰሙት ሕዝቦች ፊት ለእኔ ገናናነት፥ ክብርና ምስጋናን ታስገኛለች፤ ለኢየሩሳሌም ሕዝብ የማደርገውን መልካም ነገሮችና ለከተማይቱ የማመጣላትን ሀብትና በጎነት በሚሰሙበት ጊዜ አሕዛብ ሁሉ በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ።”
ተመልካችም ሁሉ ‘ጭራሽ ምድረ በዳ ሆና የነበረች ይህች ምድር እንዴት የዔደንን ገነት መሰለች! ቀድሞ ባድማ ወናና የፍርስራሽ ክምር ሆነው የነበሩትስ ከተሞች እንዴት እንደገና ሕዝብ ሊኖርባቸውና የተመሸጉ ሊሆኑ ቻሉ?’ ይላሉ።
እግዚአብሔር አምላክሽ ከአንቺ ጋር ነው፤ በኀይሉም ድልን ያጐናጽፍሻል፤ እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩም ያድስሻል፤ ሕዝቦች በበዓል ቀን በመዝሙር እንደሚያደርጉት፥ እርሱ በአንቺ ይደሰታል።”
ሙሽሪት ያለችው ሰው ሙሽራ ነው፤ የሙሽራው ሚዜ ግን ከሙሽራው አጠገብ ቆሞ ይሰማዋል፤ የእርሱንም ድምፅ በመስማት ይደሰታል፤ ስለዚህ የእኔም ደስታ ይህ ነው፤ እርሱም አሁን ፍጹም ሆኖአል።
እንደ አንዲት ንጽሕት ልጃገረድ በድንግልናዋ ለአንድ ባል እንደምትታጭ እኔም እናንተን ለክርስቶስ ስላአጨኋችሁ ስለ እናንተ መንፈሳዊ ቅናት እቀናለሁ።
በምትሠራው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ያበለጽግሃል፤ ልጆችህን፤ እንስሶችህንና የምድርህን ሰብልና ፍሬ ያበዛልሃል፤ እግዚአብሔር የቀድሞ አባቶችህን በማበልጸግ ደስ ይለው እንደ ነበር አንተንም በማበልጸግ ደስ ይለዋል።
እናንተ ቀድሞ የእግዚአብሔር ሕዝብ አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ናችሁ፤ ቀድሞ ምሕረት አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረት አግኝታችኋል።