ኢሳይያስ 55:1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውሃው ኑ! የምትገዙበት ገንዘብ የሌላችሁ ኑና ገዝታችሁ ብሉ! ኑና ያለ ገንዘብና ያለ ዋጋ ወተትና የወይን ጠጅን ግዙ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም “እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ኑ፤ እናንተ ገንዘብ የሌላችሁ፣ ወደ ውሆች ኑ፤ ኑና ግዙ፤ ብሉም! ኑና ያለ ገንዘብ፣ ያለ ዋጋ፣ የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ሂዱ፤ ገንዘብም የሌላችሁ ሂዱና ግዙ፤ ብሉ፤ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ጠጡ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፥ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። |
እግዚአብሔር ሆይ! አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ለማግኘት በብርቱ እናፍቃለሁ፤ ሁለንተናዬ አንተን ይመኛል፤ ውሃ በማጣት ደርቆ እንደ ተሰነጣጠቀ መሬት ነፍሴ አንተን ተጠማች።
እጄን ይዘህ ሳበኝ፤ አብረን እንሩጥ። ንጉሡ ወደ እልፍኙ አስገባኝ፤ በዚያም አብረን ደስ ይለናል፤ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ ያስደስታል፤ ስለዚህ ቈነጃጅት ሁሉ እጅግ ያፈቅሩሃል።
እኅቴ ሙሽራዬ ሆይ! እነሆ ወደ አትክልት ቦታዬ ገባሁ፤ ከርቤዬንና የሽቶ አበባዎቼን ለቀምኩ፤ የማር ሰፈፌን ከወለላው ጋር ተመገብኩ፤ የወይን ጠጄንና ወተቴንም ጠጣሁ። ወዳጆቼ ሆይ! በፍቅር እስክትረኩ ድረስ ብሉ፥ ጠጡ።
“ለተጠማው ምድር ውሃን እሰጣለሁ፤ በደረቀውም ምድር ጅረቶች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤ መንፈሴን በልጆችህ ላይ አፈሳለሁ፤ በረከትንም ለልጅ ልጆችህ እሰጣለሁ።
ከዚያም በኋላ ወደ ቤተ መቅደሱ መግቢያ መለሰኝ፤ እዚያም ከቤተ መቅደሱ መድረክ ሥር ውሃ ወደ ምሥራቅ ይፈስ ነበር፤ (ይህም የቤተ መቅደሱ በር ወደ ምሥራቅ ዞሮ ስለ ነበረ ነው) ውሃውም የሚፈሰው ከቤተ መቅደሱ በስተደቡብ በኩል ባለው መድረክ ሥር ከመሠዊያው በስተደቡብ ነበር።
ውሃው በሚፈስበት ስፍራ ሁሉ ልዩ ልዩ ዐይነት እንስሶችና ዓሣም በብዛት ይገኛል፤ የወንዙ ፈሳሽ በሙት ባሕር የሚገኘውን በማደስ ያጠራዋል፤ በሚፈስበትም ቦታ ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የሕዝቤን አለመታመን ፈውሼ፤ ወደ እኔ እመልሳቸዋለሁ ቊጣዬ ከእነርሱ ስለ ተመለሰ፥ እኔ በገዛ ፈቃዴ እወዳቸዋለሁ፤
“በዚያን ጊዜ ተራራዎችም ሁሉ በወይን ተክል ይሸፈናሉ፤ በኰረብቶችም ላይ ብዙ ወተት የሚሰጡ ከብቶች ይሰማራሉ፤ በይሁዳ ምድር የሚገኙ ወንዞች ሁሉ በውሃ የተሞሉ ይሆናሉ፤ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ምንጭ ይፈልቃል፤ የሺጢምንም ሸለቆ ያጠጣል።
የእስራኤል ሕዝብ እንደ ብርቱ ጦረኞች ይሆናሉ፤ የወይን ጠጅ እንደ ጠጣ ሰውም ደስተኞች ይሆናሉ፤ ልጆቻቸውም ይህን ድል በማስታወስ ደስ ይላቸዋል፤ በእግዚአብሔርም ሐሤት ያደርጋሉ።
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይከላከልላቸዋል፤ እነርሱም ጠላቶቻቸውን ይደመስሳሉ፤ የጠላትንም የወንጭፍ ድንጋይ ይረጋግጣሉ፤ የወይን ጠጅ ጠጥቶ እንደ ሰከረ ሰው ይጮኻሉ፤ የጠላቶቻቸውም ደም የመሥዋዕት ደም በሳሕን ሞልቶ በመሠዊያ ላይ እንደሚፈስስ ይፈስሳል።
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማይ በእርሻ ውስጥ የተሸሸገውን ሀብት ትመስላለች። አንድ ሰው ይህን ሀብት ባገኘው ጊዜ መልሶ ደበቀው፤ ከደስታውም ብዛት የተነሣ ሄደና ያለውን ሁሉ ሸጦ ያንን እርሻ ገዛ።”
በአባቴ መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ ጭማቂ ከእናንተ ጋር እስከምጠጣበት ቀን ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም እላችኋለሁ፤”
ጠንካራ ምግብ መብላት እንደማይችሉ ሕፃናት ስለ ሆናችሁ እኔ የመገብኳችሁ ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም፤ አሁንም ቢሆን ጠንካራ ምግብ መመገብ ገና የማትችሉ ናችሁ።
ከዚህም በኋላ እንዲህ አለኝ፤ “ተፈጸመ! አልፋና ዖሜጋ፥ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ፤ ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ ያለ ምንም ዋጋ በነጻ እሰጠዋለሁ፤
መንፈስ ቅዱስና ሙሽራይቱ “ና!” ይላሉ፤ የሚሰማም “ና!” ይበል፤ የተጠማም ይምጣ፤ የፈለገም የሕይወትን ውሃ ያለ ምንም ዋጋ በነጻ ይጠጣ።
ሀብታም ለመሆን በእሳት የተፈተነውን ወርቅ ከእኔ እንድትገዛ፥ የራቊትነትህን ኀፍረት ለመሸፈን ነጭ ልብስ እንድትለብስ፥ ለማየትም እንድችል የዐይን መድኃኒት ገዝተህ እንድትቀባ እመክርሃለሁ።
ቦዔዝ በከተማው በር አጠገብ ወደሚገኘው መሰብሰቢያ አደባባይ ሄዶ ተቀመጠ፤ ከዚህ በፊት ቦዔዝ ስለ እርሱ የተናገረው የአቤሜሌክ የቅርብ ዘመድ ወደዚያው ቦታ መጣ፤ ቦዔዝም በስሙ ጠርቶ “ወንድሜ ሆይ! ወደዚህ መጥተህ አጠገቤ ተቀመጥ” አለው። እርሱም ወደዚያ ሄዶ ተቀመጠ።